>

ሕገ መንግሥት ለአንድ ክልል ሕዝብ ተብሎ አይሻሻልም እንዴ? (ውብሸት ሙላት)

ሕገ መንግሥት ለአንድ ክልል ሕዝብ ተብሎ አይሻሻልም እንዴ?
ውብሸት ሙላት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ “ለአንድ ክልል ተብሎ ሕገ መንግሥት አይሻሻልም” በማለት የአብን ምክትል ሊቀ መንብር አቶ በለጠ ሞላ የተናገሩትን መነሻ አድርገዉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንዴት አይሻሻለም?
እስኪ ስለማሻሻያ የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ በመጀመሪያ፡፡
ስለ ሕገ መንግሥት ማሻሻል (amendment)  ጉዳይ ሲነሳ ቀምነገሩን በአጭር አነጋገር ሲቀመጥ ሕገ መንግሥት ላይ ማስተካከያ የሚደረግበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ማሻሻያ ከጥቅል  ክለሳ (Revision) ይለያል፡፡ በክለሳ ሲሆን በርካታ በርካታ አንቀጾች፣መሠረታዊ መገለጫዎች ሁሉ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ የ1948ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በ1923ቱ ሕገ መንግሥትን ያሻሻለ ሳይሆን  የከለሰ ነው፡፡
ማሻሻያ ሲባል በአብዮትም ይሁን በሌላ መንገድ ሕገ መንግሥት ከመለወጥም ይለያል፡፡ የ1948ቱ ሕገመንግሥት በአብዮት ቀሪ ከተደረገ በኋላ በ1979 የወጣው የደርግ ሕገ መንግሥት የቀድሞውን በመከለስ የወጣ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው፡፡ መንግሥታዊ አወቃቀሩ፣ ሥልጣን የሚገኝት ስልቱ፣የዜጎችና የመንግሥት ግንኙነቱ ሙሉ በመሉ ተቀይሯል፡፡ የደርግ አገዛዝ ከወደቀ በኋላም የመጣው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በቀድሞው ላይ ክለሳ በማድረግ የተገኘ ሳይሆን እንደ አዲስ የተዘጋጀ ነው፡፡
መሻሻል በአንድ የሕገ መንግሥት ሰነድ ውስጥ የሚደረግ የለውጥ እርምጃ ወይንም እድገት ነው፡፡ አብዝኃኛውን ጊዜ ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱን ቃላት፣ ሐረግ፣ ዓረፍተ ነገር ወይንም አንቀጾችን ላይ የሚደረግን መጠነኛ ለውጥ ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
ከላይ በተገለጹትን ሲሻሻሉ በምትካቸው የሚፈጸመው ነገር  በከፊል መጨመር ፣ በከፊል መቀነስ ወይንም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ሊሆን ይችላል፡፡  በእዚህ መንገድ የሚደረጉ ማናቸውም ለውጦች ከሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ባሕርይና ዓላማ፣ ግብና መንፈስ ጋር የሚቃረን መሆን የለበትም፡፡ በተቃራኒው ሲሆን ውጤቱ ከማሻሻያነት ያልፋል፡፡ ክለሳ ወይም ለውጥ ሊሆን ይችላል፡፡
ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ የማድረግ ሒደት ሕገ መንግሥቱ ሕይወት ኖሮት ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ፣በአጭር ጊዜ እንዳይሞት፣በሌላም እንዳይተካ ያደርገዋል፡፡ አንድን ሕገ መንግሥት በወቅቱ እንደ ሁኔታዎች ፍላጎት ማስተካከያና ማሻሻያ ሳያደርጉ መቆየት ወደ ክለሳና ሙሉ በሙሉ ቅያሬ ወደ ማድረጉ ማምራቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡
የ1923ቱ ሕገ መንግሥት በወቅት በወቅቱ ባለመሻሻሉ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማክተማያን ተከትሎ የመጡ ለውጦችን እንዲሁም የኤርትራን በፌደሬሽን ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀልን ተከትሎ በአገሪቱ የተፈጠረው ሁኔታ ማስተናገድ ስላልቻለ በ1948 ተከለሰ፡፡ ከዚያም፣ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው በፍጥነት ሲቀያየር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ባለበት ተቸንክሮ ቆሞቀር በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ፡፡
 የ1966ቱ ተጨናግፎ የቀረው ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ የ1948ቱን እንዲተካ የታሰበው እጅግ ዘግይቶ የመጣ ስለነበር መጽደቅ እንኳን ሳይችል ቀረ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም በአዋጅ ወይም በይፋ ተሻሻሎ አያውቅም፡፡ “በምስጢር” ግን ሁለት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡
በመሆኑም አንድን ሕገ መንግሥት እንደ ሁኔታው በወቅት በወቅቱ ማሻሻል ተገቢ ነው፡፡ በክለሳም በለውጥም ሕገ መንግሥት ሲለወጥ የአገር አስተዳደርና ተቋማት ከእንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀርን ስለሚያስከትል ብዙ የሥርዓት መናወጦችን ያመጣል፡፡ የተናወጡትን ሥርዓቶች እንደ አዲስ በማዋቀር እና በማቋቋም የአገር ውድ ሐብት፣ጊዜ ወዘተ ይባክናል፡፡
ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ምክንያት የሚሆነው ጊዜ በሔደና ነገሮች በተቀየሩ ቁጥር ሁለንተናዊ በሚባል መልኩ የዕድገት ደረጃ ስለሚቀየር ነው፡፡  ሁኔታዎች ሲቀየሩ፣ችግሮች ሲከሰቱ እነሱን ተከትሎ ካልተሻሻለ ሕገ መንግሥቱ ጊዜው የሚዋጀውን አልሆነም ማለት ነው፡፡
ስለዚህ፣የትኛውም ዓይነት ሕግም ይሁን ሕገ መንግሥት አብረው ከኅብረተሰብ ዕድገትና ፍላጎት ጋር በመሳነት ማደግና መሻሻል ይገባቸዋል፡፡  እናም፣ ሕገ መንግሥት ዘላቂነት ኖሮት ገዢ፣ ኅልው እና ቅቡልነት ኖሮት ይቀጥል ዘንድ መሻሻል የግድ ይሆንበታል፡፡
ሕገ መንግሥቱ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሒደትን በሁለት ከፍሎ የሚያይ ሲሆን፤ አንደኛው የሕገ መንግሥት መሻሻል በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ከተዘረዘሩት መብቶች እና ነፃነቶች እንዲሁም ከአንቀጽ 104 ውጭ ያሉት የሚሻሻሉበት ሥርዓት ነው። ሕገ መንግሥቱን አንድ ክልል ወይም የፌደሬሽን ምክር ቤት ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻዉን አያሻሽለዉም፡፡ ብቻቸዉን አያሻሽሉትም ማለት ግን አንድ ክልልን የሚጎዳ፣ ችግር ቢኖርት ለአንድ ክልል ተብሎ አይሻሻልም አይባልም፡፡
ለነገሩ የአማራ ክልል ሕዝብ ወይም የአማራ፣አገዉና ቅማንት ሕዝብ በአንድነት ቢለኩ ስንቱን በቁጥር ክልል ያጣጥፏቸዋል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋማቤላ፣የሐረሪ እና የአፋር ሕዝብ በድምሩ የደቡብ ወሎ ሕዝብን አያክሉም፡፡ የሶማሌ.የትግራይ፣የአፋር፣የሐረሪ፣ የጋምቤላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦችን ይበልጣል፡፡
 በመሆኑም፣ ለአንድ ክልል ሕዝብ ተብሎ ሕገ መንግሥት አይሻሻልም እንዴትስ ይባላል ለማሰብም ከባድ ነዉ፡፡ ደግሞ እኮ ሕጉ መንግሥቱ ብዙ ዘባተሎ አንቀጾች የታጨቀበት ነዉ፡፡ ከመግቢያዉ ጀምሮ የአማራን ሕዝብ የሚያጥላላ፡፡ ቃለ ጉባኤዎቹን ላነበበማ የአማራ ሕዝብ  ለአርባ ቀናት ያህል በኦፊሴል የተሰደበበት ዶሴ ነዉ፡፡ እናም ይሄንን ነዉ ለአንድ ክልል ሕዝብ ተብሎ ሕገ መንግሥት አይሻሻልም የተባለዉ፡፡
በነገራችን ላይ ለአንድ ክልል ተብሎ ሕገ መንግሥት አይሻሻልም ሲባል ያጨበጨቡት ፓርቲዎች ለአማራ ሕዝብ ያላቸዉን ጥላቻ ነዉ የገለጹት፡፡ መቼም እኮ አያፍሩም ለአማራ ሕዝብ ሲባል ሕገ መንግሥት አይሻሻልም ሲባል አጨብጭበዉ “የአማራን ሕዝብ ጥቅም እናስጠብቃለን” ይሉ ይሆናል፡፡
የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎ አቻምየለህ ታምሩ በገጹ ይህን ብሏል:-
 
በሉ  እናንተም  እንግዲህ ለመርሀችሁ ተገዢ ሁኑ. . . 
 
ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው እለት Belete Molla Getahun ላቀረበው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ «የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሚሻሻለው  የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት ለመመለስ እንጂ  የእናንተን  ክልል ወይንም የናንተን ብሔር ፍላጎት ለማሳካት አይሻሻልም» ብሏል። ጥሩ ነው።  ጥላሁን ገሰሰ «አመልካች ጣት»  በሚለው ዘፈኑ፤
 
ባንዷ ስትጠቁም ከጣቶችህ መሀል፣
ሶስቱ ግን ራስህን ይመለከቱሀል፤ ይላል።
 
እንግዲህ!  ዐቢይ አሕመድ  ወደ በለጠ ሞላ  እያመላከተ  «የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሚሻሻለው  የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት ለመመለስ እንጂ  የእናንተን  ክልል ወይንም የናንተን ብሔር ፍላጎት ለማሳካት አይሻሻልም» ባለው መርህ መሰረት የኦሮሞ ብሔር ወይንም ኦሮምያ የሚባለው  ክልል እያቀረበው ያለውን  ኦሮምኛን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ   የአንድ ብሔር ወይንም የአንድ ክልል ጥያቄ ስለሆነ የኦሮሞ ብሔርን ወይንም ኦሮምያ የሚባለው ክልል  ፍላጎት ለማሳካት ሲባል ኦሮምኛን የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አይደረግም፤ ኦሮምኛም የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ አይሆንም ማለት ነው። 
 
እኛም  ወደፊት የኦሮሞን ብሔር ወይንም ኦሮምያ የሚባለውን  ክልል  ፍላጎት ለማሳካት ሲባል ኦሮምኛ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ይሁን ተብሎ ሲጠየቅ  ለሚጠይቁን የኦሮሞ ብሔርተኞች ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የነገረንን  መርህ መዘን የእናንተን ክልል ወይንም የናንተን ብሔር ፍላጎት ለማሳካት ሲባል  ኦሮምኛ የፌዴራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ ሊሆን አይችልም፤ ሕገ መንግሥቱም ኦሮምኛን የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ሲባል አይሻሻልም ብለን በመርሀችሁ እናስራችኋለን! አበቃ!
Filed in: Amharic