>

ኦሮሞ ክልል እንላለን እንጂ እዚያው አማራ ክልልም ጒድ  አለ !!! (ግርማ ካሳ)

ኦሮሞ ክልል እንላለን እንጂ እዚያው አማራ ክልልም ጒድ  አለ !!!
ግርማካሳ
አንድ የገረመኝና ያሳዘነኝ ነገር ላውጋችሁ። አንድ ከደሴ የመጣ ሰው ነው የነገረኝ። ታውቃላችሁ በአማራ ክልል በአማርኛ አገልግሎት የማይሰጥበት አካባቢ እንዳለ  ኦህዴድ/ኦዴፓን ስንከስ ለካ ብአዴን/አዴፓ በሚያስተዳድረው ክልልን ዜጎች በአማርኛ መንግስታዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርጎ መብታቸው እየተገፈፈ ያለበት ሁኔታ አለ።
በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚባል በኦነግና በሕወሃት ተጠፍጥፎ የተሰራ  ዞን አለ። ዋና ከተማው ከሚሴ ነው። በዚህ ዞን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በብዛት አሉ። ሆኖም በዞኑ ባሉ ትላልቅ ከተሞች አብዛኛው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ነው። ከሚሴ፣ ባቲ፣ ሰንበቴ፣ ጨፋ ሮቢት … በመሳሰሉ ከተሞች።
ኦሮምኛ ተናጋሪ በብዛት ስላለ ኦሮምኛ የዞኑ የስራ ቋንቋ ተደርጓል። በኦሮምኛም ትምህርት በተለየ መልኩ ይሰጣል። ያ ተገቢ ነው።
ሆኖም ግን በዞኑ አማርኛ ፣ የፊዴራል የስራ ቋንቋ ሆኖ፣ የክልሉ የስራ ቋንቋ ሆኖ፣ በዞኖ የሚኖሩ አብዛኛ ነዋሪዎች አማርኛ ተናጋሪዎች ሆነው፣ አማርኛ በዞኑ የስራ ቋንቋ አለመሆኑ አስገራሚ ነው። በአማራ ክልል ባለው የኦሮሞያ ልዩ ዞን ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት  እያስተረጎሙ ነው አገልግሎት የሚያገኙት።
ባይገርማችሁ በዞኑ ያሉ አስተማሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች የመጡት ከወለጋና ከአርሲ ነው። የዞኑም የትምህርት ካሪኩለም. መማሪያ መጽሃፍት የሚዘጋጀው በኦሮሞ ክልል መንግስት ነው።
ይሄንን አፓርታዳዊ ዘረኛ የዞን አሰራር ዶ/ር አምባቸው አስቸኳይ ትኩረት ሰጥተዉት ማስቆም ያለባቸው ጉዳይ ነው ባይ ነኝ። በአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን ሁሉም እኩል መሆን አለባቸው። ኦሮምኛ ተናጋሪዎች መብታቸው መከበሩ ጥሩ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምሳሌ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ የሌላውን መብት መርገጥ ግን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
በኦሮሞ ክልል በዚያ ያሉን ዘረኞችን እየታገልን በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ነገር መኖሩ በጣም፣ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው !!!!!!!
ሌላም መሆን ያለበት የአማራ ክልል፣ በክልሉ የኦሮምኛ ትምህርት ሲሰጥ በኦነጎች በግዳጅ በሕዝቡ ላይ የተጫነውን  የላቲን ፊደል በመጠቀም ነው። የአማራ ክልል ያንን ማስቆም መቻል አለበት። የአገራችን ኩራት የሆነውን የግእዝ ፊደል ከበቂ በላይ  ኦሮምኛን ለመግልጽ ብቃት ያለው፣ ለህዝቡም የሚመቸው እርሱ ነውና በአማራ ክልል ኦሮምኛ በ ግእዝ ፊደል እንዲጻፍ መወሰኑ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ፍላጎት ማንጸባረቀ ነው። ኦህዴዶችን ለማባባል በሚል መሽኮርመም  አያስፈልግም። ኦህዴዶች ለማባባል በሚል ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር ወደ ጎን መደረግ የለበትም።”
Filed in: Amharic