>
5:13 pm - Friday April 19, 8080

ባለፎጣው ሪቮልቨር!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ባለፎጣው ሪቮልቨር!!!
አሰፋ ሀይሉ
‹‹[ይህ ኃውልት] በታነፁለት ጥቂት ጠርዞችን ብቻ ተጠቅሞ፤  የሰው ልጅ፤ አሸናፊነትን ሣይሆን ሠላምን እንዲሠጠው በመሻት፤   ያቀረበውን ከሁሉ የላቀውን ፀሎቱን፤ በቀላሉ ቁጭ ያደረገ፤  ታላቅ አብነትን የሚዘክር ቅርፅ ነው!!!››  
 —  የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን
—-
ይህ — አፈሙዙ በእርጥብ ፎጣ የተዘጋ ግዙፍ ባለ ነጥብ 357 የሪቮልቨር ኮልት ሽጉጥ ኃውልት — ‹‹ Non Violence ›› የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው — ወይም በሌላ ስሙ ‹‹ The Knotted Gun ›› በመባል የሚታወቅ — እና የዛሬ 5 ዓመት ገደማ — በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ፊትለፊት እንዲቆም የተደረገ —ዝናው እጅጉን በዓለማችን የናኘ — ዓለማቀፍ ተቋማት በመዲናነት በመረጧቸውና ታላቅ የሠላም ሙዝየሞችን በሃገራቸው ባነፁ 21 የዓለማችን ሃገሮች — አርቲስቱ እየተለመነ እና ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለው እንዲያንፅ ተደርጎ የተተከለ — ዕፁብ-ድንቅ የተሰኘ እጅግ ታዋቂ የጥበብ ሥራ ነው፡፡
በቀራጺው ሃገር በስዊድን ብቻ — ይህ ግዙፍ የተዘጋ አፈሙዝ — በ12 የተለያዩ ሥፍራዎች እንዲተከል ተደርጎለታል — ስዊድናውያኑ ሥራውን እጅግ እንደወደዱት ህያው ማስረጃ ነው እንግዲህ ይሄ፡፡ ግን ስዊድናዊው አርቲስት ካርል ፍሬድሪክ ሮተርስዋርድ — ይህን ግዙፍ የተዘጋ አፈሙዝ ኃውልት ያነፀው — በንዴት ነው፡፡ እንዴት? ለምን?
በእኛ አቆጣጠር በ1977 ዓ.ም. ላይ — ይህ አርቲስት እጀጉን የሚወደው የቢትልስ የሙዚቃ ባንድ ዋነኛ አቀንቃኝ — ጆን ሌነን — በእኛ አቆጣጠር በሕዳር 29 ቀን 1973 ዓ.ም.— በኒውዮርክ ማንሃተን አድፍጦ እየተጠባበቀው በነበረ — ማርክ ዴቪድ ቻፕማን በተሰኘ ነፍሰ-ገዳይ — በጀርባው በተተኮሱበት አራት የኮልት ጥይቶች የተነሣ — ሕይወቱ ለህልፈት ተዳረገች፡፡ …
በእርግጥ በሥራዎቹ ዓለማቀፍነትን ያቀነቅን የነበረውና — ስለሠላም ዋጋ በእጅጉን ይሰብክ የነበረው ጆን ሌነን — ምንም እንኳ ስለ ሠላም ደፍሮ በመስበክ እና የአሜሪካኖችንና የአውሮፓውያንን በቬትናምና በሌሎች ሃገራት የሚያካሂዱት ጦርነት ይቃወም የነበረ ቢሆንም — ነገር ግን መቼም ሰው ነውና አንዴ ሳት ብሎት እንዲህ የሚል ቃለምልልስ ሰጠ፡-
‹‹በእኔ አመለካከት ቢትልስ የሙዚቃ ቡድን በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በርካታ ተከታዮች አሉት!›› የሚል፡፡
እንግዲህ የጆን ሌነንን ነፍስ የቀጠፋት ይህችን የጆን ሌነንን አስተያየት በሬዲዮ ሰምቶ ትክን ያለው እና — በግል ማህደሩ ቢትልሶችን ‹‹የሠይጣን ደቀመዛሙርት›› ብሎ የፃፈው ማስታወሻ ኋላ የተገኘበት — ማርክ ቻፕማን — በዚያው በ1973 ግድም ክርስትናን የተቀበለ — አዲስ አማኝ ነበር ነው የተባለው እንግዲህ — ‹‹ጀማሪ ዲያቆን ከጳጳሱ ይብሳል›› እንዲል ያገራችን ሰው!!!
እናማ — ስዊድናዊው አርቲስት ካርል ርተርስዋርድ — የእኛም ባለ 3.2 ሚሊዮን ዓመቷ እናታችን የሃዳሯ ድንቅነሽ — ‹‹ሉሲ›› ተብላ በእርሱ ዘፈን ርዕስ የተሰየመችለትን — ተወዳጁን የቢትልስ የሙዚቃ ቡድን አቀንቃኝ — የጆን ሌነንን ሞት በሰማ ሰዓት — እጅግ በንዴት ከመጨሱ የተነሳ — በቀጥታ ወደስቱዲዮው ሄደ — እና ሌነንን እና ጥይት የተፋችበትን ያችን የተረገመች ሽጉጥ እያሰበ — ያንን የሚወደውን የሠላም ሃዋርያ የጆን ሌነንን ሕልፈተ-ሕይወት እያሰበ ነበር — ‹‹ከአሁን ወዲያ የተነጣጠሩ ሽጉጦች ሁሉ ሞትን የሚተፋ አፈሙዛቸው ፈጣሪ ከድካሙ የተነሣ ፊቱን በጠረገበት ቀዝቃዛ ፎጣ ፍፁም ተዘግቶ ይቅር!›› በማለት — የተቀደሰ ምኞቱን — ከሞት ሊመልሰው ለማይችለው ተወዳጅ አቀንቃኝ — ለጆን ሌነን መታሰቢያነት ያነፀለት፡፡
ግን ግን … ይህ የአርቲስቱ ምኞት ምን ያህል ሰምሮለታል? የሚለውን ግን — ራሱ አርቲስቱም፣ ሁላችንም፣ ሁሉም የዓለም ሕዝብ ያሚያውቀው ይመስለኛል — ብቻ ዋናው ነገር — ሁሌም ያንኑ ቃል የሚናገረው — የተቀደሰ መልዕክቱ ነው እንጂ — የማያልቅ ፍቅርና ሠላምን የሚሰብኩ ቅዱሳት መጻሕፍት ከነቅዱስ መልዕክታቸው መኖራቸው ብቻ እኮ — ከዓለማችን መች መሣሪያ ያማዘዙ ጦርነቶችን አስቀረ??? እና ዋናው መልዕክቱ መሰማቱ ነው — ልቦና ያለው ትውልድ ሲመጣ — በፅሞና ያደምጠው፣ አስተውሎ ይመለከተው፣ እና ይተገብረው ዘንድ!!!
የዚህን አፈሙዙ የተደፈነ ግዙፍ ሽጉጥ ኦሪጂናል ሥራ — የኃውልቱ ቀራፂ — ካርል ፍሬድሪክ ሮተርስዋርድ — በመጀመሪያ ያስረከበው — ለሉግዘምበርግ መንግሥት ነበር፡፡ የሉግዘምበርግ መንግሥት ይህ ልሣኑ የተዘጋ ግዙፍ ሽጉጥ ለምን አስፈለገው?? ምክንያቱ — በሉግዘምበርግ ዋና መቀመጫውን ላደረገው የአውሮፓ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት — ታላቅ የሠላምና የፍቅር ኃውልት ለማቆም በመፈለጉ ነበር — የሉግዘምበርግ መንግሥት፡፡
 የሉግዘምበርግ መንግሥት ደግሞ የዲዳውን ሽጉጥ ኃውልት  — በመዲናው በታነፀው የአውሮፓ ኮሚሽን ጽ/ቤት ፊት ካቆመው በኋላ — ያየው ባጠገቡ ያለፈ ሰው ሁሉ — በዚህ ኃውልት — ግልጽ ዓላማና ለዓለም በሚያስተላልፈው ቁርጥ ያለ መልዕክት — እንዴት እንደተከየፈበት፣ የቱን ያህል እንደደመመበት ሲገነዘብ — ኃውልቱን በአርቲስቱ እጅ — በነሃስ ማዕድን በግዙፍ አስቀርፆ — በእኛ 1981 ዓ.ም. ላይ — ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሥጦታነት አበረከተው፡፡
ኃውልቱ ለዓለም ሃገራት ሁሉ ምሣሌና ዓርማ ይሆን ዘንድ ደግሞ — ከእፍኝ ዓመታት በፊት — የዓለም ሃገራት ሰንደቅ ዓላማዎች በተሰቀሉበት — ራሱ ለኃውልቱ ምክንያት የሆነው ጆን ሌነን በሽጉጥ ነፍሱን ባጣባት — እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና መቀመጫ በሆነችው በኒውዮርክ ከተማ — ለሕዝብ በግልጽ በሚታይ ሥፍራ ላይ ትይዩ ሆኖ እንዲቆም ተደርጓል፡፡
ለሁለት የኃላፊነት ዘመናት የተባበሩት መንግሥታትን በዋና ፀሐፊነት የመሩት ጋናዊው ዶክተር ኮፊ አናን በአንድ ወቅት ስለዚህ አፈሙዙ የተዘጋ ኃውልት የተናገሩትን አስታውሰን ብንሰነባበት መልካም መስሎ ታየኝ፡-
‹‹[ይህ ኃውልት] በታነፁለት ጥቂት ጠርዞችን ብቻ ተጠቅሞ፤
የሰው ልጅ፤ አሸናፊነትን ሣይሆን ሠላምን እንዲሠጠው በመሻት፤
ያቀረበውን ከሁሉ የላቀውን ፀሎቱን፤ በቀላሉ ቁጭ ያደረገ፤
ታላቅ አብነትን የሚዘክር ቅርፅ ነው፡፡››
 —  የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን
“[This sculpture represents] A powerful symbol
that encapsulates, in a few simple curves,
the greatest prayer of man: that which asks
not for victory, but for peace.”
— Former United Nations Secretary General Kofi Annan
በመጨረሻም — አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ — የጦር መሣሪያዎቻቸውን አነጣጥረው — አንደኛቸው በሌላኛቸው ቃታ እየተሳሳቡ ያሉ — በነፍጣቸው አፈሙዝ የሞትን ፅዋ እርስበእርሳቸው እየተረጫጩ ለሚገኙ — ያልታደሉ የዓለማችን የጦርነት ቀጣና ነዋሪዎች ሕዝቦች — እንዲሁም — በየሃገራቱ — ሌሎች አማራጮች ሁሉ አልገለጥ አልሣካ ብሏቸው — የማትመለሰዋን አንዲቷን የሰውን ልጅ ክቡር ነፍስ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ — እና እርስ በእርስ ለመጠፋፋት ላቆበቀቡ የዓለማችን የሰው ልጆች በሙሉ — ከነሕጻናቶቻቸው፣ ከነወጣቶቻቸው፣ ከነአዛውንቶቻቸው ጭምር — ፈጣሪ አምላክ — ጥይት የሚተፉ አፈሙዞቻቸውን ሁሉ — በሠላምና በፍቅር ይደፍንላቸው ዘንድ — ለፈጣሪ አምላካችን ፀሎታችንን ስለዓለሙ ኗሪ ሁሉ አቀረብን፡፡
አምላክ — በመላው ኢትዮጵያውያን ልቦና ሁሉ ውስጥ — የምልስነትን፣ የወገንን ፍቅር፣ የመተሳሰብን፣ የመራራትን፣ የመዋደድን፣ የእርቅን፣ የሠላምን፣ የመሸነፍን፣ የመተውን፣ የመሰጣጣትን፣ የትዕግስትን፣ የአርቆ አስተዋይነትን፣ የወደፊቱን፣ መልካም መልካሙን ሁሉ — እንዲያሰርፅብን ስንል — ለፈጣሪ አምላካችን ወደሠማይ አንጋጠን፣ ወደምድር አጎንብሰን፣ ፀሎታችንን ስለራሳችን አቀረብን፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን — እና ሕዝቦቿን ሁሉ — አብዝቶ ይባርክ፡፡ የተከፈቱ አፈሙዞቿን ሁሉ — በድካሙ ፎጣ — በማያልቅ ፍቅሩ ያጣፋላት፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ቸር ያሰማን፡፡
Filed in: Amharic