>

"ደመቀ ያቺን ሰአት!!!" (ያሬድ ጥበቡ)

“ደመቀ ያቺን ሰአት!!!”
ያሬድ ጥበቡ
ከሌሊቱ አስር ሰአት (4:00 ኤ ኤም) ላይ የቲም ለማ ድራማ አላስተኛ ብሎ ቀስቅሶ ያናዘዘኝ “ተውኔት” ነው። ባለፈው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር የፃፍኩት አቶ መለስ ማረፋቸውን የሰማሁ ሌሊት ነበር። ልክ ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ “ጴጥሮስ ያቺን ሰአት”ን በንዴት እንደፃፈው።
—-
አቶ ደመቀ በቢሮ መስኮታቸው ጋ ቆመው በሞባይላቸው ያወራሉ። አሻግረዉ ወደ ፓርላማው ህንፃ እያዩ ነው። ከሥራቸው ባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈትቤት ዋና መግቢያ በኩል ሦስት ነጫጭ ቶዮታ ላንድ ክሩዘሮችና አጃቢዎቻቸው እየወረዱ ወደ ዶክተር አቢይ ቢሮ አመሩ። በመገረም በስልክ ጫፍ ለሚያነጋገሩት ሰው “ዛሬ ስብሰባ አለ እንዴ? ተጠርተሃል ወይ?” ብለው ጠየቋቸው።
ገዱ፣ “መጠራት ካቆምን ወራት ያስቆጠረ መስሎኝ፣ ግን ለምን ጠየቅከኝ?”
ደመቀ፣ “ሙፍሪያት፣ ለማና ወርቅነህ ተከታትለው ሲገቡ ስላየሁዋቸው”
ገዱ፣ “ይጠሩህ ይሆናል፣ ካልጠሩህም ከአንድ ግማሽ ሰአት በኋላ እንደማያውቅ ሆነህ አቢይን ለጉዳይ እንደምትፈልገው ሆነህ ሂድ እስቲ ጉዳቸውን እየው”
ደመቀ፣ “ቤት ልጆቼን ካየሁዋቸው ሰነበትኩ፣ ትንሿ ደውላ ‘ባቢ መቼ ነው እራት አብረን የምንበላው?” ስትለኝ አንጀቴ ስለተንሰፈሰፈ “ዛሬ ማታ” ብዬ ቃል ገብቼላታለሁ።
ገዱ፣ “የዛሬን ማሪኝ ብለህ ደውልላትና የቲም ለማን ጉድ ሄደህ ተጋፈጥ”
ደመቀ፣”የልጄን ተስፋ ገድዬ፣ እዚያ ስደርስ ደግሞ “ይህ የኦዴፓ ስብሰባ ነው መግባት አትችልም” ቢሉኝስ?
ገዱ፣ “ከመቼ ወዲህ ነው ሙፍሪያት ኦዴፓ የሆነችው” ብለህ አፋጣቸዋ!
ደመቀ፣ “እንጃ፣ ብቻ ከሁለት ያጣ ጎመን እንዳልሆን ፈርቻለሁ። ይህ እኮ የመጀመሪያቸው አይደለም እኔና አንተን አግለለው ሲሰበሰቡ”
ገዱ፣ “አይዞህ፣ ወሎ መጀን ኢትዮጵያንም አንተንም አይጥላችሁም፣ በል የስብሰባ ሰአቴ ደረሰብኝ፣ ደህና አምሽ፣ ወደቤት ስትሄድ ከሊመዝንህ ውስጥ በዚያኛው መስመር ደውልልኝ”
ደመቀ፣ “አንተ እብድ ይሰሙሃል እኮ፣ ከሰንሰለቱ የሚያመልጥ የለም፣ ታውቅ የለም እንዴ?”
ገዱ፣ “እሺ፣ እንግዲያውስ በዋትስአፕ ደውልልኝ”
ደመቀ፣ “እሺ”።
 አቶ ደመቀ ስልኩን ከዘጉ በኋላ በሃሳብ ርቀው ሄዱ ። የልጆቻቸው ምስሎች በራሳቸውና ባሻገር በሚታያቸው በፓርላማ ህንፃው መሃል ባለው ሰማይ ላይ እየታያቸው ነው “ለእናንተ ስል ስንት ከፈልኩ፣ ያውም ላትረዱልኝ” ብለው ሳያስቡት የእንባ ዘለላ ከዓይኖቻቸው መውረድ ጀመሩ። በቀኝ አይበሉባቸው ዓይኖቻቸውን እየጠራረጉ “ዓመት እንኳ ሳይሞላን፣ ተመልሰን እንዴት ሌላ ሃፍረት ውስጥ እንዘፈቃለን፣ ያ ሁሉ ተስፋውን የጣለብንን ህዝብ ዓይን እንዴት ብለን ነው የምናየው? አሁንስ የቴዎድሮስ  አረር ናፈቀኝ። የተረገመች ሃገር፣ እሷም ላያልፍላት እኛንም አደከመችን። አሁን ማን ነው እኮ  የሚቆጥርልን፣ ሃገሬው የሚያየው፣ ውድ ሱፍ ልብሳችንን እንጂ፣ ሃገሬው የሚያየው ጥቁር ካዲላኮቻችንን እንጂ፣ መች የህሊና ፀፀታችንን ነው፣ መች እንቅልፍ አጥተን ያደርንባቸውን ሌሊቶች ነው!” በማለት ድንገት ከጠለቁበት የሃሳብ ባህር ሲወጡ ፀሃይ ጠልቃ አካባቢያቸው ሁሉ በጨለማ ተውጦ አገኙት። “ይህንማ መፍቀድ የለብኝም፣ በህዝቡ ዘንድ የቲም ለማ አባል ተደርጌ እየተነገረ፣ እኔን ያገለለ ስብሰባ አፍንጫዬ ስር ሲደረግ መፍቀድ የለብኝም” ብለው ከራሳቸው ጋር እየተመናጨቁ ወደ ዶክተር አቢይ ቢሮ አመሩ።
ከበሩ ሲደርሱ ሙሉ ሬንጀር የማእረግ ልብስ የለበሱ ወታደሮች አስቆሙዋቸውና “ዛሬ፣ ጠበቅ ያለ ጥበቃ ላይ ነን፣ ያለፈቃድ መግባት አይቻለም” ይላቸዋል አንደኛው ከሁሉም ወጣት የሆነውና የአጋሮ ልጅ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው ከዚህ በፊት ነግሯቸው የነበረው የሪፐብሊካን ጋርድ አባል።
ደመቀ፣ “ሂድና አለቃህን ደመቀ በአስቸኳይ ይፈልግሃል በለው፣ መልሱን እዚሁ ቆሜ እጠብቃለሁ” ብለው አቶ ደመቀ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መግቢያ ላይ ካለው ኮሪደር ውስጥ በሃሳብ እየተወዘወዙ የዶክተር አቢይን መልስ ይጠባበቁ ጀመር ። ከመልሱ ይልቅ ራሰቸው ዶክተር አቢይ መጥተው፣
አቢይ፣ “ደሜ እስካሁን ቢሮህ አለህ እንዴ፣ ቤትህ  የሄድክ እኮ መስሎኝ ነበር፣ ከልጆችህ ጋ እራት የመብላት እቅድ እንደነበረህ ስለማውቅ እኮ ነው እነለማ ድንገት ሲመጡ ያላስጠራሁህ”
ደመቀ፣ “ከልጆቼ ጋር እራት እንዳለኝ በምን አወቅክ፣ ከነጋ አልተገናኘን፣ ወይ አልተደዋወልን?”
አቢይ፣ ” ያንተ ነገር፣ ከኢንሳ የሚያመልጥ ምን ነገር አለ ብለህ ነው፣ ያው የስልክህን ትራንስክሪፕት አይቼ ነዋ”
ደመቀ፣ “አንተ ሰው አብደሃል፣ ስንት ሥራ ተቆልሎብህ አንተ ማ ከማን ጋር ምን አወራ የሚል የኢንሳ ተራ መዘርዝር (ሪፖርት) ታነባለህ?
አቢይ፣ “አንተ ደግሞ ነገር አታካብድ፣ ባጋጣሚ እንጂ ሆን ብዬ፣ የደመቀንና የልጆቹን የስልክ ውይይት ስጡኝ ብዬ ጠይቄ እኮ አይደለም ።”
ደመቀ፣ “ቢሆንም፣ የኢንሳ አሠራርን ከለውጡ አኳያ ለማረም በተነጋገርነው መሠረት ሥራነክ ያልሆኑ የግል ጉዳዮች ሪፖርት እንዳይደረጉ እኮ ተስማምተን ነበር፣ ቢያቀርቡልህ እንኳ አንተ ማየት አልነበረብህም፣ ፈረንጆቹ ፕራይቬሲ የሚሉት እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ይመስለኛል።
አቢይ፣ “እነለማ እዚህ ናቸው፣ ባለፈው ጊዜ የተመድን ዋና ፀሃፊ አናግሬው ነበር ለወርቅነህ ሥራ እንዲፈልግለት፣ አሁን የናይሮቢ ቢሮ ሃላፊ አድርጎ ሊሾመው መወሰኑን ነግሮኝ የደስደስ ሻምፓኝ ለመጠጣት ተሰብስበን እኮ ነው”
ደመቀ፣ “ምድረ ጴንጤ ሁላ! ከመቼ ወዲህ ነው ሻምፓኝ መጠጣት የጀመራችሁት? ለአንዱ ነቢያችሁ ነው የምነግርላችሁ፣ ፀሎት እንዲያደርግላችሁ”
አቢይ፣ “እኛ እኮ አልኮል የሌለው ከአፕል የሚሠራ ልዩ ሻምፓኝ አለን፣ ፋራ አትሁን!”
ተያይዘው ወደ ዶክተር አቢይ ቢሮ ገቡ።
የፅህፈትቤቱ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ከአረብ ኤሚሬትስ የመጣው የተንደላቀቀ ሶፋ ላይ ለማ፣ ሙፍሪያትና ወርቅነህ ሻምፓኛቸውን ይዘው ቁጭ ብለዋል። ሙፍሪያትና ወርቅነህ ሲነሱ ለማ በተቀመጠበት “ሃይ ደመቀ” በማለት ሰላምታ ሰጠ።
ደመቀ ወደ ወርቅነህ እያየ ፣ “የሹመትህን ዜና ገና አሁን አቢይ እኮ ነው በሩ ላይ የነገረኝ፣ እንኳን ደስ አለህ ነው የሚባለው?” አለ ግራ በመጋባት ስሜት።
ወርቅነህ፣ “እንዴታ፣ ትጠራጠራለህ እንዴ ሹመት መሆኑን፣ ትልቅ ሹመት ነው እንጂ፣ የተባበሩት መንግስታት ሥራ እኮ ነው!”
ደመቀ፣ ” የአንድ ሃገር ያውም ኢትዮጵያን የሚያህል ሃገር ውጪጉዳይ ሚኒስትር የነበረ ሰው የአንዲት መናኛ የተመድ ቢሮ ሃላፊ ሲደረግ ሹመት ነው ብሎ ለመቀበል ከበድ የሚል አይመስልህም?”
ለማ፣ “እናንተ አዴፓዎች እኮ ነገር ቶሎ አይገባችሁም። ወርቅነህ ቲም ለማ ውስጥ በመቆየቱ “ፍትህ የፖለቲካ መሳሪያ ተደረገ፣ የተደመሩ ነፃ ሆነው ያልተደመሩ በፍትህ ሰይፍ የሚቀሉበት ሥርአት ነው በማለት ከወያኔም አልፎ የማህበራዊ ሚዲያው ትችት በመሆን ላይ ነው። ያንን ክስ ለማስቆም አቢይ የፈጠረው መላ ነው።
ደመቀ፣ “ታዲያ የተመድ ሠራተኛ መሆን ከኢትዮጵያ ክስ ያስጥላል እንዴ? ስሌታችሁ አልገባኝም”
አቢይ፣ “ምን አዲስ ነገር አለው ወደኋላ እንጂ ወደፊት ማየት የማንችል ህዝብ እኮ ነን!”
ደመቀ፣ “ምን ሆነሃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግግሮችህ ውስጥ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያ የሚል አነጋገር ማዘውተር ጀምረሃል፣ ከየት የመጣ ነው?”
አቢይ፣ “ማመስገን የማይችል ህዝብ ስለሆነ ነዋ፣ ዘመዶችህን እስቲ እያቸው “አላህአምዱሊላ” ሲሉ ሰምተሃቸው ታውቃለህ?”
ደመቀ፣ “ያውም በቀን አስር ጊዜ ነዋ! ከጃዋር ጋር መዋል ከጀመራችሁ በሁዋላ የምታውቁትን ደግ ህዝብ በሌላ መነፅር ማየት ጀምራችኋል”
ለማ፣ (የጃዋር ስም ሲነሳ ቱግ ብሎ በመቆጣት ስሜት)፣ “ደሜ! አንተም በጃዋር ትከሰን? አሁን ይሄ ትንሽ ልጅ በምን አቅሙ ነው አስተሳሰባችን ላይ ተፅእኖ ማድረግ የሚችለው? አየህ ጃዋርን ያቀረብነው ከኦነግ ለማራቅ እንጂ ወደነው እንዳይመስልህ፣ ፈረንጆች ምንድን ነው የሚሉት “ጠላትህን እጅግ ቀረብ አድረግህ ያዘው አይደል የሚሉት? እኛም ጃዋር ላይ በአንገቱ ሰንሰለት አጠለቅንለት እንጂ፣ የርሱ እስረኛ አልሆንንም”
ደመቀ፣” ታዲያ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ የመተቸት ወኔ ከየት ነው የሚመጣው? ምንስ ስላጠፋ ነው፣ ወንጀላችንን ንቆ ለውጡን ምሩ ብሎ እድል ስለሰጠን? ከቶ ምን እንከን ተገኘበት? እስቲ ንገሩኝ።
ለማ፣ “ታከለ ላይ የሚደረገውን ትችት አታይም፣ ሥራውን መሥራት እኮ አልቻለም”
ደመቀ፣ “ታከለ የተተቸስ እንደሆን ምን ይጠበስ? ተው ህግ እየጣስን ባንሰራ ይሻላል፣ ከአዲስ አበባ ምክርቤት አባላት መሃል ከንቲባውን እንምረጥ ስላችሁ እምቢ ብላችሁ ያመጣችሁት ጣጣ አይደል እንዴ? ትችቱንማ ቻሉት እንጂ፣ ሲሆን ለመብቱ ቀናኢ ህዝብ ቢሆን ኖሮ ያንኑ እለት ነበር አደባባይ ወጥቶ አልመለስም ማለት የነበረበት፣ ሆኖም እድል ሊሰጠን ፈቀደ፣ እኛ ግን አልገባንም፣ ትህትናውን እንደ ድክመት ቆጠርንበት”
ለማ፣ “ደሜ! እዚህ እኛ ጋ ምን ታደርጋለህ፣ ለምን ሄደህ የማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪዎቹን አትቀላቀልም!
አቢይ፣ “እናንተ ሁለታችሁ ከቅርብ ወራት ወዲህ በብዙ ጉዳይ መካረር ጀምራችኋል፣ የኦሮማራ ጥምረት እያሳሰበኝ ነው።”
ደመቀ፣ “ኦሮማራ አልሞተም እንዴ፣ በድኑን የሚቀብረው እኮ ነው የጠፋው፣ እስትንፋሱ ይሰማችኋል? እስቲ ንገሩኝ!”
አቢይ፣ “እረ ተው ደሜ እንደዚህ አትሁን! ያኔ በነጌታቸው አፍንጫ ሥር እነዚያን እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ያሳለፍን ሰዎች፣ መሳሪያችንን ታጥቀን ጫማችንን ሳናወልቅ እናሸልብ የነበርን ሰዎች አሁን እንዲህ መለያየት ምን ይጠቅማል ብላችሁ ነው፣ እረ ተው ወንድሞቼ እንደ ዱሮው ተማምነን በጋራ እንሥራ!
ደመቀ፣ “ረሳችሁታ! የታሪክ ሽሚያ ላይ ሆነአ ዓይናችሁ የጠመተው።”
አቢይ፣ “የምን የታሪክ ሽሚያ ነው የምታወራው?”
ደመቀ፣ “አቢይ፣ አንተማ ሁሉን ታውቃለህ፣ ለሥራ ጉብኝት ብዬ ይዤህ እየወጣሁ፣ አይዞህ እያልኩ እያደፋፈርኩ፣ ሥርአቱን መቀየር እንችላለን እያልኩ እያግባበሁ በወራት ምክክር ነበር ከለውጡ ዋዜማ የደረስነው። ሆኖም ሁሉ ነገር በቄሮና ባንተና ለማ ብቻ እንደተደረገ ያልነበረ ታሪክ መፃፍ ጀመራችሁ። ቀጥላችሁም፣ በቄሮ መስዋእትነት የመጣ ለውጥ ስለሆነ ሥልጣኑ ሁሉ ለኛ ይገባናል የሚል ወያኔያዊ ስህተት ውስጥ መዘፈቅ ጀመራችሁ። እውነት ይነገር ከተባለ ግን፣ የወያኔን የበላይነት ብአዴን ገትሮ ሲሞግት ኦህዴዶች የት ነበራችሁ? እስቲ አስታውሱት! ያ ሁሉ ትግል እኮ የተካሄደው ከወያኔ የበላይነት ወደ ኦህዴድ አግላይነት ለመሸጋገር አልነበረም። የዚያ የዚያማ ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ከህዝባቸው ርቀው የመጡትና ራሳቸውን እንደፀጉረ ልውጥ በማየት ደንገጥ የሚሉት ህወሓቶች ይሻሉ ነበር! በብዙ መልኩ።
አቢይ፣ “እንዲህ አምርረህ ለመናገር ምን ምክንያት አለህ?”
ለማ፣ “በለውጥ ስም ከትምክህተኞች ጋር እየዋለ ምን ትጠብቃለህ? ደርጎች አይደሉ እንዴ ሲያማክሯቸው የሚውሉት!
አቢይ፣ “ለማ እባክህ እንደሱ አትበል፣ ታምራት ላይኔ ጥያቄ ባነሳ ቁጥር፣ አንተ ከትምክህተኞች ጋ እየዋልክ በማለት መለስ አላናግር እያለው ሥርአቱ ለመታረም የነበረውን እድል እንዳጨናገ ታምራት አጫውቶኛል ዴንቨር፣ ኮሎራዶ ቤቱ ባመሸንበት ወቅት።
ደመቀ፣ (ወደ አቢይ እየተመለከተ) “የለማ ክስ ለመልስም ስለማይበቃ ልተወው። የምሬትህ ምክንያት ምንድን ነው ያልከኝን ልዘርዝርልህ። በመከላከያና ደህንነት አደረጃጀት የኦሮሞን የበላይነት ለማስጠበቅ ያደረጋችሁት፣ ታከለን አዲስአበባ አምጥታችሁ በየደረጃው ያለውን አስተዳደር ለመውሰድ የሠራችሁት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለ75 ዓመታት ያካበተውን ሃብቱን ያስቀመጠባትን አንዲት ባንክ አመራር አግልላችሁና ጠቅልላችሁ ለመውሰድ የፈፀማችሁት ወዘተ ወዘተ ከብዙው እጅግ በጥቂቱ ነው። ታዲያ ይህ አያስመርርም?
አቢይ፣ “ምሬትህ ይገባኛል፣ ግን የኔንም ችግር ተረዳልኛ። ኦነግ ምእራብ ኦሮሚያን ነጥቆናል። ከዚያም አልፎ ሃገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ 14 ወራት ብቻ ነው የቀሩን። በኦነግና ኦፌኮ ኦሮሚያን ከተነጠቅን ምን ላይ ቆመን ማሸነፍ እንችላለን? የኦሮሚያን ልብ ለማሸነፍ የግድ የኦነግን አጀንዳ መንጠቅ መገደዳችን ስልታዊ (ታክቲካል) አካሄድ እንጂ ስትራተጂክ ግብ እንዳልሆነ እንዴት ላንተ ይሳትሃል?
ደመቀ፣ (ወደ ለማ እየተመለከተ)፣ እዚህ ላይ አንድ ገፅ ላይ ናችሁ? እየተናበባችሁ ነው የምትሠሩት? እውን ይህ ሁሉ ሥራችሁ ታክቲካዊ እንጂ የመጨረሻ ግባችሁ አይደለም?
ለማ፣ ምን መሰለህ ደሜ! እንዲህ ፍርጥርጥ አድርጎ መወያየቱን እኔም አልጠላውም። ምናልባት ከ10 ወራት በፊት በዚህ መጀመርና መተማመን ነበረብን። ፍኖተካርታውን  አብረን መሳል ነበረብን። ያን ማድረግ አልቻለንም። ከዚያ ደግሞ እነጌታቸው በየቦታው የለኮሱዋቸው እሳቶች ፋታ አልሰጥ አሉን። በእሳት ማጥፋትና፣ በተፈናቃዪች ችግር ተዋጥን። ቁጭ ብለን የመድረሻ ግባችንን ለማሰብ ፋታ አላገኘንም። ይህ አሁን የተዘፈቅንበት አለመተማመን ውስጥ ከቶናል። ታክቲኩና ስትራተጂው ተደበላልቆብናል። እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ የኦሮሞ ክልል መሪ ነኝ። ቀዳሚ ሃላፊነቴም የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም መወከል ነው። “እትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” ስላልኩ ቀዳሚ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ነው ማለቴ አልነበረም። ኢትዮጵያዊው ራሱ በነበረው ረሃብ የሰጠው ትርጓሜ ነው። ይገባኛል፣ እናንት አማሮች በታሪክ በነበራችሁ ሚና የተነሳ በኢትዮጵያዊነታችሁና በአማራነታችሁ መሃል ያለው መስመር የደበዘዘ ነው። ከአንዱ ወደሌላው እንደልባችሁ መሸጋገር ትችላላችሁ። ለኛ ግን እንደዚያ አይደለም። እኛም በታሪክ በነበረን ቦታ የተነሳ ኢትዮጵያዊነታችን የድርድር ጉዳይ ሆኖብናል። ወደን አይደለም። ታሪክ የጣለብን ቀንበር ነው። ቀዳሚ ማንነታችን ኢትዮጵያዊ ቢሆን ባልጠላን ነበር፣ ሆኖም አንድ ቀን ከዚያ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ። አልዋሽህም ዛሬ ግን እዚያ ጋ አይደለንም። ይህ ለኩርፊያና መለያየት መንስኤ መሆን የለበትም። ጊዜ ስጡን፣ ኦሮሞው የሃገረ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቱን እያየ ሲሄድ የአንድነት ፋይዳውን እየተረዳ ሲሄድ ዛሬ እናንተ ካላችሁበት አድማስ ይደርሳል። ታገሱን።
ደመቀ፣ “እኛስ እስከዚያ ምን እንድርግ? ዝም ብለን እንያችሁ? የኛስ ልሂቃንና ሰፊው ህዝብ የምታደርጉትን እያየ የሚታገሰን ይመስላችኋል? እኛስ ምርጫ ስንሄድ፣ በፊት በወያኔ አሁን በናንተ ተላላኪነት እየተከሰስን ምርጫውን ማሸነፍ የምንችል ይመስላችኋል? እኛስ ከተሸነፍን እንዴት አድርጎ ነው ፓርቲያችን ሃገራዊ ምርጫውን አሸንፎ በሥልጣን መቀጠል የሚችለው? የኛስ ችግር ይታያችኋል። ሙፍሪያት፣ ወርቅነህ ሃሳብ ስጡ እንጂ፣ ምንድን ነው ዝምታው?
ከውጪ ስልክ ተደወለ። የጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሮ በር በከፍተኛ ድምፅ እየተንኳኳ ነው። ከባልደራስ  ስብሰባ እስክንድር ነጋን አድምጦ በመመለስ ላይ የነበረው ወጣት አራት ኪሎ አካባቢ የሚያሰማው ድምፅ በመስኮቶቹ ሰርጎ እየገባ ነው።
አሁን ከጠዋቱ አንድ ሰአት (7:00 ኤ ኤም) ይላል። አቦ! ሄጄ ትንሽ ልተኛበት፣ ሥራ ከመጀመሬ በፊት ። ክፍል ሁለትን በሌላ ቀን ጠብቁ።
Filed in: Amharic