>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1189

"ብርሌ"  (ዳንኤል ክብረት) 

“ብርሌ” 
ዳንኤል ክብረት
……
በአንድ የገጠር ደብር አንድ ታዋቂ ሊቅ ነበሩ፡፡ እኒህ ይህ ቀረህ የማይባሉ ሊቅ ምንም ዓይነት ስሕተት አያልፉም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስሕተቶችን ያርማሉ፡፡ እርሳቸው ለሰው ሳይሆን ለእውነት የቆሙ ነበሩ፡፡ የጎደለ ካለ ይሞላሉ፡፡የተጣመመ ካለም ያቃናሉ፡፡ ታላቅ ነው ብለው አይፈሩም፣ ታናሽ ነው ብለው አይደፍሩም፡፡
.
አንድ ጊዜ አንድ ተምሬያለሁ ያለ #ብርሌ የሚባል ሰው እዚያ ደብር ይቀጠራል፡፡ ታድያ ብርሌ ዕውቀት በዞረበት የዞረ አይመስልም፡፡ ያልተማረውን ሳይሆን የተማረውን መቁጠር ይቀላል፡፡ እንኳን ምሥጢር ሊያደላድል ንባብ አይሆንለትም፡፡ነገር ግን «አላዋቂነትን ምላስ፣ ቁስልን ልብስ ይሸፍነዋል» እንደሚባለው ነገር እንደ ተልባ የሚያንጣጣ ኃይለኛ ምላስ ነበረ፡፡ ለሊቃውንቱ የሚሆን ቢያጣ ለባልቴቶች የሚሆን ነገረ ዘርቅ ነበረውና ሠፈሩን ሁሉ በአንድ እግሩ አቆመው፡፡ ሴት ወይዘሮው ወንድ መኳንንቱ ሁሉ እጅግ ወደደው፡፡ ታድያ ብርሌ ጠዋት ጠዋት የሰው ትኩረት እስባለሁ ብሎ ተአምረ ማርያም ሊያነብ ይነሣል፡፡ ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ «ተአምሪሃ» ይላል፡፡ «ሃ» ን ወደ ላይ እያነሣ፡፡ ሊቁም አትሮንሱ አጠገብ ተቀምጠው «ማርያም አትነሣም፣ ተጣይ
ናት» ይሉታል፡፡ በግእዝ ንባብ ሕግ «ማርያም» የሚለው ስም ሲነበብ ንባቡ ይወርዳል እንጂ አይነሣም ማለታቸው ነው፡፡
.
ብርሌም በአላዋቂነቱ ሳያፍር «አለመማሬ በሕዝብ ፊት ተገለጠብኝ» ብሎ ቂም ይይዛል፡፡ ሊቁ በየጊዜው ንባቡን እያረሙ አስቸገሩት፡፡ ብርሌ ሊቁን የሚበቀልበት ተንኮል ሠራ፡፡ ተአምረ ማርያም ማንበቡን ተወ፡፡ ምእመናኑ ቅሬታ ተሰምቷቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም በየምእመኑ ቤት እየዞረ «እኔ ተአምረ ማርያም ሳነብብ ሊቁ የማርያምን ስም አታንሣ ስላሉኝ ነው» እያለ አድማ ቀሰቀሰ፡፡ የማያስተውል ሕዝብ እና ኮለል ያለ ውኃ በፈለጉት መንገድ ይነዳልና ሕዝቡ በሊቁ ላይ ቂም ያዘባቸው፡፡ አንዳንድ ምእመናንም ለብርሌ «እስኪ እርስዎ ተአምሩን ያንብቡና ሊቁ የማርያምን ስም አታንሣ ሲሉዎት እንስማ» አሉት፡፡ ብርሌም እሺ ብሎ በቀጣዩ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ ተአምረ ማርያሙን አውጥቶ «ተአምሪሃ» ብሎ ንባቡን
አንሥቶ አነበበው፡፡ ሊቁም እንደ ልማዳቸው «ማርያም አትነሣም» ይሉና ያርሙታል፡፡ ብርሌምም ወደ ሕዝቡ ዞሮ «እይውላችሁ ምእመናን ማርያምን አታንሣ እያሉ እኔ ማንበብ አልቻልኩም» አለና ተናገረ፡፡ ሕዝቡም ሆ ብሎ በሊቁ ላይ ተነሣ፡፡ ከደብሩ ካልወጡ ብሎም ዐመፀ፡፡ ሊቁም ማወቃቸው ጥፋት ሆኖ ባልተማሩ እና በማያስተውሉ ሰዎች ግፊት ደብሩን ለቅቀው ሄዱ፡፡
……..
ለመሆኑ እንዴት ነው መስማት ያለብን? የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉስ ትክክል ናቸውን? መምህር ደጉ ዓለም ካሣ «እውነትን የሚያስንቅ ውሸት፣ መውጋትን የሚያስንቅ መሳት አለ» ይላሉ፡፡ ፎርጅድ ብር ከእውነተኛው ብር የተሻለ መልክ
እና ንጽሕና አለው፡፡ ታድያ የዋሓን እንዴት እንለየው? አንዳንድ ጊዜ ለውሸትም ማስረጃ የሚመስል ነገር ሊኖረው ይችላል፡፡ ልቡናን እና አእምሮን ማስተባበር፣ ነገሮችንም ረጋ ብሎ መመርመር ካልተቻለ በግንፍልተኛነት ሊያስወስኑን የሚችሉ ለስሜት ስስ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በተለይም ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ነገሮች #በአላዋቂነት_እርሻ ላይ ከተዘሩ የሚያፈሩት ፍሬ አደገኛ ነው፡፡ በተለይም ለምንወዳቸው ነገሮች ስሜታችን ስስ ነው፡፡ ሰዎችም ይህንን ስስ ብልት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ብርሌ ሕዝቡ ለእመቤታችን ያለውን ፍቅር ነው ለራሱ ጥቅም የተጠቀመው፡፡ ሕዝብ፣ ሀገር፣ ደኅንነት፣ ትዳር፣ ልጅ፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ ኃይማኖት፣ ዓይነት ነገሮች ለነ ብርሌ የተመቹ ናቸው፡፡
.
ከሌሎች ነገሮች ይልቅ ባል ስለሚስቱ፣ ሚስትም ስለ ባልዋ የሚሰሙትን ፈጥኖ ለማመን ቅርቦች ናቸው፡፡ አንዳንድ ፍቅር ጥርጣሬን በውስጡ ያዘለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለነ ብርሌ ያመቻቸዋል፡፡ ሰው የሚያየው ማየት የሚፈልገውን ነው፤ የሚሰማውም መስማት የሚፈልገውን፡፡ በጎ ነገር ለመስማት ራሱን ያዘጋጀ ሰው የሚሰማው ሁሉ በጎ ነው፤ በተቃራኒውም ለክፉ ራሱን ያዘጋጀ ሰው እንዲሁ፡፡ በልጅነታችን ስለ ጅብ እና ጭራቅ ስለሚነገረን በጨለማ ስንወጣ ጎቶውን እና ድንጋዩን ሁሉ ጅብ እና ጭራቅ አድርገን እንስለው ነበር፡፡ በጨለማ ውስጥ ጭራቅ ይኖራል ብለን ስለምናምን ጉቶው ጥፍሩን አስረዝሞ፣ ምላሱን አሹሎ፣ ጥርሶቹን አግጥጦ፣ ዓይኖቹን አፍጥጦ ይታየን ነበር፡፡ ጭራቅ ለማየት #ተዘጋጅተን ነበርና «ጭራቅ እናይ ነበር»፡፡ ሚስቱን ከወንድ ጋር ባያት ቁጥር ለመጠራጠር አስቀድሞ የተዘጋጀ ባል #እውነት_ለሚመስሉ ውሸቶች ተጋላጭ ነው፡፡ ከሚስቱ ጎን የቆመ ወንድ ሁሉ ሲያቅፋት እና ሲስማት ብቻ ነው የሚታየው፡፡ በጣም እንደሚበር መኪና ለመገልበጥ በጣም እንደሚዋደዱ የሚዋደዱ ባል እና ሚስትም ለመጣላት ቅርብ የሆነ የለም፡፡ ጋሽ ግርማ ከበደ «ሰው በሚወድደው ነገር ይፈተንበታል» ይላልና በምንወዳቸው ሰዎች የምንፈተነውን ያህል በምንጠላቸው ሰዎች አንፈተንም፡፡
.
አንድ ሰው ውሳኔው የተስተካከለ እንዲሆን ልቡና እና አእምሮ ያስፈልገዋል፡፡ #ልቡና ሃይማኖትን፣ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን፣ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡ #አዕምሮ ደግሞ ዕውቀት፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ማመዛዘን፣ ማነፃፀር፣ ማዛመድ እና የተጠራቀመ ልምድ የምናገኝበት መዝገብ ነው፡፡ አንድ ሰው ነገሮችን በዕውቀት እና በርጋታ፣ በማመዛዘን እና በትእግሥት የሚመ ዝናቸው ከሆነ ከአስመሳይ ውሸቶች ጀርባ ያለውን እውነት የማግኘት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ እነ ብርሌ ሁለት ነገሮችን በመሥራት የተካኑ ናቸው፡፡ እውነት የሚመስሉ ውሸቶችን እና የተቀናበሩ ውሸቶችን፡፡ አልቅሰው፣ ተቅለስልሰው እና ራሳቸውን አዋርደው የሚናገሩ ሰዎች ድርቅ ብለው ከሚናገሩ ሰዎች ይልቅ ሰዎችን የማሳመን ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሽማግሌዎች፣ ፖሊሶች እና ዳኞች ዕንባ ማፍሰስ በሚችሉ ሰዎች ቶሎ ልባቸው ይሰበራል፡፡ የኔ ቢጤው ፈጣጣ ደግሞ «ዓይነ ደረቅ» ለመባል ቅርብ ነው፡፡
.
ለመሆኑ ግን ነገሮችን #ከማመን ነው ወይስ #ከመጠራጠር ነው መጀመር ያለብን? በተለይም የሌሎች ሰዎችን እንከን በተመለከተ አንዳች ነገር ስናይ ወይንም ስንሰማ፣ ነገሩ የሚያሳምን ነገር እንኳን ቢመስል መጀመርያ ግን ሙሉ በሙሉ ማመን የለብንም፡፡ ለጥርጣሬ ቦታ መኖር አለበት፡፡ በዚያ ወቅት ከሰማነው እና ካየነው ነገር ይልቅ ሌላ ነገር ቢኖርስ? ደግሞስ ባለቤቱ ራሱ የሚነግረን ሌላ ነገር ካለስ? የሆነው ነገር በሌላ ባህል፣ መንገድ፣ እምነት፣ ርእዮት የተለየ ትርጉም ቢኖረውስ? የሚደረገውን ነገር ራሱ ሰውዬው ሳያውቀው እያደረገው ቢሆንስ) ሌሎችም ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ አንድ የሰማሁት ታሪክ አለ፡፡ ከሃያ ዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ ሐበሻ ወገናችን ሚስቱን ገድሏል ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ያ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት በቀረበ ቁጥር አንገቱን እንደ ደፋ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕጉ ብዙ ነገር ይዘረዝርና «ይህ ሰው ከሁሉም በላይ የሠራው ነገር ስለፀፀተው አንገቱን እንደ ደፋ ነው» ይህም የፀፀት ስሜት guilty conscious እንደ ተሰማው ያሳያል» ብሎ ያቀርባል፡፡ዳኛውም አዘውትረው የሚያዩት ነገር ነበርና ይቀበሉታል፡፡ በኋላ ግን ጠበቆቹ በኢትዮጵያውያን ባህል አንገት መድፋት #የጨዋነት እንጂ የፀፀት ስሜት መግለጫ እንዳልሆነ፤ እንዲያውም ባላደረገው ነገር ለዚህ በመብቃቱ ማዘኑን እንደሚገልጥ የባህል ኤክስፐርት አስቀርበው አስመሰከሩ፡፡ዳኛውም በነገሩ ተገርመው ነጻ ለመውጣቱ እንደረዳው ከኢትዮጵያውያን ጠበቆች ሰምቻለሁ፡፡
.
እንደ ብርሌ ያሉት ይህንን አጋጣሚ ለራሳቸው ማስረጃ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ አላዋቂነትን ተንተርሰው ዐዋቂነትን ይከስሳሉ፡፡ አጋጣሚዎችንም ከሁኔታዎች ጋር ያቀናብራሉ፡፡ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያልተወሰነበት ሰው ሁሉ ነጻ ሰው ተብሎ የመታሰብ መብት አለው የሚባለው ይህንን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አስቀድሞ ዳኛው ሰውዬውን ወንጀለኛ #ሊሆን_ይችላል ብሎ በማሰብ ነጻ ለመሆኑ ማስረጃ የሚፈልግ ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ የጠረጠረውና ደስ ያለው ሰው ሁሉ በከሰሰው ቁጥር ነጻ መሆኑን ሲያስረዳ መኖሩ ነው፡፡ የማስረዳት እና የማሳመን ጫናም በከሳሹ ላይ መሆኑ ቀርቶ በተከሳሹ ላይ ሊሆን ነው፡፡ አንዳንድ ተከሳሾች የፀጉራቸው፣ የልብሳቸው፣ የፊታቸው ገጽታ ማኅበረሰቡ ስለ ጨዋነት ከሚሥለው ገጽታ የተለየ በመሆኑ ምክንያት የመጠርጠር እና ሊያደርጉ ይችላሉ የመባል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ምናልባትም የሚናገሩበት የቋንቋ ዘዬ ከተለመደው ጨዋዊ አነጋገር ወጣ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ያን ጊዜ «ይኼማ በደንብ ያደርጋል» የመባል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
.
ልቡና እና አእምሮ ያለው ዳኛ ግን የሚመስለው ነገር ቢያገኝም #ለጥርጣሬው ግን ቦታ ይኖረዋል፡፡ ምናልባት ባያደርግስ? ብሎም ይጀምራል፡፡ በፍትሕ ጉዞ ውስጥ አንዱ አከራካሪ ነገር «ሰውዬው ወንጀለኛ ተብሎ ማስረጃው ነው መፈለግ ያለበት ወይስ ማስረጃው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ሰውዬው ወንጀለኛ መባል ያለበት» የሚለው ነው፡፡በአንዳንዶች ዘንድ መጀመርያ ሰውዬው ተይዞ ነው በሰውዬው ልክ መረጃ የሚፈለገው፡፡ ማስረጃ መፈለግ እና ማስረጃ ማቀናበር ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ በሀገራችን «አንገት ደፊ አገር አጥፊ» የሚል አባባል አለ፡፡ አንገት ደፊ ሰው ጨዋ ነው፣ ምንም ነገር አያውቅም፣ አንገተ ሰባራ ትኁት ነው ተብሎ የመታሰብ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ሰው ጥፋት ቢያጠፋ እንኳን ማንም እርሱ አደረገ ብሎ ለመቀበል ዝግጁ አይደለም፡፡ ማኅበረሰቡ የሚጠይቃቸውን አፍአዊ የጨዋነት መመዘኛዎች ያሟላልና፡፡ በዚህም የተነሣ አንገት ደፊው የፈለገውን ዓይነት ወንጀል ቢፈጽም «ዱርዬ ናቸው፣ አስቸጋሪ ናቸው፣ ጋጠ ወጥ ናቸው» በሚባሉ ሰዎች እየተመካኘ ስለሚኖር በድብቅ አገር ያጠፋል፡፡
.
በሀገራችንም አንድ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ ቡዳ ሰው ይበላል የሚለው ነገር እንዴት እንደ መጣ የሚነገር ታሪክ፡፡ ሰውዬው ደግ ሰው ነበረ አሉ፡፡ ማብላት ማጠጣት የሚወድድ፡፡ ታድያ ሰዎች ይቀኑበት ነበር፡፡ ሁሉ ይወደው ነበርና፡፡ በሬ አርዶ ቅርጫ ባከፋፈለ ቁጥር መግዛት ለማይችሉ ድኾች እርሱ ይገዛና ደብቆ ይሰጣቸዋል፡፡ ታድያ ይህንን የሚያውቁ ምቀኞች የሰው ሥጋ ይበላል ብለው አወሩበት፡፡ ወሬው ውስጥ ለውስጥ ተወራ፡፡ አንድ ቀን ቅርጫ ተከፋፍሎ ሰው ሁሉ የድርሻውን እየወሰደ እያለ የመንደር ውሻ ሾልካ ወደ ጓዳ ትገባለች፡፡ ያ ሰው ይህንን ያይና «ኧረ ያንን የሰው ሥጋ ውሻ እንዳይወስደው» ብሎ ለባለቤቱ ይነግራታል፡፡ ቅርጫ ወሳጁ ሁሉ ክው ይልና በእጁ የያዘውን እየተወ ተጣድፎ ከአካባቢው ይጠፋል፡፡ ከዚያም «የሰው ሥጋ እንደሚበላ ሰማን፣ እኛው በጆሯ ችን ሰማን» የሚሉ ሰዎች አገሩን አጥለቀለቁት፡፡ የርሱ ልጆችም ሰው በላ ቡዶች ተብለው ቀሩ ይባላል፡፡ ይህ አፈ ታሪክ የማኅበረሰባችን ችግር ለመጠቆም የተተረከ ነው፡፡ እውነት ስለሚመስሉ ውሸቶች፡፡ ሰውዬው «የሰው ሥጋ» በቤቱ አስቀምጦ ነበር ወይ? መልሱ «አዎ ነው»፡፡ «የሰው ሥጋ በቤቴ አለ» ብሎ የተናገረ ማነው? ራሱ ሰውዬው፡፡ ነገር ግን «የሰው ሥጋ» የተባለው ባለቤትነትን እንጂ ከሰው አካል የተገኘ ሥጋ መሆኑን አልነበረም የሚያመለክተው፡፡
.
ጥቂት እውነት የመሰለ ነገር በውስጡ ስላለ ነው ሰዎችን ለማሳመን የበቃው፡፡ አጭበርባሪ ነጋዴዎች ሙዝን ከቅቤ ጋር፣ በርበሬንም ከሸክላ አፈር ጋር እንደሚ ያቀርቡት ሁሉ፤ ለነ ብርሌ ሰዎችን ለማታለል ቀላሉ ዘዴ #ጥቂት_እውነት የተቀላቀለበት ውሸት ማቅረብ ነው፡፡
————–
መልካም ቀን!
Filed in: Amharic