>

የአድዋ ተጓዦች!!! (ያሬድ ሀይል ማርያም)

የአድዋ ተጓዦች!!!
ያሬድ ሀይል ማርያም
ዘረኝነትን ለመቃወም፣ ፍቅርን እና አንድነትን ለመስበክ እና ለማስተማር፣ እኩልነትን ለማንገስ እና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ከአድዋ የተሻለ እድል የለም!!!
 
በመጀመሪያ ይህን ድንቅ ፎቶ ያነሳውን ሰው ለማመስገን እወዳለሁ። ፎቶው እጅግ ውብ ከመሆኑ ጀርባ ያለው ዝርዝር ታርክ ደግሞ የበለጠ ገለጭ አድርጎታል። የአድዋን ድል ለማክበር፣ ለዛ ድል ያበቁንን አባቶች ለማስታወስ በታላቅ መንፈሳዊ ብርታት፣ ቅንነት እና ፍቅር የተሞላ ታሪክ ዘካሪ ጉዞ። ፎቶውን ሳይ አንድ ነገር ተመኘሁ። ይህን የእግር ጉዞ ሰልፍ በሚሊዮኖች ሆነን እና እደሰንሰለት ተቀጣጥለን የምንጓዝበት ቀን ናፈቀኝ። ሰልፉን በሚመራው የመጀመሪያው ሰው እና ሰልፉን በሚከተለው የመጨረሻው ሰው መካከል ያለው ልዩነት ብዙ ከተሞችን እና ክልሎችን ተቀጣጥሎ ያዳረሰ ሰልፈኛ።
በቅርቡ በደቡቡ የሕንድ ግዛት ኬራላ በሚባል ስፍራ የሚኖሩ ሴቶች የጽዖታ እኩልነት ይከበር በሚል እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል እና ትንኮሳ ለመቃወም እጅ ለእጅ ተያይዘው እና ተቀጣጥለው 620 km እርዝመት ያለው ሰልፍ አድርገዋል። በዛ እርቀት ውስጥ ባሉ ሥፍራዎች ሁሉ መልዕክታቸው በአንድ ጊዜ ተሰምቷል።
እኛም ዘረኝነትን ለመቃወም፣ ፍቅርን እና አንድነትን ለመስበክ እና ለማስተማር፣ እኩልነትን ለማንገስ እና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ከአድዋ የተሻለ እድል የለም።
በቀጣዩ አመት በዚህ መንፈስ ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት የእግር ጉዞ ቢሆን በተመሳሳይ ሰዓት እና ደቂቃ ውስጥ የሰልፉ አንድ ጫፍ አድዋ፤ ሌላኛው ጫፍ ደግሞ ከመነሻው አዲስ ሆኖ የአለምንም ትኩረት ሊስብ የሚችል የአንድነት ቀን ይሆናል።
የመጨረሻው ሰልፈኛ አድዋ ሲደርስ የመጀመሪያው ሰልፍ መሪ አዲስ አበባ ተመልሶ ይገባል። አላማው አንድም አድዋን ማሰብ እና የታሪክ ባለውለተኞቻችንን ማስታወስና መዘከር ነው። ሁለትም በመካከላችን ያለውን የዘር እና ሌሎች የመጋጫ ልዩነቶቻችንን አጥብበን እንደ አንድ አገር ልጆች ተከባብረን እና ተሳስበን የምንኖረባትን ኢትዮጵያን ሰፊ ቤት ለማድረግ በጋራ ቃል ኪዳን የምንገባበት ጉዞ ይሆናል። አዘጋጆቹም ቢያስቡበት መልካም ነው።
ክብር ለአድዋ ሰማዕታት!
አድናቆት ለአድዋ የእግር ተጓዦች!
Filed in: Amharic