>

"የአይወክሉንም መፈክር"  ውሎ ሲያድር የጋራ እሴት፣ ባህል፣ ታሪክ ከዛም አገር ያሳጣናል!!! (ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ)

“የአይወክሉንም መፈክር”  ውሎ ሲያድር የጋራ እሴት፣ ባህል፣ ታሪክ ከዛም አገር ያሳጣናል!!!
 ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ – ዶ/ር
በኢትዮጵያ አገር ማፍረስ እንደ ቀልድ እና እንደ ዋዛ እየታየ ነው። አንዱ ስለሌላው ሙያ በልብ ነው ብሎ የመጠፋፊያ ቢላዋ ከሳለ እና ሌላውም ራሱን ለመከላከል የራሱን ቢላዋ መሳል ከጀመረ አብሮ ለመኖር እና አብሮ አገር ለመገንባት ሳይሆን ለመጠፋፋት እና ለጦርነት ዝግጅት ጀምረናል ማለት ነው።
በመንግስት መ/ቤቶች አማራ ኦሮሞን፣ኦሮሞ ትግሬን፣ ሌላውም እንደዚሁ ሌላውን አይወክለኝም ማለት ከጀመረ ምንም የጋራ ተቋም፣ ምንም የጋራ አገር፣ ኢትዮጵያም ሆነች ኢትዮጵያዊነት የሉም ማለት ነው።
በኢትዮጵያ መንግስት መ/ቤቶች እና በኢትዮጵያ ከተሞች የኢትዮጵያዊነት ካባው ተነስቶ ሁሉም ብሄሩን መፈለግ ከጀመረ ቢያንስ 70% አከባቢ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ውክልና የለኝም ወይም በበቂ ሁኔታ አልተወከልኩም ብሎ “የአይወክሉንም መፈክር” መጀመር ይችላል። አሁን ባለንበት የጡዘት ፖላቲከ ይህ አካሄድ ከኢትዮጵያዊያን አእምሮ ውስጥ አብሮነቱን እና የጋራ አገርነቱን አጥፍቶ አገር ለማፍረሰ ካልሆነ በስተቀር የአገሩን ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ በሂደት እና በሰለጠነ መልኩ ለመፍታት አይረዳም።
ይህን የቆየ ውስብስብ ችግር ሳይገነዘብ ወይም ታዋቂነትን አገኛለሁ ብሎ አንድ ሰው ተነስቶ በተሰበሰበ ህዝብ መካከል ቆሞ ስለሌላው ብሄር ሲናገር ስለአንድ አገር ዜጋ ሳይሆን ከውጭ አገር ዜጋም ሰለ ጠላት አገር ዜጋ የሚናገር ይመስል ጦርነት እንክፈት ሲል ተሰብሳቢው ሲያጨበጭብ ማየት አገርቷ ምን አይነት አደጋ ውስጥ እንደገባች ካልታየን፣ እያየን እና እየሰማን አይደለንም ማለት ነው። ይህ መንገድ ህዝቡን አጨፋጭፈን አገር እናፈርሳለን ከማለት ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም። መንግስት እነዚህ መረን የወጡ ቃላት እና ንግግሮች ወደ ጥይት ጩኸት እና እንዱ እንዳለው “ሃያ ሚልዮን እሬሳ ወደ መፍጠር” ሳይለወጡ ህግ እና ስረዓት ማስከበር አለበት።
Filed in: Amharic