>
5:13 pm - Thursday April 19, 1629

የሌላውን “ሞት” እና "የብቻ ህይወት" የሚያውጁ የሃሳብ ስንኩላን ናቸው!!! (ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን )

የሌላውን “ሞት” እና “የብቻ ህይወት” የሚያውጁ የሃሳብ ስንኩላን ናቸው!!!
ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን
ዛሬ ዕለተ ቅዳሜ አንባቢያን እጅ መድረስ የነበረባቸው ጋዜጦች ለአደባባይ አልበቁም፡፡ ብርሐንና ሠላም “ማሽን ተበላሽብኝ” ብሎ ነው አሉ በዕለቱ ለንባብ ያልበቁት፡፡ በሐገሪቱ አለ የሚባለው አንጋፋ ማተሚያ ቤት ማሽን ተበላሸብኝ ብሎ በአንድ ቀን በቁጥር 100 ሺ (ሁሉም ተደምረው) ኮፒ የማይሞሉ ጋዜጣዎችን ለአደባባይ እንዳይበቁ ማድረጉ አሳፋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥርጣሬ ከመፍጠር በቀር ስሜት አይሰጥም፡፡ ቢያንስ በ1997 ዓ.ም በአንድ ቀን 5 መቶ እና ስድስት መቶ ሺ ኮፒ ያትም እንደነበረ እናውቃለንና፡፡
.
የሆነ ሆኖ ብርሐንና ሠላምን እንመነውና 😀 ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 30/2011 ዓም ጋዜጦች ለንባብ አልበቁም፡፡  (አሁን ከመሸ የጋዜጦቹ ህትመት መጠናቀቁን ሰምቻለሁ) ነገ እሁድ መጋቢት 1/2011 ግን አንባቢያን እጅ ይደርሳሉ፡፡
.
እና….
እኔም ስለአዲሳባ እንዲህ የሚል ወግ ከትቤያለሁ፦
የሸገር ልጅ ነኝ – የአዲሳባ
አንዱን ጥዬ ሌላውን የማላንጠለጥል የሸገር ልጅ ነኝ፡፡ ራሴን የምመስል፣ ሌላውንም የማልጥል፤ ሁሉንም አኑሬ፤ እንደሁሉም ኖሬ፤ ከሁሉም አብሬ፣ በፍቅር ሰግሬ፤ ለፍቅር ዘምሬ፤ ከሁሉም ሰምሬ ህይወትን የምመራ …..የሸገር ልጅ ነኝ፡- የአዲሳባ፡፡
ከኦሮሞው ጋር ተዋድጄ፤ ከአማራው ጋር ተዋህጄ፤ ከትግሬው ጋር ተጋምጄ፤ ከጉራጌው ጋር ተጣምሬ፤ ከወላይታው ጋር ዘምሬ፤ ከሱማሌው ጋር ተጣምሬ፤ ከጉምዙ ጋር ተፋቅሬ፣ ከሌላው ከሌላውም ተደምሬ፤ በሕብረ ባህል የደመቅኩ፤ በአብሮነት ፀጋ የከበርኩ፤ ከሁሉም ጋር የተሰናሰንኩ፤ በእምነት ቀለም ያሸበረቅኩ …. የሸገር ልጅ ነኝ፡- የአዲሳባ፡፡
አዎ፤ የአዲሳባ ልጅ ነኝ፡፡ በብሔር የማልገደብ፤ በቋንቋ የማልሻጠር፣ በልዩነት የማልታጠር፤ በእብሪት የማልኮፈስ፤ በአግላይነት ማልጠረጠር፤ አንድነት ነው እምነቴ፡-ሸገራዊ ማንነቴ፤ ዘላለማዊ እውነቴ፡፡ የህልውናዬ መሰረት፣ ሸገራዊ ጦር ጥሩሬ፣ “ሰው”ን በብሔሩ ሳይሆን፣ ሰውን በቋንቋው ሳይሆን፣ ሰውን በየት መጤነቱ ሳይሆን፣ ሰውን በሰውነቱ ማፍቅር፤ በሰውነቱ መቀበል ነው፡፡ በቃ የሸገር ልጅ ማለት ፍቅር ብቻ ነው ሚዛኑ፡- ሰውነቱ ነው ኪዳኑ፡፡
.
“እኔ ለወዳጄ፣ አንዲት ናት ግዳጄ!
ሲመጡ መቀበል – ሲሄዱ መሸኘት
እንደልቡ ሲሆን፣ የልቡን ለማግኘት”
እንዲል ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ፡- ክንዴን የምዘረጋ፣ ደጃፌን የማልዘጋ፣ ከሁሉንም እንደአመጣጡ የምቀበል፣ ሁሉንም እንደመሻቱ የማስጠልል፣ “እንኳንስ ሰው ወፍ የማለምድ”፣ እቡይነትን የማልወድ፣ ሁሉንም አክብሬ፣ በማክበሬ ተከብሬ፣ ከሁሉም ጋር መክሬ፣  ከሁሉም ጋር ዘክሬ የምኖር፣ መሄድ ያሻውን የምሸኝ፣ ፍቅር ብቻ የሚገደኝ…አዎ የሸገል ልጅ ነኝ – የአዲሳባ፡፡
 
እነዚህ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ይገርሙኛል?!?
 
ስግብግብነታቸው ያስቀኛል፤ ደግሞም ያሳቅቀኛል፡፡ የብሔር/የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች “ለእኔ” እንጂ “ለእኛ” ብሎ ነገር አያውቁም፡፡ መፈክራቸው “ከራስ በላይ ንፋስ” ዓይነት ነው፡፡ ከአፍንጫቸው አርቀው አያስቡም፡፡ የግለኝነት በሽታ የተጠናወታቸው ናቸው፤ አብሮነት አይስማማቸውም፡፡  የጋራ ኑሮ፣ የጋራ ሕይወት፣ የጋራ ጥቅም፣ የጋራ ሀገር ወዘተ ብሎ ነገር ሕመማቸው ነው፡፡ በአጭሩ ስግብግቦች ናቸው፡፡ ተማሩም አልተማሩም፣ ሕልማቸውም ግባቸውም ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም አበቃቃላቸውም፣ አስተዳደጋቸውም የተጣመመ ነው፡፡ አስተሳሰባቸውም የጎበጠ፡፡ ስለዚህም ቀናነት ብሎ ነገር አይሆንላቸውም፡፡ ከጥንታዊ የአውሮፓውያን ፈላስፎች አንዱ በአስተምህሮው እንደገለፃቸው ጠማማ ዛፎች “ሴረኞች” ናቸው፡፡ እንደውም እዚህ ላይ የዚህን ጥንታዊ ፈላስፋ አስተምሮ ብንተርከው ነው የሚሻለው፡፡
በዲሞክራሲ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር አስተምህሮ
ፈላስፋው ዜግነቱ ሩሲያዊ መሰለኝ፡-  እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስሙም ተዘንግቶኛል፡፡ ዜግነቱም ሆነ ስሙ ማንም ይሁን ምንም፤ አሁን የሚያስፈልገን አስተምሮቱ ነው፡፡
በዲሞክራሲ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር አስተምህሮቱ፡፡ እናም ከፊት ለፊቱ በአሻጋሪ ያለውን ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነውን ተራራ እያመለከተ ነበር ገለፃውን የጀመረው፡-
“ይታያችኋል ያ በደን ጥቅጥቅ ያለ ተራራ!… እዚያ ተራራ ውስጥ የበቀሉት ሁለት ዓይነት ዛፎች ናቸው፡፡ እጅግ ረዣዥም እና ቀጥ ቀጥ ያሉ፤ እንዲሁም እጅግ አጫጭር እና ጎባጣ ዛፎች ናቸው ተራራውን የሸፈኑት፡፡ …” አለ፡፡
ቀጠለ፡-
“አጫጭሮቹና ጎባጦቹ መብታችን ተነፈገ ባዮች ናቸው፡፡ ማነው መብታችሁን የነፈገው? ሲባሉ ረዣዥሞቹና ቀጥ ቀጥ ያሉ ዛፎች ናቸው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እጅግ ቀጥ ቀጥ ያሉ የረዘሙ በመሆናቸው ከእኛ ቀድመው ንፋስ፣ ዝናብና ፀሐይ ያገኛሉ፡፡ ስራቸውም እጅግ ረዣዥም በመሆኑ ከእኛ ቀድመው ለዛፎች ዕድገት የሚያስፈልገንን የምድርን ማዕድን ይሰበስባሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ነው እኛ አጭርና ጎባጣ ለመሆነው የበቃነው” ይላሉ፡፡
“በነገራችን ላይ…”  አለ ፈላስፋው ትንፋሹን ሰብሰብ አድርጎ፡፡ “በነገራችን ላይ እዚያ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ የሚመላለስ አንድ ገበሬ አለ፡፡ እሱ ብቻ ወደዚያ በደን ወደተሸፈነ ጥቅጥቅ ያለ ተራራ የሚመላለሰው፡፡ ዛፎቹ ያ ብቸኛ ገበሬ ለምን እንደሚመላለስ ያውቃሉ፡፡ በገበሬው ወደዚያ ተራራ ጎራ ማለት ይበልጥ የሚደሰቱት ግን አጫጭሮቹና ጎባጦቹ ዛፎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያ ገበሬ ወደዚያ ተራራ የሚዘልቀው የመጥረቢያ ዛቢያ ለመቁረጥ ነው፡፡ ለመጥረቢያ ዛቢያነት የሚሆኑት ደግሞ እነሱዉ ናቸው፡- አጠርና ጎበጥ ያሉ በመሆናቸው፡፡ ቀድሞ የሚቆርጣቸውም እነሱኑ ነው፡፡ ቢሆንም በገበሬው መምጣት እጅጉን ይደሰታሉ፡፡”፡፡
እናም “አጫጭሮቹ እና ጎባጦቹ ዛፎች  የሚደሰቱት ለምን መሰላችሁ?” ሲል ይጠይቅና፤ ራሱ ምላሽ ሰጥቶ አስተምህሮቱን ይደመድማል፡፡ እነሆ ምላሹ፡-
“አጫጭሮቹ ዛፎች፣ ገበሬው አስቀድሞ እነሱን እንደሚቆርጥ እያወቁ በደስታ የሚፍነከነኩት፤…. ገና ለገና ተቆርጠው፤ ገና ለገና የመጥረቢያ ዛቢያ ሆነው፤ ገና ለገና ገበሬው እጅ ላይ ውለው፤ ገና ለገና ረዣዥምና ቀጥ ቀጥ ያሉትን ዛፎች ገንድሰው መጣልን ስለሚያልሙ (ስለሚጥሉ) ነው”
ይኸው ነው፡፡ ፅንፈኛ ብሔርተኞችም እንደዛው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው አበቃቀላቸው ጠማማ፣ አስተሳሰባቸው (አመለካከታቸው) ጠባብ ነው ያልኩት፡፡ ለዚህ ነው ቀናነት ፈፅሞ አይዳብሳቸውም ያልኩት፡፡
የሌላውን “ሞት” እና የብቻ ህይወት የሚያውጁ የሃሳብ ስንኩላን ናቸው!!!
ነገሮችን ከማስተዋል፣ ራስን ቀና ከማድረግ፣ ችግራቸውን ከመለየት፣ እና መፍትሄ ከመሻት ይልቅ፣ ቀና ያለውን፣ ቀጥ ብሎ ያደገውን፣ በከፍታ ዕድገት ያለውን መቁረጥ፣ ጎትቶ መጣል ነው የሚቀናቸው፡፡ ለራሳቸው ሳይበጁ፣ የሌላውን “ሞት” እና የብቻ ህይወት የሚያውጁ የሃሳብ ስንኩላን ናቸው፡፡ የአብሮነት ህይወት የማይጥማቸው ስስታሞች ናቸው፡፡
አዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ ግን ይህ “የእኔ ብቻ” ስስት አይነካካቸውም፡፡ አብሮነት ነው መክሊታቸው፡፡ አብሮነት ነው ውበታቸው፤ አብሮነት ነው ዕድገታቸው፤ እምነታቸው፡፡
.
ምንጭ:-ከቦሌ_ታይምስ_ጋዜጣ_
Filed in: Amharic