>
5:13 pm - Saturday April 20, 8199

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዙሪያ ያሉ ሕገ መንግስታዊ ግድፈቶች!!! (ግርማ ካሳ)

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዙሪያ ያሉ ሕገ መንግስታዊ ግድፈቶች!!!
ግርማ ካሳ
አምስት ሚልዮን የአዲስ አበባ ሕዝብ ብትወስዱ በፌዴሪሽን ምክር ቤት ውክልና የለውም!!!
 
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰን፣ አከላለልና የማንነት ጉዳዮችን የሚመለከት ኮሚሽን በአዋጅ አቋቁሟል። የዚህን ኮሚሽን መቋቋምን አንዳንድ ወገኖች “ሕገ መንግስቱን የጣሰ ነው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ሃላፊነት የሚጋፋ ነው” እያሉ ይከሳሉ። በሌላ በኩል የኮሚሽኑ መቋቋም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ሆኖ ጥናትና ሪፖርት የሚያቀርብ እንደሆነ የሚናገሩት የኮሚሽኑን መቋቋም የሚደገፉ አካላት፣ “የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደ ግባት ሊጠቀምበት ይችላል” በማለት የኮሚሽኑ መቋቋም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስራ ጣልቃ መግባት እንዳለሆነ በመግለጽ ይከራከራሉ።
ያ ማለት አሁን የዶ/ር አብይ አስተዳደር የወሰንና የማንነት ኮሚሽን እንዲቋቋም ቢያደርግም፣ ኮሚሽኑ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጭ ምንም ነገር የማድረግ ስልጣን እንደሌለው ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዬ ወ/ሮ ኪሪያ ኢብራሂም በወልቃይት ጠገዴና ራያ አካባቢ ስላለው ቀውስ ፣ የፌዴሪሽን ምክር ቤቱ ሰላማዊና ህዝብን ማእከል ባደረገ መልኩ ችግሮቹን ለመፍታት ገለልተኛ ኮሚቴ እንደሚያዋቅሩ እንደገለጹ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። በወልቃይት፣ ራያና ተመሳሳይ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊሰራ ያሰበውን ለጊዘው እናቆየዉና ይሄ የፌዴሪሽን ምክር ቤት የሚባለው አካል ምን እንደሆነ የሚገልጽ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማስቀመጥ እምክራለሁ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዋናነት ሁለት ቁልፍ ተግባራትን እንደሚፈጽም በሕግ መንግስቱ ተደንግጓል። እነርሱም በአንቀጽ 48 እና አንቀጽ 83/84 ላይ ይገኛሉ።
አንቀጽ 48 ፣ “የክልሎችም ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል” ይላል። (በነገራችን ላይ የፌዴሪሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከተጠበቀ፣ በዚህ ሕግ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እነ ወልቃይትን በተመለከተ ሕዝብ ዉሳኔ እንዲደረግ ከማድረግ ውጭ ሌላ ነገር ማድረግ እንደማይቻል ከወዲሁ ማወቁ ጥሩ ነው)
አንቀጽ 83 ደግሞ ፣ “ የሕገ መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉስኔ ያገኛል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕግ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ በሚያቀርብለት ሕግ መንግስታዊ ጉዳይ ላይ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ዉስኔ ይሰጣል” ሲል አንቀጽ 84 የሕግ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዬ አባላት 11 እንደሆኑም ያስቀምጣል። እነርሱም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዘዳንት፣ በፓርላማ አቅራቢነት በፕሬዘዳንቱ የሚሾሙ ስድስት የሕግ ባለሞያዎችና ሶስት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተመረጡ ሶስት የምክር ቤቱ አባላት።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት
፩. ኢትዮጵያ ውስጥ በ2007 የሕዝብ ቆጠራ ሪፖርት መሰረት 86 ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች የሚሏቸው አሉ። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 61 መሰረት እያንዳንዳቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዳንድ መቀመጫ አላቸው።
፪. ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ብዛት ያላቸው ለአንድ ሚሊዮን ተጨማሪ አንድ መቀመጫ ያገኛሉ። ከ86ቱ አስር የሚሆኑት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ናቸው። ኦሮሞዎች ከ29 ሚሊዮን በላይ ስለሆኑ ተጨማሪ 29 መቀመጫ ያገኛሉ። አማራዎች 19፣ ሶማሌዎችና ትግሬዎች 4 ፣ ሲዳማዎች 2፣ ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች፣ ጋሞዎች፣ አፋሮች፣ ሃዲያዎች ተጨማሪ አንድ አንድ ያገኛሉ።
በአጠቃላይ ኦሮሞ 30፣ አማራ 20፣ ሶማሌና ትግሬ 5 ፣ ሲዳማ 3 ፣ ሃዲያ፣ ጋሞ፣ አፋር ጉራጌና ወልይታ እያንዳንዳቸው 2 ሲኖራቸው የተቀሩት 76 ብሄር ብሄረሰብና ሕዝቦች አንዳንድ መቀመጫ ነው የሚኖራቸው።
፫. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን የሚመርጡት የክልል ምክር ቤቶች ናቸው ይላል ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 61። ይህ ማለት ክልሎችን ከብሄር ብሄረሰብ ጋር በቀጥታ ያገናኘዋል። ዶ/ር አብይ ከአዋሳ የኢሕአዴግ ጉባዬ በኋላ ክልሎችን ከብሄር ብሄረሰብ ጋር ማገናኝት የለብንም ያሉት አሁን ባለው ሕግ መንግስት እንደማይሆን ይሄም ግልጽ ማሳያ ነው። ሕግ መንግስቱ ራሱ ክልሎችን ከብሄር ብሄረሰብ ጋር ያገናኘበትና ያምታታበት ሁኔታ ነው ያለው።
– ወደ አማራ ተወካዮች ብንሄድ ራሱን የቻለ ትልቅ ተቃርኖ እናያለን። በ2007 የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት ከሃያ በመቶ በላይ አማራዎች የሚኖሩት ከአማራ ክልል ውጭ ነው። የአማራ ተወካዮች ፣ ምን ያህሉ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ የክልል ምክር ቤቶች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወከሉ ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም ነው የሚሆነው። ያ ማለት ሃያ በመቶ ራሱን አማራ ነኝ የሚለው በአማራ ክልል የማይኖረው ማህበረሰብ በፌዴሪሽን ምክር ቤት ዉክልና እንደሌለው ነው የሚያሳየው።
– የአዲስ አበባ ሕዝብ ብትወስዱ በፌዴሪሽን ምክር ቤት ውክልና የለውም።
– ለነርሱ ጎሳ ከተመደበው አካባቢ ውጭ ያሉ ወገኖች ዉክልና የላቸውም። በከሚሴ ያሉ ኦሮሞዎች፣ በጎንደር ያሉ ትግሬዎች፣ በሶማሌ ክልል ያሉ ኦሮሞዎች፣ በቤኔሻንጉል ክልል ክልል ያሉ አማራዎችና ኦሮሞዎች ….ዉክልና የላቸውም።
ከዚህም መደምደም የምንችለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት አመራረጥ ግልጽነትና ዴሞክራሲያዊነት በሌለው መልኩ መሆኑን ነው።
፬. በሕዝብ ብዛት ትላልቅ የሆኑ ማህበረሰባትን ብንመለከት ኦሮሞ፣ አማራና ሶማሌ ከአንድ እስከ ሶስት ናቸው። ከኢትዮጵያ ህዝብ ከሁለት ሶስተኛ በላይ ናቸው። ኦሮምና አማራን ብቻ ከወሰድን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ 62% በመቶ ናቸው። በፊዲሬሽን ምክር ቤት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ 2/3ኛ የሆኑት ያላቸው መቀመጫ ከ129 ኙ 42% ቱን ነው። 62% የሆኑት ደግሞ 38% ቱን ነው። ይሄም ሌላ በራሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ኢዲሞክራሲያዊነትንና ኢፍትሃዊነትን የሚያመላክት ነው።
፭. ከላይ እንዳልነው አሁን ያለው የፌዲሬሽን ምክር ቤት የተመረጠው በክልል ምከር ቤቶች ነው። የክልል ምክር ቤቶች ደግሞ ባለው ነጻና ፍትሃዊ ባልሆነው፣ አሳፋሪዉና አስቂኙ ምርጫ የተመረጡ ናቸው። በመቶ በመቶው ምርጫ። በመሆኑም በዚያ መልኩ የተመረጡ ግለሰቦች ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የመወሰን ማንዴትና ሌጂቲመሲ የላቸውም። እነርሱ የወሰኑትን ገዢ አድርጎ መቀበል አይቻልም።
፮. የፌዴሪሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤት ይመረጣሉ ይላል እንጂ ሕገ መንግስቱ፣ የሕግ ባለሞያዎች መሆን ስላለባቸው የተናገረው ነገር የለም። ያ ማለት ስለ አገሪቷ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የፍትሃ ብሄርና ሕገ መንግስታዊ ሕጎች የማያውቁ ፣ በሞያቸው ከሕግ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። አብዛኞቹ አባላትም በአሁኑ ጊዜ የሕግ ባለሞያዎች አይደሉም። ይሄ ማለት በአገሪቷ የሕጎች ሁሉ ሕግ በሆነው በሕገ መንግስቱ ዙሪያ ሕጉን እንዲተረግሙ ስልጣን የተሰጣቸው ብቃቱ የሌላቸው ወገኖች ናቸው ማለት ነው።
፯. ሕግ መንግስቱ በአንቀጽ 78 ንኡስ አንቀስ 1 “ነጻ የዳኝነት አካል በዚህ ሕግ መንግስት ተቋቁሟል” ይላል። በንኡስ አቀጽ 2 ደግሞ “የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የዳኝነት አካል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል “ብሎ በግልጽ የፍትህ አካሉ የበላይ ፍርድ ቤት እንደሆነ ይደነግጋል።በአንቀጽ 83 ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው “ የሕገ መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉስኔ ያገኛል” ይላል።
ይሄ ማለት የሕጎች የበላይ የሆነው ሕግ መንግስቱ እንደመሆኑ፣ ሄዶ ሄዶ ጉዳዮች የሚቋጩት በበፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወሰነዉን ዉስኔ የፌዴሪሽን ምክር በቱ ሊገለብጠው ይችላል ማለት ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የምናየው አንቀጽ 78 እና አንቀጽ 83 እርስ በርስ በቀጥታ እንደሚጋጩ ነው።
የፌዴሪሽን ምክር ቤት ያለ ምንም ማጋነን የዘር ካርድ ለመጫወት እነ መለስ ዜናዊ ያዋቀሩት ቀልድ የሆነ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ስር ነቀል በሆነ መልኩ መሻሻል ያለበት ተቋም ነው። አንደኛ ሕግ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ሊኖረው አይገባም። ፍርድ ቤት ሙሉ ለሙሉ ነጻና ገለልተኛ መሆን ነው ያለበት። ሁለተኛ ምክር ቤቱ የባህል መእከል ወይንም የብሄረሰቦች ኢንስቲትዩት መሆን የለበትም። የፌዴራል መስተዳድሮችን የሚወክሉ፣ በቀጥታ በሕዝብ የተመረጡ፣ ከጎሳና ከዘር ጋር ያልተገናኙ መሆን መቻል አለባቸው።
አሁን ያለው የፌዴራል ምክር ቤት በህግ፣ በብቃት አንጻር በአገሪቷ የተፈጠሩ ችግሮን የመፍታት አቅም የለውም። አባላቱ ፍላጎቱና ቅንነቱ ቢኖራቸውም አወቃቀሩና የምክር ቤቱ አሰራር ግን አይፈቅድላቸውም።
በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰን፣ አከላለልና የማነት ጉዳዮችን የሚመለከት ኮሚሽን በአዋጅ አቋቁማል። የዚህን ኮሚሽን መቋቋምን አንዳንድ ወገኖች “ሕገ መንግስቱን የጣሰ ነው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ሃላፊነት የሚጋፋ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። የኮሚሽኑ መቋቋም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ሆኖ ጥናትና ሪፖርት ነው የሚያቀርበው። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የኮሞሽኑን ሪፖርት እንደ ግባት ለጠቀምበት ይችላል” በማለት የኮሚሽኑ መቋቋም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስራ ጣልቃ መግባት እንዳለሆነ በመህገልጽ የመንግስት ባለስልጣናት ይከራከራሉ። ያ ማለት አሁን የዶ/ር አብይ አስተዳደር የወሰንና የማንነት ኮሚሽን እንዲቋቋም ቢያደርግም፣ ኮሚሽኑ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጭ ምንም ነገር የማድረግ ስልጣን የለውም።
ምንጭ:- በረራ ጋዜጣ
February 16, 2019
Filed in: Amharic