>
5:13 pm - Wednesday April 19, 5178

እሳት የሚጭረው ካጣ ይጠፋል!!! (ዳንኤል ክብረት)

እሳት የሚጭረው ካጣ ይጠፋል!!!

ዳንኤል ክብረት

ኢትዮጵያ መቀየር ካስፈለገ አስተሳሰብ ላይ ነው መሰራት ያለበት። አስተሳሰብ ካልተቀየረ የፈለገውን ነገር ብንሰራ ምንም ጥቅም የለውም

ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የዲስኩር፣ የወግ፣ የግጥም እና የሙዚቃ መርሃ ግብር ላይ ከቀረቡ ዲስኩሮች (መጋቤ አዕምሮዎች) መካከል ለዛሬ የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን እናስነብባችሁ። ሰሞኑን አንድ ዕድል ገጥሞኝ አጼ ምኒልክ የነበሩበትን ቤተ መንግስት ጎብኝቼ ነበር። ይሄ አራት ኪሎ ያለውና ‹‹የምኒልክ ቤተ መንግስት›› የምንለው ከመቶ ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ከእርሳቸው ጀምሮ አሁን እስካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ የሚኖሩበት ነው።

ይሄ ቦታ የእርሳቸው ትክል ነው። ከላይ ዙፋን ቤት የሚባለው ፍርድ ሲሰጡበት የነበረው ቦታ አለ። ከሥር እንደ አሁኑ ጊዜ ፍሪጅ ስለሌለ እጅግ ቀዝቃዛ የሆነ ምድር ቤት አላቸው። በዚያ በእርሳቸው ዘመን ያ ቀዝቃዛ ቤት ለጠጅ፣ ለጠላ፣ ለእንጀራ.. ማስቀመጫ ታስቦ የተሰራ ነው። ቀዝቃዛ ስለሆነ እንዳይበላሽ ይከላከላል። ለብዙ ዓመታት እንደዚህ ሲያገለግል ነው የቆየው። በኋላ ዘመን ተቀየረና የ1966ዓ.ም ዘመን ሲመጣ እሱ ቀርቶ፤ መጀመሪያ የ1963ቱ እያልን ምንጠራቸው የአጼ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት ታሰሩበት። እነርሱ ሲያስከለክሉበትና ሲያስችሉበት የነበረው ቦታ ላይ ታሰሩበት። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ረጅም ገመድ ውፍረቱ የሰው ክንድ የሚያክል ከግራና ከቀኝ በአርማታ ተሰርቶ እዚያ ላይ ሰዎች እየተንጠለጠሉ የወፌላላ መግረፊያ ሆነ።

ያ ገመድ አሁንም ድረስ አለ። ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ አበራ ጀንበሬ እዚያ ቦታ ላይ ታስረዋል። ‹‹የእስር ቤቱ አበሳ›› የሚል መጽሐፍ አላቸው። እዚያ መጽሐፋቸው ላይ እዚያ ቦታ ሲታሰሩ ማን ከማን አጠገብ ይተኛ እንደነበር በሥዕል ሳይቀር አስቀምጠውታል። እዚያ ቦታ ላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ በጣምነበር ያየሁት። ያ የዙፋን ቦታ፤ አጼ ምኒልክ፣ በተወሰነ መልኩም ልጅ ኢያሱና ንግሥት ዘውዲቱ፣ እስከተወሰነ ድረስ ተፈሪ ያን ቦታ ተጠቅመውበታል። ሲጠቀሙበት ከአጠገቡ ‹‹አስናቀ›› የሚባል ትልቅ አዳራሽ አለ። ብሔራዊ ቴአትር የሱን ያህል አይዝም። ከሦስት ሺህ እስከ አራት ሺህ ይይዛል።

አዳራሹ 110 ዓመት ይሆነዋል። አሁንም አለ፤ እዚያ አዳራሽ በየጊዜው ሰው እየገባ ይበላል። ግብር ማግባት የሚባል ባህል አላቸው። እሱን ባህል አንዳንድ ሰዎች የነገሥታቱን ስም ለማንገስ ብቻ የሚጠቀሙበት ይመስላቸዋል። ዓላማው በህዝብና በመንግስት መካከል ቀረቤታ ለመፍጠር ነው። ሰው ቤተ መንግስቱ የራሱ መሆኑንና በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ድልድይ ለመገንባት ነው። ግብሩ ሲቀር በመንግስትና በህዝብ መካከል ትልቅ ርቀት ነው የሚፈጠር። አንድ ሰሞን እኔ እንደማስታውሰው ወደ አጥሩ ዞር ብለን ስናይ ‹‹ወደዚያ አታይም?›› ይባላል። ውስጡ ገብቶ ግብር ይበላበት የነበረው በአይን እንኳን ለማየት የተከለከለበት ጊዜ ነበር ማለት ነው። በኋላም የመጡት ሰዎች ደግነቱ ቦታውን አላፈረሱትም። የቦታውን ጥቅም ቀየሩትና ግን ማሰሪያ፣ ቀጥሎም መግረፊያ ሆነ። አገር ምንድነው የምትሆነው? ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ›› የሚለውን በግልጽ የሚያሳይ ነገር ነው።

ቦታው ያው ቦታ ነው፤ ቅዝቃዜውም ያው ቅዝቃዜ ነው። ቦታውን መጀመሪያ የግብር መብያ፣ ቀጥሎ፣ ማሰሪያ፣ ቀጥሎ ደግሞ መግረፊያ ያደረገው ምንድነው? ካልን አስተሳሰብ ነው። ቦታው አልተቀየረም፤ በቦታው የሚቀመጡ ሰዎች በተቀየሩ ቁጥር ግን አገልግሎቱ ይቀየራል። መግረፊያ ሆነ፣ እስር ቤት ሆነ፤ ወደፊት ደግሞ ምን እንደሚሆን እናያለን። ኢትዮጵያ መቀየር ካስፈለገ አስተሳሰብ ላይነው መሰራት ያለበት። አስተሳሰብ ካልተቀየረ የፈለገውን ነገር ብንሰራ ምንም ጥቅም የለውም። ብዙ ጊዜ አገርን ከመሰረተ ልማት፣ ከቤት፣ ከመንገድ፣ ከድልድይ፣ ከግንብ፣ ከኢንዱስትሪ ጋር ብቻ ነው የሚታየው። የመጀመሪያውን ድልድይ በዓባይ በረሃ ላይ የሰራው ጣሊያን ነው። የሰራበት ዓላማ ግን የተለየ ነው፤ ኢትዮጵያን ለመግዛት በነበረው ሀሳብ ነው። የኢትዮጵያን ሀብቶች ወደ አገሩ ለመጫን እንዲያመቸው ነው። ህዝቡን እንደፈለገው ለመግዛት እንዲያመቸው ነው።

በኋላም ያደስነውና ጃፓን የሰራው ያው ድልድይ ነው። ጣሊያን ከወጣ በኋላ እኛ ተጠቀምንበት። አሁን ድልድዩን አይደለም የቀየርነው፤ አስተሳሰቡን ነው የቀየርነው። ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመግዛት የተጠቀመበትን ድልድይ አርበኞች ኢትዮጵያን ለማዳን ተጠቀሙበት፤ እኛ ደግሞ ይሄው ለመኖርእየተጠቀምንበት ነው። ብዙ ረጃጅም መንገዶች በጣሊያን ጊዜ የተገነቡ ናቸው፤ እነዚያን መንገዶች የገነባበት ሀሳብ ግን ሌላ ነበር፤ አሁን እኛ የምንጠቀምበት ነገር ደግሞ ሌላ ነው። ስለዚህ አገር የምትሰራው አዕምሮ ውስጥ ነው እንጂ ምድር ላይ ባለው ቁስ አይደለም። ብዙዎችን አይታችሁ እንደሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች የሚጠቀሙት ቀን ቀን ቢሮ ሲሆኑ ወይም ዋይፋይ ያለበት ቦታ ሲሆኑ ነው። ያንን ሲያይ ውሎ፤ በአስተያየቱም በምኑም ሲበሳጭ ውሎ ማታ ቤት ሲገባ ያወራል።

ይሄ ሊከሰት ነው፣ እንዲህ ሊመጣ ነው… እያለ ያወራል። ይሄንን ሲል የአራት ዓመት፣ የአምስት፣ የስድስት ዓመት ልጆች ይሰማሉ። አስተያየት አይሰጡም፤ ፌስቡክ የላቸውም፤ ግን ያ ሲወራ ይጨነቃሉ። ጥሩ ነገር ስንነግራቸው ደስ ይላቸዋል፤ የማይሆን ነገር ስንነግራቸው ደግሞ ውስጣቸው ይጨነቃል። ይሳቀቃሉ፤ ‹‹ምን ይፈጠር ይሆን›› ይላሉ፤ አይረዱትም። እኛ የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው አካል አለን፤ እነርሱ ግን የሚደግፉትም ሆነ የሚቃወሙት የላቸውም። አንድ ነገር ልማድ የሚሆነው ደጋግመን ስንሰራው ነው። በአገራችን ሟርት የሚባል ነገር አለ።

‹‹ሟርተኛ፣ ምላሱ ጥቁር ነው፤ እሱ የረገመው ይደርሳል›› ይባላል። ብዙ ጊዜም ይደርሳል። ለምንድነው የሚደርሰው? ‹‹አንተ ፀሐይ የሚመታህ ከሆነ እንዲህ ትሆናለህ›› ብሎ ሰውየው ይናገራል። እኛ ውስጥ ይሄን በተደጋጋሚ እንሰማዋለን። አይ አይሆንም ብለን አይደለም የምንተወው። አንድ ቀን ፀሐይ መቶን ራሳችንን ቢያመን እንቀበለዋለን። በተደጋጋሚ እሱን እንለዋለን። አዕምሯችን በዚህ መንገድ ይቀረጻል ማለት ነው። ከዚያ ራሳችን ወደ ሟርቱ ሄድን ማለት ነው። አሁን አገር ልትፈርስ ነው፣ ልንጫረስ ነው፣ልንባላ ነው… የሚለው በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው። ይሄን በነገርን ቁጥር ቀጥሎ የሚመጣው ትውልድ የሚያፈርስ ነው የሚሆነው። ለምን? አገር ማዳን የሚባል ነገር አልሰማም! ቋንቋ ነው ሰውን የሚፈጥረው። እስኪ ፌስቡክን ከፍታችሁ እዩ! ጥሩ ነገር ጻፉና እዩት! መጥፎ ቃላት ጻፉና እዩት፤ የሁለቱን የአንባቢ ብዛት አነፃፅሩት። ይሄ ቀጣዩ ትውልድ በየትኛው ሀሳብ ነው እየታነጸ ያለው የሚለውን ያሳየናል። እኛ የምናወራነውን ነገር ነው ልጆች የሚያወሩት። ትምህርት ቤት በእረፍት ሰዓት ከእኛ የሰሙትን ነው የሚያወሩት። የተነጋገሩትን መጥተው ደግሞ ይነግሩናል። እነርሱ ደግሞ በተረት አቅም ስለሆነ የሚረዱት ፍርሃት ነው የሚሰማቸው። ይሄንን ይዘው ነው የሚያድጉ። የነገዋ ኢትዮጵያ የተስተካከለች እንድትሆን ከፈለግን እኛ ነን ይሄን ክፉ ሀሳብ እምቢ ማለት ያለብን። አሁን የሚያስፈልገን የትውልድ ቃል ኪዳን ነው። ይሄን ይሄን አንቀበልም ብለን ማስወገድ አለብን።

ይሄንን ከተስማማን የነገዋን ኢትዮጵያ በእጃችን እንመሰርታታለን። አሁንም ድረስ ስለ 1966ቱ ትውልድ እየተነጋገርን ነው። እነርሱ ግማሾቹ ደክመዋል፤ ግማሾችም አርጅተዋል፤ ሌሎቹም ደግሞ የሉም። ግን አሁንም የእነርሱ ጉዳይ እኛ ጋ አለ፤ በእነርሱ ነው የምንዘወረው። ስለዚህ በተጻፈልን ነው እየኖርን ያለነው። ለምንድን ነው እኛ የማንጽፈው? ፌስቡክ ላይ ያልሆነ ነገር ሲጻፍ እኮ «ይሄ የእኛ አይደለም» ማለት አለብን። ማንኛውም እሳት እኮ የሚጭረው ካጣ ይጠፋል። እሳቱ እንዲጠፋ ከፈለግን ጫሪውን ነው መከልከል። እሳት ሲቀጣጠል መጀመሪያ ቀይ ይሆንና አስፈሪ ይሆናል፤ ይሄ እሳት ካልተነካካ፤ ካልተጫረ፤ ዝም ሲሉት ከሰል ይሆናል፤ ከዚያም አመድ ሆኖ ይቀራል! (ይቀጥላል)

Filed in: Amharic