>

በቻይና እስር ቤት “የሞት ፍርድ” በመጠባበቅ ላይ ስለምትገኘው ኢትዮጵያዊት ድምጻችንን እናሰማ!!!   (ዘመድኩን በቀለ)


በቻይና እስር ቤት “የሞት ፍርድ” በመጠባበቅ ላይ ስለምትገኘው ኢትዮጵያዊት ድምጻችንን እናሰማ!!!
  ዘመድኩን በቀለ
 
★ ወላጅ እናቷ በድንጋጤ ግማሽ አካላቸው ፓራላይዝድ እንደሆነ ተናግሯል። 
 
★ አደገኛውን ዕፅ አስይዛ ወደ ቻይና የላከቻት እንደ እህት የምትቆጠራት ጓደኛዋ ሰናይት ካህሳይ በኢንተር ፖል ተይዛ ታስራ መፈተቷም ተነግሯል።
 
★ የስምረት ካህሳይ ድርጊት ሰው ሁሉ የአደራ ዕቃ ይዞ ለሰው እንዳይሄድ የሚያደርግና መተማመንን ከዜጎች መሃል የሚያጠፋ ክፉ ድርጊት ነው። 
#ETHIOPIA | ~ በቻይና እስር ቤት “የሞት ፍርድ” በመጠባበቅ ላይ ስለምትገኘው ኢትዮጵያዊት እህታችን ናዝራዊት አበራ ወንድሟ ያየህይራድ አበራ የተናገረውን “ Dagu Tube – ዳጉ ቲዩብ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
ሙሉ ታሪኩ…
•••
ወንድሟ ያየህይራድ ስለተፈጠረው ነገር ሲያስረዳ እንዲህ ይላል። “በቻይና እስር ቤት የምትገኘው እህቴ ናዝራዊት አበራ እና ዕቃውን አድርሺልኝ ያለቻት ጓደኛዋ ስምረት ትውውቃቸው የሚጀምረው ገና ከሃይስኩል ጀምሮ ነው። ውሏቸው ሁሉ ወይ እኛ ቤት ወይ ተክለሃይማኖት አካባቢ ያለው እነሱ ቤት ነበር።
•••
ከትምህርት በኋላ ወደ ስራ አለም ሲገቡ ፤ ናዝራዊት መሃንዲስ፣ ስምረት ደሞ የአየር መንገድ ሆስተስ ሆኑ።
•••
የዛሬ 3 ወር ገደማ ናዝራዊት በኢንጅነርነት ከምትሠራበት ድርጅት የፊኒሺንግ ዕቃዎችን እንደሚፈልግ የምታውቀው ስምረት አንድ ሃሳብ ታመጣለች።
•••
ከኔጋ አንድ የጉብኝት ፕሮግራም ወደ ቻይና ላመቻችና አብረን ተዝናንተን እንመለስ። ከዛ ድርጅቱ ዕቃ ሲፈልግ ልምዱ ስላለሽ አንቺን እንዲልክሽ ሀሳብ አቅርቢ ትላታለች።
•••
በሃሳቡ ተስማምታ አብረው ሊጓዙ ቅድመ ዝግጅቱ ሁሉ ካለቀ በኋላ ስምረት ካህሳይ ድንገት “ክፍለ ሀገር ገጠር ያለው አባቴ ስለሞተ እኔ መሄድ አልችልም። አንቺ ግን ዕድሉ እንዲያመልጥሽ ስለማልፈልግ መቅረት የለብሽም። እንደኔ ሆነው አገር እሚያሳዩሽ አሪፍ አሪፍ ጓደኞቼ እዛ ስላሉ ደሞ ምንም አይደብርሽም” ብላ ታሳምናታለች።[ ሴራ ፩ ]
•••
የበረራዋ ቀን እራሱ ድንገት ከምትሠራበት ቦታ አቻኩላ ጠርታ ትኬት አስቆርጣ ነው እኛ ሳንሰማ የሸኘቻት። በኋላ በስልክ ደውላ ነው “የት ጠፋች እንዳትሉ። አሁን መሄድ አለብሽ ብላኝ ጉዞ ጀምሬ ነው” ያለችን። [ ሴራ ፪ ]
•••
ሄድኩ ካለችን በኋላ ትደርሳለች ብለን ካሰብንበስ ሰዓት ጀምሮ ለ2 ቀናት ያህል ብናይ አትደውልም፣ ብናይ Online አትሆንም። ጭንቀታችን ሲበዛ ቻይና ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደወልን። ሙሉ ስሟን ከጠየቁን በኋላ ያልጠበቅነውን አስደንጋጭ ዜና አረዱን።
•••
ይዛ በመጣችው ዕቃ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ተገኝቶባት ከኤርፖርት ነው ቀጥታ ወደ እስር ቤት የተወሰደችው። በሃገሪቱ ህግ መሠረት ደግሞ ከ10 ግራም በላይ ይዞ የተገኘ ሰው የዕድሜ ልክ እስራት፣ 50 ግራም ከሆነ ደሞ የሞት ፍርድ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። እሷም አንድ ነገር ካልተደረገላት በቀር የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃት አረዱን።
•••
ወድያው የጓደኛ ተብዬዋ ስልክ ላይ ደጋግመን ስንደውል አላነሳ አለችን። በሂደት ስታነሳ የተፈጠረውን ነገር አስረድተናት የምታውቀው ነገር ካለ ስንጠይቃት፤ መጀመሪያ “በምን ልትታሰር ትችላለች?” ምናምን እያለች ካቅማማች በኋላ “እዛ ያሉ ጓደኞቼ ይሄን ነገር ብታመጪ በጣም ትርፍ አለው፣ በአንዴ ትለወጪበታለሽ ብለውኝ ከብራዚል ያመጣሁትን አንድ ዕቃ አድርሺልኝ ብዬ ሰጥቻት ነበር። በሱ ይሆናል የተያዘችው” ብላ አመነች።
•••
እኛም ያሉንን 3 የሰው ምስክሮችና በስልክ የቀዳናትን ይሄን ንግግር ይዘን ወደ ፖሊስ በመሄድ አመለከትን። በወቅቱ ልጅቷ ሀገር ውስጥ ስላልነበረች በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዛ እንድትታሰር ተደረገ። እሷም ለፖሊስ የእምነት ቃሏን ሰጥታ በዋስ ስለተፈታች የክስ ሂደቷን በተመላላሽ እየተከታተለች ነው።
★ ቻይና ስላለው ጉዳይ በተመለከተ ፦
“ ላለፉት 3 ወራት ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ የፊታችን አርብ ጉዳይዋ ለአቃቤ ሕግ ተላልፎ ክስ እንደሚመሰረትባት ተነግሮናል። አደንዛዥ ዕፁ እጇ ላይ ስለሆነ የተገኘው እና ከዚ በላይ ማስረጃም ብዙ ስለማያስፈልግ ከአንድ ግዜ በላይ ቀጠሮ ሳያበዙ ሊፈርዱባት እንደሚችሉም ሰምተናል።
•••
እናታችን ይሄንን ስትሰማ በድንጋጤ ግማሽ ሰውነቷ ፓራላይዝ ሆኖ ተቀምጣለች። እኔና ሌሎች በርታ በርታ ያልን ቤተሰቦቿ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረግን ነው።
1ኛ~ የቻይና መንግሥት እህታችንን ወደ ሀገሯ እንዲመልስልን ፒቲሽን እያሰባሰብን ነው።
2ኛ~ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መፍትሄ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው።
3ኛ~ ምናልባት በቅርቡ ደግሞ ሰልፍም አስበናል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በሚችለው ሁሉ ድጋፉን ያደርግልን ዘንድ በየዋኋ እህታችንና በበሽተኛ እናታችን ስም እንማፀናለን።
•••
#ማስታወሻ | ~ ይህቺን በማታውቀው ጉዳይ የሞት ፍርድ በመጠባበቅ ላይ የምትገኘው ምስኪን ኢትዮጵያዊት እህታችንን ናዝራዊት አበራን ማዳን ይቻል ከሆነ እኛ ምን ማድረግ እንዳለብን ሃሳብ አቅርቡና እንረባረብ።
•••
መጽሐፍም እንዲህ ይላል። “ ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥
ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ …ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥… ከዳተኞች፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤…ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።” 2ኛ ጢሞ 3፣ 1-5
ሻሎም !   ሰላም !
መጋቢት 12/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic