>

ጽንፈኛ አስተሳሰብና አደረጃጀት በተፈጥሮው ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ፈትሃዊ ነው (ቾምቤ ተሾመ)

ጽንፈኛ አስተሳሰብና አደረጃጀት በተፈጥሮው ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ፈትሃዊ ነው

ቾምቤ ተሾመ

የወያኔና የኦሮሞ የዘር አቀንቃኞች የበላይነት አግኝተው በዘር እየጠረቡ በክልል አጥር ስር ወርውረው ነጻነት አመጣንላቸሁ ብለው መስበክ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ለሃያ ሰባት አመታት ሳይታክቱ የሰሩበት አላማ የኢትዮጵያ ህዝቦች የቅርብ እሩቆች እንድንሆን ፤እርስ በራሳችን የምንጠራጠር ብቻ ሳንሆን የምንፈራራ፤አንዳችን ከሌላችን ደህና ጥሩ ነገር የማንጠብቅ ብቻ ሳንሆን አንዳችን ሌላችን ላይ ደባ ስንቀምር እንደማንተኛ ጠላቶች አይን ለአይን እንዳንተያይ አድርገውናል፡፡ እነዚህ ጽንፈኞች የሰው ዘር ግንድ ካንድ ስር ተመዞ ወጥቶ ማየት ካልቻሉ ሰውን እንደተበላሸ እቃ እስከማየት የደረሱ ስብእናቸው ተሟጦ ያለቀ የሰው ቅርጽ የያዙ ስብእናቸው በጥላቻ ነቀዝ ተቦጥብጦ ያለቀ ባዷቸውን የሚጓዙ ቀፎዎች ናቸው፡፡

ከራሳቸው አንድ ሰው ሲጎዳ ደረት እንደሚመቱት ያህል ከነርሱ ክልል ውጭ ያለ ሰው በእነርሱ ክልል ጉልበተኛ ሲጠቃ ያ ሰው ስቃዮ እንደሚገባው ሊያሳምኑ የሚሄዱበት እርቀት ምን ያህል አምላክ የሰጣቸውን ሰእብና አራግፈው ጥለው የአጋንንት መንፈስ የተላበሱ መሆናቸውን ነው ፡፡ ሁለት ምሳሌ ስለነዚህ ሰዎች ቀፎ ተፈጥሮ ለመጥቀስ ያህል እንይ፤ በዘር መከፋፈልን እንደ ቀዶ ጥገና የተካነው መለስ አንዴ በፓርላማ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ቤተሰቦች መፈናቀልና ያሉበትን ሰቆቃ በተመለከተ ለተነሳው ዘገባ መልስ ሲሰጥ ” ሄደው ሌላ ቦታ መንደር መመስረታችው ምንም ችግር የለውም ነገር ግን ዞፍ እየቆረጡ Environmental destruction ማምጣታቸው ብቻ ነው ለዚህ መፈናቀልና ሰቆቃ የዳረጋቸው ብሎ ነበር የተመጻደቀው; ይህንን አይነቱን ሰው ነው የሰው ቅርጽ ያለው የስብእነት ቀፎ ተብሎ በአግባቡ የሚጠራው ፡፡

በወቅቱ ወያኔ በሰራው አጥር ውስጥ ተደላድለው በወያኔ አድሏዊ አገዛዝ የተመቻቸው የወያኔ ደጋፊዎች በመለሰ “እረቂቅ” መልስ ተደንቀው ጣታቸው እስኪላጥ ነበር ያጨበጨቡለት፡፡ እነዚሁ ሰዎች አሁን ወያኔ በልዩ መልክ አደራጅቶ ሌላውን ክልል ለመቆጣጠር ያስቀመጣቸው የራሱ ሰዎች ላይ ሰው በቁጣ ሲነሳ የዘር ጥፋት ተካሄደብን ብለው ይጮሃሉ፡፡ ጉሰኝነት የራሱን እንጂ የሌላው ቁስልና ህመም አይሰማውም፤ እንደውም ጎጠኞች ስሌላው ቁስሉ ተገቢነት ሲደሰኩሩ ለጆሮ ቢሰቀጥጥም መስማት የተለመደ ነበር አሁን ደግሞ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ስልጣን ከበፊቱ ጎሰኛ ወደ አዲሱ ጉሰኞች ቤት ሲገባ ደግሞ የጎሰኛው ቋንቋና ባህል ይለያይ እንጂ ተግባሩና አስተሳሰቡ አንድ እንደሆነ የለጋጮፎዋ የሴት ከንቲባ በተግባር አሳይታናለች፡፡ ምንም እንኳን የለጋጮፎ ነዋሪውች በዚያ አካባቢ ከ10 አመት በላይ ቢኖሩም ፤ ለሚኖሩበት ቤት በየአመቱ የአፈር ግብር ክፈሉ እየተባሉ ቢከፍሉም ፤በከተማው አስተዳደር መብራትና የዉሀ ማስገቢያ ፍቃድ ተስጥቷቸው ቢስገቡም፤ ከእነዚህ ሰፋሪዎች አስተዳዳሪዎቹ ጉቦ ወስደው በራሳቸው ፍቃድ ቢያሰፍሯቸውም ፤ የዘረኝነት ዛራቸው ሲነሳ ግን የነዋሪዎቹ ማንነት ከሌላ ጎሳ አጥር/ ክልል የመጡ ስለሆነ በለጋጮፎ ከንቲባ አመለካከት የደረሰባችው ማንኛውም ኢሰባዊ ድርጊት የሚገባቸው ነው ብላ እንደምታስብ ነበር በግልጽ ያሳየችን ፡፡ ከሌላው ጎሳ አጥር/ክልል ያሉ ሰዎች ስለሆኑ የነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ ፤ሰቆቃ፤ በሙሉ የሚገባቸው ነው ብላ ስለወሰነች ነው ከምሽቱ 10 ሰአት ላይ ቦልዶዘር ልኮ ህጻናት ፤ ሸማግሌዎች፤ አራስ እናቶች ላይ ማፍረሱ ምንም አይነት ስሜትን የሚቆነጥጥ ተግባር ሆኖ ያላገኝችው ፡፡

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያዊያን ሴቶች እንዲህ አይነት ጭካኔን መስማት ጭራሽ ባይገመትም፤ ከንቲባዋም እርሷ ክልል ውስጥ ላሉት ሴቶች ፤ህጻናት ፤ አዛውንቶች አሁንም ቢሆን የምትንሰፋሰፍላቸው ቢሆኑም እነኝህ ከሌላ ክልል እርሷ አጥር ስር የወደቁ የሌላ ክልል ሰዎች ግን ስብአዊ ክብር ያላቸው ሰዎች አይደሉም ፤ ቤቱም እራሳቸው ላይ መናዱ የጎሳ ፖለቲካ እንዳሰከረው መለሰ ከአርንጓዴው የከተማው ልማት አንጻር ሲተያይ የሰዎቹ ለቅሶ ምኗም እንዳልነበረ ከፊቷ ላይ ከምታሳየው ንቀት ማንበብ ቀላል ነበረ ፡፡ አይምሮዋ በጥላቻ ስለተናወጠ ሜዳ ላይ የተዘሩትን ህጻናት እንኳን አይታ ከቤት የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን እንኳን እውቅና መስጠት አልፈለገችም “ እንዳለቸው የፈረሰም የተፈናቀለም ሰው የለም ብላ ነው የጋዜጣ መግለጫ የሰጠቸው ምንም እንኳን የፈረሱት ቤቶች በካሜራው ውስጥ ከበስተጀርባዋ ቢታይም፡፡ ጥላቻ ልቧን አውልቆ ቀፎ ያደርጋል አንድ እንስት ነች፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ የጎሳኝነትና የጥላቻ ፋብሪካ የሆነው የኦሚን ጋዜጠኛ ከሰው መብት ከሚከበርበት የተባበሩት አሜሪካ ተመልሶ አዲስ አባባ ከትሞ የሰውን ስቆቃ እየተመለከተ ህሊናውን ሳይጎነፍጠው “ ለምንድነው ጫጫታው እንዲህ የበዛው?” የሚል ጥያቄ ለከንቲባዎ ሲያቀረበላት ነው ፤ እርሱም ካሜሪካ የኑሮ ልምዱ ትምህርት ሳይወስድና ከክልሉ አሻግሮ ማየት ስላልቻለ ፤ የሁለት ቀን ህጻን ይዞ ለጅብ የተጣለቸው የእናት ለቅሶ ሳይሆን ጆሮውን የወጋው ፤ ከሌላ “ክልል “ያለ ሰዎች የተገፈተረችውን የእናት ጩህቷን አስተጋቡላት ቡሎ ነብር የከነከነው፡፡ ምንም እንኳን የኖረበት አሜሪካ እንኳን ሰው ላይ እንስሳ ላይ ጭካኔ አሳየህ ተብሎ ሰው ፍርድ ቤት እንደሚቆም በእርግጥ ቢያውቅም፡፡ጋዜጠኛውም ሆነ ከንቲባዋ የከነከናቸው ተጣለች ብለው የሚጮሁት ሰዎች ማንነት ነው የከነከናቸው በግፍ የተጎዳቸው እናት ሳትሆን ሌላ ቀፎን ተሽከሞ የሚዞር ሰውነት፡፡ እነዝህ ሰዎች መጽሃፈ ቁልቁላ ወይም ቁራን የዞረበት ቦታ ያለፉ አይደሉም እንኳን ሊያነቡት፡፡ ከተማ ሲያድግ ሰዎች የሚኖርበትን ቦታ እንዲለቁ ይገደዳሉ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሰዎችን በቂ ጊዜ ስጥተው አሳውቀው ፤ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ነው ፤ ሰው አለቅም ቢል እንኳን የከተማው አስተዳደር ስዎችን ፍርድ ቤት ወስዶ ፍርድ ቤቱ ነው እርምጃው እንዲወሰድ የሚያደርገው፡፡ ወቃ ወይም እግዚያብሄር በራሱ አምሳል የፈጠረውን ሰው እንደ እቃ መወርወር በእግዚያብሄርም ወይም በሰው ዘንድ ከፍርድ አያድንም፡፡

ከላይ ያየነው በግልጽ የጽንፈኝነት ድንቁርና ዝቅጠት ወሰን እንደሌለው ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ይህንን ፖለቲካ እነጀዋር በኦምን ቀን ሲገባና ሲወጣ በተቀነባበረ መልኩ በከተሜ አነጋገር እያጦዙት ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር ላይ የጥላቻ ዘመቻቸውን በድብቅ ሳይሆን በግልጽ አዲስ አባባ ላይ ተቀምጠው ቢንዚን እያርከፈከፉ በጥላቻ መሬቱን እያራሱት ይገኛሉ፡፡ እነ አብይና ለማላም ላይ ጸረ ኦሮሞ ናችሁ እያሉ ትልቅ ዘመቻ ሲያኪያሂዱባቸው ስለከረሙ አብይም ለማም እየፈሩ የመጡ ይመስላሉ ሰሞኑን የሚታየው የኦዲፒ መግለጫም ቀውስ ጫሪና ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን የዘጠኝ ወር በፊት የተወገደውን የወያኔ የኮረፋ ሽታ ይዞ የመጣ መግለጫና እርምጃ ነው ፡፡አብይና ለማ በጣም የሚደነቁ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ነገር ግን የኢትዮያዊው በቅጡ ተደራጅቶ ጥንካሪውን ማሳየትና አብሯቸው መቆም ስላልቻለ ለጽንፈኞቹ ተጽእኖ ሽብረክ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊው የሚፈልጉንት ያህል የመፈናፈኛ የፖለቲካ ቦታ መስጠቱ የዲሞክራሲያዊ ግንባታው እንዳይስተጓጎል ቢሆንም፤ ነገር ግን ቀንደኛ ጸረ ኢትዮጵያ አንድነት የሆኑትን እንደነ ዶ/ር ሊበን ዋኮ ያሉ ጽንፈኝች ትልልቅ የፖለቲካ ስልጣን እየሰጡ እመኑን ማለት አውቆ የተደረገ የፖለቲካ አይን አውጣነት ወይም ደግሞ ፤ሳያውቁ ከተደረገ ደግሞ የፖለቲካ እንዝህላልነት ነው (https://w.youtube.com/watch?v=jyKW2_FmIxo) ለኦሮሞ ነጻነት የኢትዮጵያ መበታተን ዋስትና ነው ሲሊ የነበረ ጽንፈኛው ዶ/ር ሊበን ዋኮ በኤል ቲቪ ላይ እንደ ኦዲፓ ቃላ አቀባይ ቀርቦ እንኳን አንድ ህንጻ አንድ ዞፍ ኦሮሚያ መትከል አትችሉም ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ማየት ችለናል ፡፡ ይህ በግልጽ ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለን በግልጽ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ሆኖም ግን ትልቁን ሸክም መሸከምና መቋቋም ያለብን እኝው ኢትዮጵያዊያን ነን ፤ዝማሬና ተግባር በየቅሉ ስለሆኑ ፡፡ ጎሰኝቹ በተገባር ከበለጡን እንደሚያሽንፉን መጠራጠር ሞኝነትም ብቻ ስይሆን የዲሞክራሲ መንገዱ የሚፈለገውን መስዋእትነት ከፍለን ለውጡ መስመር እንዲይዝ ካላደረን ስህተታችንን ለማረም ጊዜ ወደማይሰጥ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የሚዘፍቀን ፡፡

ግንቦት 7 እንዲሁም ሌሎች የፖለቲ ድርጅቶችና ሌሎች ኢትዮጵያውነትን መሰረት አድርገው የተደራጁ የብሄራዊ ፓርቲዎች እንደዚህ አይነት የመብት ጥሰትና የህዝብ አንድነትን የሚሸረሽሩ መግለጫዎች ሲወጡ ዝም ብለው ማየት የለባቸው፣ አቋም መውሰድና መግለጫ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ህዝቡንም በበለጠ ማደራጀትና ለመብቱ እንዲታገል የማድረግ ግዴታም አለባቸው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች እነጀዋር ቢላቸውን ሲስሉ እያዩ ሀሳቧን እንደጣለች የጨፌ በግ ሳር እየጋጡ አለም ለምኔ ብሎ ዘንጋ ማለት የማይገባ ሃላፊነት የጎደለው ስራ ነው የሚሆነው፡፡ እነጀዋር ፤ እነጸጋዬ አራርሳ መሬቱን ቤንዝን እያርከፈከፉ አርስውታል ስለዚህ እሳቱ ሳይጫር ቀድሞ አለመገኝት የዋህነት ሳይሆን የነርሱን እርኩሳዊ ሀሳብ ተግባር እንዲውል እንደመተባበር ነው የሚቆጠረው፡፡ እነጀዋርና እነ ጸጋዬ አራርሳ የወጠኑት ሴራ እንደዝናብ ያልፋል ብሎ መጠበቅም ትልቅ ስህተት ነው ፡፡ ህብረተሰቡ እራሱን ለመከላከል ከተደራጀ ብቻ ነው ሰላም የሚረጋገጠው ፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ኢትዮጵያዊው የዶ/ር አብይና ለማ መገርሳ ጥሩ ቃላት ይዞው የተኙ ይመስላሉ፡፡ ሁለቱ ቅን የኢትዮጵያ መሪዎች እነርሱ ቆይተው ኢትዮጵያን የተሻለ ቦታ ቢያደርሷት ትልቅ ደስታችን ነው ድጋፋችንም ሳንቆጥብ እንሰጣለን ፤ ነገር ግን ዲሞክራሲ ፍትህ እንዲሁም እኩልነት እንዲነግሱ ገና ብዙ መወጣትና መወረድ ያለበት ተራራና ቁልቁለቶች መኖራቸውን አውቆ ዝግጁ ሆኖ መገኝት ብቻ ነው ያንን እውነታን የሚያረጋግጠው ፡፡

አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ቢኖር ጥላቻ ያነገቡ የእኩይ ስራቸውን ለማሳካት እንደማይተኙ ነው፡ ቅን ልብ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚመክረው “ ልብህ እንደ እርግብ ደግ ይሁን ጥንቃቄህ ደግሞ እንደ እባብ “ የሚለውን መርሳት የለበትም;፡፡ ዲሞክራሲ ፤ፍትህ ፤እኩልነት በነጻ የሚታደሉ ስጦታዎች አይደሉም ያላቋረጠ ንቁ ተሳትፎን ይጠይቃሉ ፤ እነዚህን ከሁሉም በላይ እጹብ ድንቅ የሆኑ የሰውን ኑሩ ትርጉም የሚስጡ ሀሳቦች ያለመሰዋእትነት የሚበቅሉ አትክልቶችም አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊያን እስካሁንም የተሰውት አንዱን ዘረኛነትን አቀንቃኝ በሌላ አዲስ አቀንቃኝ ለመተካት አይደለም ፡፡ ለዚህ መፍትሄው ዲሞክራሲያዊ በሆነና ግልጽነት ባለበት መንገድ መደራጀት መደራጀት አሁንም መደራጀት ነው ፡፡ ይህም ሲሆን ብቻ ነው ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመመስረት ቀንና ለሊት የሚጥሩትን መሪዎቻችንን በተግባር መርዳት የምንችለው፡፡ ይኛን ድርሻ ሳንወጣ ከነርሱ ብቻ መጠበቅ እነርሱንም ያደክማል እንደ ሰውም ጥረታቸውን የማንቆጥራላቸው ስለሚመስላቸው ተስፋ መቁረጥንም ሊያመጣ ይችላል፡፡ ዲሞክራሲ ካለህዝብ ተሳትፎ ህይወት የለውም፡፡

Filed in: Amharic