>

ጥቂት... ስለ ግርማዊ ጃንሆይ መታሰቢያ ኃውልት !!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጥቂት… ስለ ግርማዊ ጃንሆይ መታሰቢያ ኃውልት !!!

አሰፋ ሀይሉ

 

ከብዙ ተደጋጋሚ ሕዝባዊ ውትወታ በኋላ – እና –  የግራ-ዘመሙን የህወኀት-ኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣነ-መንበር ማዝመም ተከትሎ – የዚሁ የእኛው ምቀኛ ብሔር-ተኮር መንግሥት – ቀደም ሲል ለአፍሪካ ህብረት ያሰማውን ቁጣ የቀላቀለበት ተቃውሞ – ይሄኛው የዶ/ር አብይ መንግሥት ማንሳቱን ተከትሎ – አንድ ነገር ሆነ። የታላቁ የአፍሪቃ ግርማ-ሞገስ የግርማዊነታቸው ኃውልት በአዲስ አበባችን ታነፀ። ቆመ። ተነሳ። ኢትዮጵያዊነት- አፍሪካዊነት – ፀረ-ባርነት – ነፃነት – ተነሳሳ። ነፃነት ባርነትን እነሆ ድል ነሳ!!

(በነገራችን ላይ የቀኃሥን ኃውልቶች ከየተተከሉበት እያሰሰ ሲያፈራርስ የኖረው ወታደራዊ መንግሥትም በዘመኑ የእሳቸው ኃውልት እንዳይሰራ በተቃውሞው ፀንቶ ነው የተሰናበተው! ይሄ ይሄ ሲሰማ ጥሎብን “መረገም” ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል?!?!)

ቀደም ሲል የአፍሪካ ህብረት ከግርማዊነታቸው በመቀጠል – (ልክ እንደ እነ ጁልየስ ኔሬሬ) – ለአፍሪካ አንድነት ታላቅ አስተዋፅዖ ያበረከቱትን የጋናውን ክዋሜ ንኩሩማህ መታሰቢያ ኃውልት ብቻ ለይቶ በማቆሙ በብዙ ለአፍሪካ እውነተኛ የነፃነት ታሪክ በሚቆረቆሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጉትጎታና ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

እና አሁን በስተመጨረሻ –  የኢትዮጵያው የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት – የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ኃውልት – በቀድሞው እሳቸው ከካዝናቸው ሶስት ሚሊየን ብር ከስክሰው (በአሁን ሶስት መቶ ሚሊየን አይሆን ይሆን?!) – እና በግሩም ዓለማቀፍ ንድፍ አዋቂዎች አሰርተው – ዙሪያቸውን አፍሪካውያንን እያስገበሩ ከከበቧቸው የአፍሪካውያንን አንድነት ከማይፈልጉ ጉልበታም አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው – ታላቁን አይቀሬውን የአፍሪካውያን ሕዝቦች የወደፊት አንድነት ቀድመው በማለም – በነፃይቱ አቢሲኒያ በጭቆና ተፅዕኖ ሥር ላሉ አፍሪካውያን እንደልባቸው መሠብሰቢያ እንዲሆናቸው በማለት ባሠሩት – እና የመጀመሪያውንም የመሪዎች ጉባዔ መርቀው በከፈቱበት – አዲስ አበባ ከተማ ዕምብርት ላይ ባሳነፁት – የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ቅፅር ግቢ ውስጥ በስማቸው እንዲቆምላቸው ተደረገ።

ከስንት እግዚኦታ በኋላ አሁን የቆመላቸው የእኚህ ታላቅ የነፃይቱ አፍሪካ ወላጅ አባት የግርማዊ ጃንሆይ መታሰቢያ – ይህ ዘመኑን ጠብቆ በፀረ-ታሪኮችና በምቀኞች ተቀብሮ የቆየ ታሪካቸው – እንዲህ በገሀድ ተገልፆ መውጣቱ – ታላቅ ራዕይን አንግበው ለተሟሟቱበትና ላሳኩት የአፍሪካውያን ነፃነት የቤት ሥራቸው ዕውቅና መሠጠት መጀመሩ – ለዚህች ሀገርና ለአፍሪካችን ታሪክ እና አኩሪ ቅርሶቿ ለምንጨነቅ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንጀት አርስ የምሥራች ነው።

እምዬ ኢትዮጵያ በአዲስ የነፃነት ኃይል አንሠራርታ ለሺህዎች ዓመታት በጉያዋ አኑራ የቆየችውን ነፃነት ለራሷና ለአፍሪካ ሕዝቦች ለማዳረስ ታላቅ ቃልኪዳኗን የምታድስበት ማስታወሻም ነው – ይህ ዛሬ በመካከላችን የቆመው የአፍሪካውያን የነፃነት አባት መታሰቢያ ኃውልት።

በኃውልቱ አወቃቀር ላይ ግን የብዙዎችን ቅሬታ እኔም ሳልገልፅ ማለፍ አላስቻለኝም። የዚህ የግርማዊ ጃንሆይ ኃውልት ቀረፃ ለአርቲስት መምህር በቀለ መኮንን እንደተሰጠም ከወራት በፊት ሰምቼያለሁ። ለአርቲስቱ እና ሥራዎቹ እንደ ጥበብ አድናቂና ተከታታይ ትልቅ አክብሮት አለኝ።

ይህ የደብረዘይት የአድአ ኢትዮጵያዊት መረሬ አፈር ያበቀለችው – በቀለ መኮንን – ድንቅ ችሎታን የተካነ ቀራፂ በአርት ስኩል በተማሪነት ዘመኑ በላቀ ተሰጥዖው ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ለመምህርነት የታጨ ማኛ ወጣት ጥበብ ፈላጊ እንደነበረ፣ ወደ ሶሻሊስት ሩሲያ በቀደምትነት ተልከው ጥበብን ከቀሰሙ ጥቂት ብርቅ ኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነ፣ አሁን በመሥራቹ አርቲስት አሌ ፈለገሠላም ስም በተሰየመው የአዲስ አበባ አርት ስኩል ውስጥም በቄ ለረዥም ዓመታት ጥበብን በማስተማር ብዙ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን እንዳፈራም፣ በዳይሬክተርነት እንዳገለገለና እንደሚገኝም አውቃለሁ።

በዚያ ላይ አርቲስት በቀለ መኮንንን ዘመኑን የሚኮረኩሩ “እንቆቅልሽ” የሚል ዲግሪና ሞፈርን ጎንለጎን በሚያሳይ ዐውደ ጥበቡ (ኤግዚቢሽኑ)፣ “ባሩድና ብርጉድ” በሚል ቦምብና በርበሬ በሙቀጫ ስንወቅጥ በሚያሳይ አውደ ጥበቡ፣ በተሸነቆሩ ድስቶች፣ “ነፍስ አድን በነፍስ አድድን”፣ወዘተ በሚሉ ከየት ወደየት እየሄድን እንደሆነ ህሊናችንን እንድንጠይቅ የግድ በሚሉ ጥበባዊ ሥራዎቹም ከአርቲስትነቱም ባሻገር ከልብ የማከብረው ማህበራዊ ሃያሲ እና ትውልድ ቀራፂ ነው።

የቀራፂውን የ70ዎቹን ሥራዎች የፈለገ … በደብረዘይት ዓየር ኃይል ግቢ መግቢያ ላይ ያሉትን ግርማን የተጎናፀፉ ጡንቻማ የጭቁኑ ሕዝብ መለዮ ለባሽ የለውጥ ሃዋርያት ኃውልት ማየት ይበቃዋል።

የቅርብ ሥራዎቹን ለማየት ደግሞ… በናዝሬት ከተማ በድሮው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር ሠራዊት ካምፕ ጎን የታነፀውን “የኦሮሞ ሰማዕታት” የተሰኘ ሁለት ጭንቅላት ለጭንቅላት የሚፋተጉ ያዘመሙ የአክሱም ኃውልቶች የሚመስሉትን ረዣዥም ምሰሶዎች፣ የእሬቻን ባህላዊ አልባሳት የተጎናፀፉ ኃውልቶች፣ እና “የኢትዮጵያ ሚሌኒየም 2000” ብሎ የሠራውን የቡና ስንጥቅ መሐሉን የሚያሳይ (በባለ 60 ሣንቲም ቴምብርም የታተመለትን) መለያ ምልክት ወይም ሎጎ ማየት ይበቃዋል።

(ድሮ አንዳንድ የአብዮቱ ዘመን ተቃዋሚዎች ደርግ ያሰራውን ረዥሙን የድላችን ኃውልት “የአብዮቱ ብልት” እያሉ ይሳለቁበት እንደነበረው ነፍሱን ይማረውና ያ ጋሽ ስብሃት እየሳቀ ያነሳልን ነበር፤ አሁንም ለሚሊኒየሙ አርቲስት በቀለ የሰራውን የስንጥቅ ቡና ምልክት አንዳንድ አርቲስት ጓደኞቼ ሳነሳባቸው “እእእ… ያ ‘የሚሊኒየሙን ፑሲ’ ነው የምትለን?!” እያሉ ያስቁኝ ነበረ!!

እና ይህ የተከበረ አርቲስት እንዲህ የግርማዊነታቸውን ግርማ ለምን ጨርሶ ገፈፋቸው? ለምን አኮሰመናቸው? አፍሪካን ከራሳቸው በላይ አግዝፈው ታይተውት ይሆን ለአርቲስቱ? አርቲስቱ ቀደም ብሎ በአፍሪካ ህብረት ግቢ የቆመውን የክዋሜ ንኩሩማህን ባለግርማ ሞገስ ወርቃማ የወደፊት ብሩህ ዘመን አመላካች ኃውልት ማየቱ አይቀርም መቼም። እና ያንን ግዙፍ የንኩሩማህ ግርማ ሞገስ ከግርማዊነታቸው ላይ ስለምን መግፈፍ አስፈለገው? በአርቲስቱ ኃውልት ግርማዊነታቸው የለበሱት ካኪ እኮ ራሱ የቀጭን ተጋዳላይ ወይ የቀድሞ መንግሥት የሠራተኛ ማህበር መሪ እኮ ነው ያስመሠላቸው!?! ምነው በቀለ?!

…ወይስ አርቲስቱ ለሞዴልነት የተጠቀመው የንጉሡ ምስል በግርማ ሞገስ ቆመው ከተመላለሱት ቀኃሥ ይልቅ በገዛ ሕዝባቸው ተዋርደው ይገቡበት አጥተው በሞታቸው አፋፍ ላይ በታሰሩበት የክፍለጦር ግቢ ውስጥ በትካዜ ቆመው ለመጨረሻ ጊዜ ቆመው የተነሱትን ፎቶግራፋቸውን ይሆን?!! ግን ለምን?!

ሳስበው… ምናልባት ከብዙ የቀኃሥ የአፍሪካውያን ነፃነት ተጋድሎአቸውን ከሚያሳዩ ነገሮቻቸው ይልቅ ከእኚህ ሰው ለአርቲስቱ ጎልቶ የታየው በጣታቸው ዘወትር የሚሠሩት የዳዊት ኮከብ ምልክት ሳይሆን አልቀረም የሚል ግምትም አሳድሮብኛል በእውነቱ። አርቲስቱ ከሁሉ ነገራቸው በአፅንዖት የቀረፀልንን የዳዊት ኮከባቸውን የመጪው የአፍሪካውያን ብሩህ ዘመን ፅሞናዊ ትንቢታቸው ያረፈበት ታላቁ የግርማዊነታቸው የጃ-ያስተሠርያል መታሰቢያ ሥጦታ አድርገን እንቀበለው ይሆን?!

… በበኩሌ ከአርቲስቱ የግርማዊነታቸው መታሰቢያ ኃውልት ምን መቀበል እንዳለብኝ፣ ምንስ መቀበል እንደሌለብኝ በትክክል አላወቅኩም። ምናልባትም አርቲስት በቀለ መኮንን ይሄንንም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ኃውልት እንደቀደመ አውደ-ጥበቡ – “እንቆቆልሽ” – ለእኛ “ምናውቅልሽ” ብለን እማሬና ፍካሬውን እንድንጠይቅ፣ እንድንፈልግ፣ እንድንመልስ የዘመን የቤት ሥራ እየሰጠንም ይሆን ይሆናል። ያሰበውን እና ያየነውን በየልቦናችን ያሳድርልን ብዬ ከመሠናበት ውጭ የምለው የለኝም።

አርቲስቱን ስለታላቁ ሰው ኮሳሳ ኃውልት (ተጠብቦ ተጨንቆበታልና!) ምስጋናን እና ሂስን ደርቤ በታላቅ መደመም እነሆ በረከት ብዬ ተሰናበትኩ!

ፈጣሪ አምላክ የአፍሪካውን የነፃነት ወላጅ አባት የግርማዊ ጃንሆይን ነፍስ በአፀደ ገነቱ በሠላም ያሳርፍላቸው!

ጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን አብዝቶ ይባርክ!

እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በፍቅር፣ በነፃነት፣ በደስታ ትኑር!

መልካም ጊዜ ለሁላችን።

Filed in: Amharic