>
5:13 pm - Thursday April 20, 2817

ከአዲስአበባ ምጽዋ የባቡር መስመር ሊዘረጋ ነው!!! (ኢዜአ)

ከአዲስአበባ ምጽዋ የባቡር መስመር ሊዘረጋ ነው!!!

 ኢዜአ

አዲስ አበባን ከኤርትራዋ ምፅዋ ጋር ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥናት ወጪ ለመሸፈን የጣሊያን መንግስት መስማማቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

በጣሊያን ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተወያይተዋል።

መሪዎቹ ከውይይቱ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጣልያን አዲስ አበባን ከምፅዋ ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ጥናት ወጪ ለመሸፈን ተስማምታለች።

ከጥናቱም በኋላ በሚገኘው ውጤት በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ጁሴፔ ኮንቴ እንደገለጹላቸውና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ እንደ ስሟ እንድትሆንና ነዋሪዎች ወጥተው ሲገቡ የሚዝናኑበትን ቦታ ከመፈለግ አንጻር በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች የተወሰነ ቦታቸውን ለህዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲያውሉ ጥያቄ ቀርቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጣልያን መንግስትም ለዚህ ቅን ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ ቤተ መንግስቱን ግማሽ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ለተቸገሩ ወገኖች ምግብ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ጣልያን በመዲናዋ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣልያን ቆይታቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በልማትና በሰላም ውይይቶች እንዳደረጉና ከአቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ያደረጉት ሁለገብ ምክክርም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ ልማትና አንድነት እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጣሊያን መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ዶክተር አብይ አመልክተዋል።

ዛሬ የተደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚካሄዱ የሁለትዮሽ ውይይቶች አገራቱ በሰላም፣ በልማትና በቱሪዝም ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል። አገራቱ ለጋራ እድገትና ሰላም በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በአጠቃላይ ከልዑካን ቡድኑ ጋር በጣልያን የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። “እንደ ወንድም አገርና እንደ ጠንካራ ወዳጅ ከምናያት ከጣልያን የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጄሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸውና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመስራት መግባባታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎች የጣሊያን መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጣልያን ጉብኝት ያደረጉት የጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባረደጉበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ዳ ሲልቫና ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር ተወያይተዋል።

በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጓዘው የልዑካን ቡድን በሮም ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽነር አበበ አበባየሁን ያካተተው የልዑካን ቡድን ለባለሃብቶቹ ሃገሪቱ ስላላት የተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎችና አማራጮች ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ካርቪኮ ግሩፕ በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን እያጠናቀቀ ሲሆን፥ በጣሊያንና በቬትናም በሚገኙ ፋብሪካዎች የሰራተኛ ስልጠና በማድረግ ዝግጅቱን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

በውይይቱ የተገኙት ሌሎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመድሀኒት፣ በግንባታ፣ በግብርና ማቀነባበርያና አልባሳት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጣልያን ቆይታው በኋላ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።

Filed in: Amharic