>
5:13 pm - Tuesday April 18, 9076

"ጎሳዬ ተስፋዬ"ዎች ወደቀልባችሁ ተመለሱ!!! (ዮናስ ሀጎስ)

“ጎሳዬ ተስፋዬ”ዎች ወደቀልባችሁ ተመለሱ!!!
ዮናስ ሀጎስ
* ተስፋህ ጎሳህ ብቻ ሲሆን ምንም ዓይነት ሎጂክ አያሳምንህም። ምንም ዓይነት ድርድር አያስማማህም። ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ውይይት አይገባህም። ምንም ዓይነት አመክንዮ ባንተ ተቀባይነት አይኖረውም!!!
 
 * ጎሳዬ ተስፋዬ ስትሆን አንተን የሚያሳምንህ በጉልበትህ የምታደርገው ነገር ብቻ ነው! ጉልበት ትግልን፤ ትግል ጦርነትን፤ ጦርነት ረሐብን፤ ረሐብ ቸነፈርን ይወልዳል። አንተ ግን ምንም ግድ አይሰጥህም!
•°•
ደቡብ ሱዳን እኔ በምኖርበት የካኩማ ስደተኛ ጣቢያ ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች አሏት። አብዛኛዎቹ ሴቶችና የወታደርነትን ምልመላ አምልጠው የመጡ ሕፃናት ናቸው። እዚሁ ካምፕ ውስጥ ተወልደው እዚሁ ተምረው ያደጉ ካልሆነ በቀር ደቡብ ሱዳን አዋቂ ወንድ ሆኖ የሚሰደድ ሰው ብዙም የላትም። ለምን ቢባል አዋቂ ወንዶች ጦርነት ላይ ናቸው። ጦርነቱ ደግሞ ና ውረድ እንውረድ ተባብለው የሆነ ጫካ አካባቢ ተገናኝተው የሚደረግ ሳይሆን ሕዝብ በሚኖርባቸው ጥቅጥቅ ያሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ነው እየተካሄደ ያለው።
•°•
አብዛኛዎቹ ስደተኞች መንደራቸው የነርሱ ጎሳ ባልሆነ ጦር ተወርሮ፣ ሴቶቹ ተደፍረው ወንዶቹ ተገድለው፣ ቤታቸው መንደሩ ሁሉ እሳት ተለቅቆበት ከዚያ በፈጣሪ ተዓምር ተርፈው የመጡ ናቸው። ካኩማ ካምፕ ውስጥ አንድ የአስራ ምናምን ዓመት ሱዳናዊ ወጣት አግኝተህ ስለ ሳይንስና ሒሳብ ብትጠይቀው ምንም እንደማያውቅ የታወቀ ነው። ስለ AK 47 ጠመንጃ አፈታት፣ የዒላማ ርቀት፣ home made ቦምብ እንዴት እንደሚሰራ፣ አንድ ምሽግ እንዴት መስበር እንደሚቻል ብትጠይቀው ግን ከሌላ ሐገር ረዘም ያለ ጊዜ በውትድርና ዓለም ከቆየ ወታደር በተሻለ መልኩ የተብራራ ምላሽ ሊሰጥህ ይችላል።
•°•
አልፎ አልፎ እዚሁ ካምፕ ውስጥ ጎሳን መሰረት ያደረገ ፀብ ይነሳል። ፀቡ በገጀራአ ድንጋይ፣ ጩቤና የመሳሰሉ ገዳይ መሳርያዎች የሚካሄድ ሲሆን ብዙ ጊዜ በትንሹ አስራ ምናምን ሰዎች ሞተው ነው የሚበርደው። በፀቡ ውስጥ ያንተ ሚና የሚወሰነው እንደ ጎሳህ ዓይነት ነው። ፀቡ በኑዌርና ዲንቃ ጎሳዎች መሐከል ከሆነ የፈለገ ጨዋ የኑዌር አሊያም የዲንቃ ተወላጅ ብትሆን ሕይወትህ አደጋ ላይ ነው። በማናቸውም መልኩ ባላሰብከው መንገድ ጥቃት ሊደርስብህ ይችላል። «አይ እሱ የለበትምና ተዉት…» ምናምን ዓይነት ምህረት በፍፁም ስለማታገኝ አንተም የግድ የፀቡ አካል ትሆናለህ። ደስ የሚለው ነገር በዚህ ሁሉ ፀብ መሐከል የሌላ ጎሳ አሊያም ዜግነት ያላቸው የካምፑ ነዋሪዎች ጫፋቸውን አይነኩም። ጧት ተነስተን ወደ ስራ/ትምህርት ቤት ልንሄድ ስንወጣ ታርዶ የተጣለ ወጣት፣ ሕፃን ልጅ ማየት የዛን ሰሞን ኖርም ይሆናል።
•°•
የሚገርመው ነገር ግን አብዛኞቹ ሱዳኖች በተለይ እዛው የተወለዱት ሐገራቸውን በጣም ነው የሚወዷት። ከዓመታት በፊት ነፃነቷን አውጃ ከሱዳን በተገነጠለችበት ወቅት በሐገራቸው ተስፋ በመሰነቅ የUNHCRንም ሆነ የማንንም እርዳታ ሳይፈልጉ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳኖች ወደ ሐገራቸው ተምመዋል። አሁንም በእንደዚህ ዓይነት መከራ ውስጥ ሆናም ደቡብ ሱዳኖች ከዚያ ካምፕ ወደ ሌላ ምዕራባዊ ሐገር መሻገርን አያልሙም። እዚያው ካምፕ ተቀምጠው ሐገራቸው ሰላም ሆና ወደዛው የሚመለሱበትን ቀን በጉጉት ይናፍቃሉ!
•°•
የካቶሊኩ ፖፕ እንግዲህ ይህንን ጥላቻ ነው በፍቅር ለማቆም ከደረጃቸው እጅግ ዝቅ ብለው እነዚህ የሰው ግማሽ ያልሆኑ ግዑዞች እግር ስር የተንበረከኩት። ምልጃቸው እነዚህ ግዑዛን ድንጋይ ልብ ውስጥ ገብቶ የሆነ ተፅዕኖ ፈጥሮ ስደተኞች ደቡብ ሱዳናውያን ወደሚናፍቋት ሐገራቸው ይመልሳቸው ይሆን?
—-
ከፍ ላለ ጉዳይ ዝቅ ማለት!!!!!
ይህ ምስል ሃይል አለው በሃይል ውስጥም ፍቅር አለው። ከምንምና ከማንም በላይ ብትሆንም ለፍቅርና ለሰላም ስትል መሬት ትወድቃለህ።
Filed in: Amharic