>

የፍትህ ስርዓቱ አካሄድ ‘ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’ እንዳይሆን ፈጣን እርምት ያስፈልጋል!

 የፍትህ ስርዓቱ አካሄድ ‘ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’

እንዳይሆን ፈጣን እርምት ያስፈልጋል!

አበጋዝ ወንድሙ

አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ከተሾመ በዃላ አስረግጦ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ሰዎች ጥፋት አጥፍተዋል ወይንም ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ጥርጣሬ መንግስት ካለው፣ ታስረው መረጃ ማሰባሰብ ሳይሆን በቂ መረጃ ከተሰበሰበ በዃላ እንደሚታሰሩና ለፍርድ እንደሚቀርቡ የተናገረው፣ ወሳኝና፣ ሀገሪቱ ህጋዊ ስርዓትን ለመመስረት ለምታደርገው ጉዞ ቁርጠኝነት ያሳየ መልካም ጅማሮ ነው በሚል ተስፋ አሳድሮብኝ ነበር።

ሆኖም ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ ሰዎች ላይ የተመሰረቱ ክሶችና የክስ አካሄዶች ይሄንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ መስለው ታይተውኛል።

የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት 27 ዓመታት እንደ በርካታ አምባገነን መንግስታት የሚታወቀው፣ ህግን የአገዛዝ ስርዓቱ መገልገያ አድርጎ በመጠቀም እንጂ፣ ህጋዊ ስርዓትን በሀገራችን ለማስፈን ባለመሆኑ፣ (ፈረንጆቹ አንደሚሉት rule by law instead of rule of law) በህግ ስም ዜጎች ላይ ለማመን የሚከብዱ ግፍ፣ ስቃይና እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር መንግስት ራሱ ያመነውና፣ አስከፊ ገጽታዎቹን በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን ያስተናገደ በመሆኑ ሁላችንም የታዘብነው ጉዳይ ነው።

ለዚህም ነበር የጠቅላይ ምኒስትሩን መግለጫ ስሰማ ወደ ህጋዊ ስርዓት ለመሄድ መንገድ ይጀመራል የሚል ተስፋ ልሰንቅ ችዬ የነበረው

ሆኖም የዛሬ አምስት ወር የአዲስ አበባ ወጣቶችን ህገወጥ በሆነ መንገድ በጅምላ አፍሶ ጦላይ ስልጠናበመላክ የተጀመረው አካሄድ፣ በሂደት ሌሎች ክሶች ተመስርተው ግልጽነት በሌለው መልክ ሲቋረጡ (ሻሸመኔ ላይ የተለቀቁ አስራ አራት ተከሳቾችና አዲስ አበባ በታላቅ የህዝብ ሃብትና ንብረት ዘረፋ ታሰሩ የተባሉ  ‘ለህዝብ ጥቅም ሲባልየተለቀቁ !!) አንዳንድ በገሃድ ተሰሩ የተባሉ  ወንጀሎችና ግድያዎች  ክስ ሳይመሰረትባቸው በሽምግልና ተቋጩ ሲባል  (ምእራብ ወለጋ) እየሰማንና እያየን ነው።

አሁን አሁን ደግሞ፣ ተጨማሪ ማጣራትና መረጃ  ማሰባሰብ ይቀረናል በሚል ግለሰቦችን አስረው ሲያበቁ ፣ እንደከዚህ ቀደሙ አቃቤ ህግ ተደጋጋሚ የአስራ አራት ቀን ቀጠሮ በመጠየቅ፣ ዳኞችም ተባባሪ በመሆን የተያዘው አካሄድ፣ ነገሮች እንዳልተለወጡ የሚያሳይና የጠቅላይ ሚኒስትሩም ቃል በፍርድቤቶች አካባቢ ሰሚ ጆሮ እንዳልተሰጠው የሚያመላክት ነው።

ይሄ አካሄድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተለውጦ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጠው ቃል መሰረት የህግ ስርዓቱ  መሄድ ካልቻለ፣ ሌሎች የተገቡ ቃሎችም ላይ ጥርጣሬ ስለሚፈጥሩና የሰዎችን እምነት ሸርሽሮ ለለውጡ ሂደት እንቅፋት ስለሚሆን ሳይረፍድ አጣዳፊ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል።

 

Filed in: Amharic