>

ደቀ መዛሙርቱ ታሪክ ሰሩ ዝምታውንም ሰበሩ!!! (ዘመድኩን በቀለ)



ደቀ መዛሙርቱ ታሪክ ሰሩ ዝምታውንም ሰበሩ!!!
 ዘመድኩን በቀለ
• ሀገርን ከእነ ድንበሩ፥ ነፃነትን ከነክብሩ፥ ፊደልን ከነ ቁጥሩ፥ አንድነትን ከነ ጀግንነቱ ለሀገር ያስረከበች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይሄ ፈጽሞ አይገባትም። 
 
• ጮማውን ትበላላችሁ፥ ጠጉሩንም ትለብሳለችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳለችሁ፥ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የሚል ኃይለ ቃል ያረፈበት ባነርም አጽፈው ይዘው ወጥተዋል። 
★ ዝምታ፣ ትዕግስትም ልክ አለው። ምእመናን ከቀጠሉ፣ ካህናቱ ከመከሩ፣ ማኅበራት ከተሰባሰቡ ደግሞ ነገሩ መሬት ይረግጣል። መከባበር ሆይ እባክሽን በተሎ ነይ?
• ይሄ ማለት ምልክት ነው። መንግሥት አሁንም ቤተ ክርስቲያንን እንደ ችቦ፣ እንደ ደመራ ማንደድ ማስነደዱን፣ ካህናትና ምእመናንን በመንበሩ ፊት እንደ ሽንኩርት መቀርደዱን፣ መክተፍ እንደ በግም ማረዱን ካላቆመም፣ ካላስቆመም የከፋ ነገር እንደሚከሰት ጠቋሚ ምልክት ነው።
• ደቀ መዛሙርቱን ባለፈው ጊዜ መውቀሴ ይታወሳል። አሁንም ማኅበራት፣ በተለይ ከማኅበረ ቅዱሳን ብዙ ይጠበቃል። ማብራሪያ የመጠየቅ ሥልጣንም አቅምም አለው። ካህናትም፣ መነኮሳትም፣ ምእመናንም በህጋዊ መልኩ መንግሥትን የመጠየቅ ተፈጥሮአዊም ሕገ መንግሥታዊም መብት አላችሁ። እናም ሰብሰብ ብላችሁ ጠይቁ።
~ አዲስ አበባ 
• ደቀ መዛሙርቱ በፖሊስ አካላት ፓትሪያርኩን ለማናገር ቅድሚያ ታከለ ኡማ መፍቀድ አለበት ቢባሉም ደቀ መዛሙርቱ ግን ቀኖናዊ አካሄድ አይደለም በማለት የፖሊስን መመሪያ አልተቀበሉትም። ለካ ታከለ ኡማ የፓትሪያርኩም አዛዥ ኖሯል?
• በፌደራል ፖሊስ እና በአድማ በታኝ ፖሊስ ቢከበቡም እነሱ ግን ከምትቃጠለው ቤተ ክርስቲያንና ከሚታረዱት ካህናትና ምእመናን የበለጠ የከፋ ነገር አይገጥመንም በማለት በድፍረት ፍርሃትን አሸንፈው ጥያቄያአቸውን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት አቅርበዋል።
• የአድማ በታኙን ኃይል “ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ እስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በማነጋገር ልጆቻችን ሰላማዊያን ናቸው። ጥያቄያቸውም ተገቢ ነው። እናም በሰለም ወደ መጣችሁበት ተመለሱ በማለት አደጋ ለመጣል የመጡትን ደም የጠማቸው ፌደራሎች መልሰዋል ተብሏል።
• ከሁሉም ብሔር ብሔረ ሰቦች የተውጣጡት እኒሁ የቤተክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች በተለያዩ ቋንቋዎች ለሚዲያ አካላት ቃለ መጠይቅ መስጠታቸውም ተነግሯል። በተለይ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተማሪዎች የሳስተላለፉት መልእክት ልብ ይሰብር እንደነበርም ተነግሯል።
•••
ዛሬ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪዎችና የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ለሁለተኛ ጊዜ ለታሪክ የሚቀመጥ ተግባር በዛሬው ዕለት ፈጽመው ተገኝተዋል። ደቀ መዛሙርቱ ከእስከ ዛሬው ተመራቂዎች የሚለያቸው የሚማሩት ለሆዳቸው ብቻ እንዳልሆነ ማሳየታቸው ነው። በሸዋ በሰላሌ ኤጄሬና በአጣየ፣ በካራ ቆሬ፣ በሰንበቴ፣ በማጀቴ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያኮረፈ ፖለቲከኛ ሁሉ እየተነሳ እሳት ለሚለኩስባት እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ድምጻቸውን በአደባባይ ሲያሰሙ አርፍደዋል።
•••
ደቀመዛሙርቱ በዛሬው የአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄአቸውን እንዳያቀርቡ የአድማ በታኝ ፖሊስ ቢላክባቸውም እነሱ ግን ነገሩን ከቁብም ሳይቆጥሩ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሆን ተብሎ በሚፈጸም ቃጠሎ የቤተክርስቲያኗ አመራሮች ዝምታስ እሰከ መቼ ነው? ብለው በመጠየቅ ጥያቄአቸውን ሲያሰሙ አርፍደዋል።
•••
ከጅማ በሻሻ ጀምሮ ከጅጅጋ እሰከ ሰላሌና አጣዬ ቆሬ ሜዳ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የቤተ ክርስቲያንን እንደ ችቦ የማንደድ አስጸያፊ ተግባር የመንግሥቱም የቤተክህነቱም እያየ ዝምታን መምረጥ ግራ የሚያጋባ መሆኑንም በድፍረት ገልጸዋል።
• “ ሀገር የተባለች ቤተክርስቲያን ስትቃጠል የቅዱስ ሲኖዶስ ዝምታ እስከ መቼ ነው?
• እረኞች በጎቼን ስለማይፈልጉ ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ በጎቼ ለምድር አራዊትም መብል ሆነዋል። ሕዝ ምእራፍ 34፣
•የንጹሐን ደም ሲፈስና ቅድስት ቤተክርስቲያን ስትቃጠል መንግሥት ዝም ሊል አይገባም።
• መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ የስምህን ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።  መዝ 74፣ 7
• ሀገርን ከእነ ድንበሩ፥ ነፃነትን ከነክብሩ፥ ፊደልን ከነ ቁጥሩ፥ አንድነትን ከነ ጀግንነቱ ለሀገር ያስረከበች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይሄ ፈጽሞ አይገባትም።
• ጮማውን ትበላላችሁ፥ ጠጉሩንም ትለብሳለችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳለችሁ፥ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የሚል ኃይለ ቃል ያረፈበት ባነርም አጽፈው ይዘው ወጥተዋል።
• ደቀ መዛሙርቱ የጋራ መግለጫም ያወጡ ሲሆን ይህንንም በጽሑፍ ለቤተክርስቲያኒቷ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትና በተዋረድ ላሉት ለተጠያቂ አካላት ልከዋል።
•••
ለዝምታም ይሁን ለትዕግስት መጠንና ልክ ያለው ከመሆኑ አንፃር ቤተክርስትያን ላይ እንዲሁም ምእመናኖቿና ካህናቶቿ ላይ ለዚህ የከፋ ጥቃት፣ ስቃይ፣ መከራና ስደት ስለማይደርስ የቅዱስ ሲኖዶሱና የመንጋው ጠባቂ እረኞች ዝምታ ይሰበርና ለቤተክርስቲያንቱ ህልውናና ክብር እንዲሁም ለመንጋው አልመጨነቅና አለማሰብ ሊያበቃ ይገባዋልም ብለዋል።
•••
መንግሥትም የዜጎችን ሞት፣ ስደትና መከራ እንዲሁም ለሀገር ባለውለታ የሆነች ቤተክርስቲያንን ውድመትና ጥፋት ከቃላት ባለፈ በተግባር ለመከላከልና ሕግና ሥርዓትን በማስጠበቅ ደረጃ ዳግም ችግሮች እንዳይከሰቱ መንግሥታዊ ግዴታውን ይወጣ ዘንድ በአፁንኦት እናሳስባለን በማለት ተማሪዎቹ ገልፀዋል።
በግልባጭም
•ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት • •ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በየደረጃቸው
•ለቅድስት የሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ
•ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ
•ለሰላም ሚኒስቴር
•ለሰላም ሚኒስቴር ለእምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አዲስ አበባ በማለት ለሁሉም በየአድራሻቸው ልከዋል።
ሰላም ለኢትዮጲያ 
ሰላም ለቅድስት ቤተክርስቲያንም ተመኝተዋል!!!
•••
ሻሎም !  ሰላም !
ሚያዝያ 4/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic