>

በአንድ ነገር ትልቅ አክብሮቴን ለትሁቱ አብርሃ ደስታ ሰጠሁት [ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

Abrha desta 1አብርሃ ደስታን በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወኩት ባለፈው ዓመት ፒያሳ አከባቢ ነበር፡፡ አብርሃ እና የቅርብ ጓደኛ የሆነው ፖለቲከኛ እና ደራሲ አስራት አብርሃ ፒያሳ መብራት ሃይል ፊትለፊት በሚገኘው መንገድ በእግራቸው ረጋ ብለው በመራመድ ቁልቁለቱን ወረድ እያሉ አገኘኋቸው፡፡ ከአስራት ጋር ሰላም ተባባልን፡፡ አስራት ‹‹አብርሃ ደስታ ነው፣ ተዋወቁ›› አለኝ፡፡ በእጅ ሰላምታ ሰላም ተባባልን፡፡ አብርሃን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች እና በተለያዩ የህትመት ውጤቶች በሚጽፋቸው በርካታ ጽሑፎች በፎቶ ግራፍ አውቀዋለሁ፡፡ በዚያን ዕለት ትልቅ ቦርሳ ከጀርባው ሸክፏል፡፡ ሲናገርም በጣም በትህትና ነበር፡፡
ከወራቶች በፊት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ማከላል ታሪካዊ ሁነትን በመረጃ በማስደገፍ በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እና የውይይት መድረክ ላይ አብርሃ ደስታን በማድነቅ ‹‹ከአይን ያውጣው›› በማለት ሲናገሩለት በቦታው ተገኝቼ አድምጫለሁ፡፡…የተወሰኑ ቀናቶችም ለመጽሔት ሥራ አብርሃን በስልክ ሳነጋግረው ምላሾቹ ሁሉ በትህትና የተሞሉ ነበሩ፡፡
ዛሬ አብርሃ ደስታ በእስር ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አብርሃ በአንድ ነገር በጣም ይገርመኝ ነበር፡፡ ፕሮፍ መስፍን በ83 ዓመታቸው ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ ታከተኝ ሳይሉ በፋክት መጽሄት ላይ አምደኛ በመሆን በየሳምንቱ መጻፍ መቀጠላቸውን በማየት ትልቅ አክብሮቴን እንደሰጠኋቸው ሁሉ አብርሃም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ ታከተኝ ሳይል ዘወትር ቁጥራቸው በዛ ያሉ አጭር፣ መካከለኛ እና ረዥም ጽሑፎችን በሶሻል ሚዲያ የሚያስነብበን ጠንካራ እና ደፋር ኢትዮጵያዊ ወገናችን ነው፡፡ እናም ዛሬ ለአብርሃ ደስታ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ትልቅ አክብሮቴን ልገልጽለት ወደድኩ፡፡
አብርሃ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ፣ ስለተፈጠሩ ችግሮች፣ እየተደረጉ ስላሉ ሁነቶች፣ ስለመልካም አስተዳደር እጦቶች፣ አረና ፓርቲ በሚደርጋቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ስለሚደርስበት ወከባ እና ተግዳሮት፣ ስለሰላማዊ ሰልፎች መከልከል/ አለመከልከል፣ በቅርቡ በሽብር ወንጀል ተጠርጥራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለዋለቸው አንዲት የልጆች እናት የእስር እና የፍርድ ሂደት ሁኔታ፣ መድረክ በአዋሳ ያደረገው ሰልፍ የገጠመውን ፈተና …ወዘተ ወዲያው ወዲያው በግል ተነሻሽነት መረጃ ይሰጠን ነበር፡፡ይህ ሳይታክቱ መረጃዎችን የመስጠት ልምድ ብዙ ሰዎች ላይ አይታይም፡፡ የአብርሃ ደስታን ሳይታክቱ የመጽሐፍ እና መረጃ የመስጠት ልምዱን ከልቤ አከበርኩለት፡፡ በታሰረበት ቦታ ፈጣሪ ይጠብቀው፣ ብርታትንም ይስጠው! ሌላ ምን ልበል ወዳጆቼ?
በእሱ አባባል፣

It is so!

 

 


 

Filed in: Amharic