>

አገራችን ዛሬ የሚያስፈልጋት አጼ በክንዱ የሆነ መንግሥት ነው!!! (ዉብሸት ሙላት)

አገራችን ዛሬ የሚያስፈልጋት አጼ በክንዱ የሆነ መንግሥት ነው!!!
ዉብሸት ሙላት
ተክለጻድቅ መኩሪያ ስለ ግራኝ በጻፉበት የዳጎሰ መጽሐፋቸዉ ላይ በመግቢያነት ያዘጋጁትን ክፍል ሲያጠናቅቁ የመጨረሻዉ አንቀጽ ላይ ስለ ‘ዐጼ በክንዱ’  በማዉሳት ነዉ፡፡ ዐጼ በክንዱን እንዲህ ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡ 
 
“የዓፄ በክንዱ ትርጓሜ በራሱ ክንድ የሚተማመን ኃይሉ ከራሱ የሚመነጭ ትጥቁን ራሱ የሚያደረጅ የጥንቱና የመካከለኛዉ ዘመን ጎልማሳ ባሁኑ ጊዜ የ፫ሺ ዓመት ዕድሜዉን የሚቆጥር ዘወትር የሚታደስ የአዛዉንት ወጣት፣ዕድሜዉን ሙሉ ዓለምን ለወረሩ ቄሳሮች ያልተንበረከከ ራሱ በቤቱ ሰዉነቱን የማያስደፍር ክብሩን የማያስገስስ ቄሳር ነዉ፡፡”
 
 ይህ መጽሐፍ የታተመዉ በ1966 ዓ.ም. ነዉ፡፡ በወቅቱ ዐቢዮቱ እየመጣ አፋፍ ላይ ደርሷል፡፡ የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ እና ሌሎቹንም ሕዝባዊ የለዉጥ ፍላጎትና የዐጼ ኃይለ ሥላሴን አስተዳደር ገፍትሮ ለመጣል ጫፍ ላይ የተደረሰበት ወቅት መሆኑን ተክለጻዲቅ መኩሪያ በመገንዘብም ጭምር ነዉ የመጽሐፉን መግቢያ ያሰናዱት፡፡ 
 
የተክለጻድቅ መኩሪያ ስለ ዐጼ በክንዱ ማዉሳት የመጣዉም በዚያን ወቅት የተገነዘቡትን የሰላም ሁኔታ በምን አካሄድ ማስተካከል ይቻላል ለወደፊትስ ምን መደረግ አለበት የሚለዉን ሲመክሩ ነዉ፡፡ ለምክራቸዉ መነሻ የሆነዉ የዐጼ ልብነ ድንግልን በኢማም አህመድ (ግራኝ) እንዴት እንደተሸነፈ ከፈተሹ ካስረዱ በኋላ ነዉ፡፡ 
 
አሁንም ያለንበት አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ዐጼ በክንዱ የሆነ መንግሥት የሚያስፈለግበት ወቅት መሆኑን ነዉ፡፡ ለዚህ ዐዉድ ዐጼ የሚለዉ የፌደራልም ይሁን የክልል መንግሠትን ሊወክል ይችላል፡፡ የፌደራሉም መንግሥት በራሱ ኃይል መተማመንና አገር የሚያተራምሱ ቡድኖችን በክንዱ ሥር ማስገባት አለበት፡፡ በኦሮሚያ ክልል ወታደራዊ ሥልጠና የሚሰጥን፣የአገሪቱን ገንዘብ ከየባንኩ በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፍን፣ሕጻናትን ለወታደርነት የሚመለምልን፣ወንጀል ሠርቶ መቀሌን ምሽግ ያደረገን፣ አገር በማተራመስ ተግባር ላይ የተሰማራን ቡድን በክንዱ ሥር የማስገባት ዐቅምና ችሎታ መኖር እንደማለት ነዉ ዐጼ በክንዱ፡፡ አይደለም ከዉስጥ ያሉ ቡድኖችን ይቅርና ከዉጭ ሊመጡ የሚችሉ ጠላቶችን የሚመክትም የሚደፍቅ ኃይልም መኖርን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ 
 
ይህ ሁኔታ ለአማራ ክልል መንግሥትም ይሠራል፡፡ የክልሉ መንግሥት በራሱ የአስተዳደር ወሰን ዉስጥ ያሉትን ሁኔታዎች በትክክል መቆጣጠር ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር እንዳይከሠት መከላከል ፣ከተከሠተም በፍጥነት መቋቋም የሚችልና ብሎም እንዲህ ዓይነቱን ቡድን በክንዱ መደቆስን ያመለክታል፡፡ 
 
 በአማራ ክልል በተለይም በማእከላዊና በምእራብ ጎንደር ሕዝብን ለሞት፣ለስቃይ፣ለጉዳት የዳረጉ አስነዋሪ ተግባር እንዳይፈጠር አስቀድሞ መሥራት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ያ ባይሆን እንኳን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ማዋል ነበረበት፡፡ ከፌደራል መንግሥትም ቢሆን ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል በመጠየቅ ብሎም በክልሉ ፖለስ አመራር ሥር ሆነዉ እንዲመሩ በማድረግ (ለተጠያቂነተም ለዉጤታማ አመራርም በሕግም አሠራሩ እንዲሁ እንዲሆን ስለሚጠይቅ) በአፋጣኝ ሁኔታዉን እልባት መሥጠት መቻል ነበረበት፡፡ አልሆነም፡፡ 
 
መንግሥትነት የሚያስተዳድረዉን ወሰን በብቃትና በትክክል በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ እያንዳንዷን የጸጥታ ሥጋት የሕዝብን ደኅንነነት አደጋ ላይ የሚጥል አጋጣሚን አስቀድሞ ገምቶ (ዐዉቆ) የሚከላከል፣ካልተቻለ ደግሞ ችግሮቹን ለመፍጠር ሲሞከር ወይም ሲፈጠሩ በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችል መሆን አለበት፡፡
 
ይሁን እንጂ፣ የክልሉም መንግሥት እንደማንኛዉም ዝርዝር መረጃ እንደሌለዉ ተመልካች ሕዝብ ሐሜትና አሉባልታ እንዲሁም መረጃን መሠረት ያላደረገ ግምት በመጠቀም እንዲህ ዓይነት ቡድኖች እንዲህ ዓይነት አተራማሾች ወዘተ በማለት ተጠምዷል፡፡ መሆን የነበረበት መረጃን መሠረት ያደረገ እንትና እንቶኔ በማለት ለይቶ በመግለጽ እርምጃ መዉሰድ ነዉ፡፡ ይህን ለማድረግ የተለያዩ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ዘዴዎችን መጠቀም ነዉ፡፡ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር የቴሌና የኢንተርኔት መረጃዎችን መሰብሰብ ነዉ፡፡ ይህን ለማድረግ ወራት መፍጀትም የለበትም፡፡ 
 
አሁን ላይ የፌደራሉም ይሁን የሌሎች ክልል መንግሥታት በተለይ ደግሞ የአማራ ክልል ዐጼ በክንዱ ሆኖ የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡ ሕዝብን ለአደጋ አጋልጦ ነገር ግን እዚህ ግባ የሚባል መንግሥታዊ ግዴታዉን መወጣት አቅቶት ወይም በቀዘዝተኛነት ተቀምጧል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሕዝብ ዕለት ዕለት እየሞተ ነዉ፡፡ እየተፈናቀለ ነዉ፡፡ ሃብትና ንብረቱ እየወደመ ነዉ፡፡ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡትን መፍትሔ መስጠት ያቃተዉ የፌደራልና የክልል መንግሥት ነዉ ያለዉ፡፡ ይኼዉ ትላንትና እና ዛሬ ደግሞ አራት ሺ የሚጠጋ ሰዉ አዘዞና አይምባ ላይ ሰፍሯል፡፡ 
 
“ሞትን ጦርነትን እክልላችሁ እናመጣላችኋለን” ያለን አካል ይህን ጦርነት ሲያመጣለት አንቀላፍቶ የተኛ ብሎም ሕዝብን ለዚህ ሁሉ ሥቃይ እንዲገባ መንግሥትነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ ዐጼ በክንዱ ሁናችሁ ሕዝቡን ከገዳይ ከአፈናቃይ ታደጉት፡፡ ከላይ ለዐጼ በበክንዱ በተሰጠዉ ብያኔ ማገባደጃ ላይ የሚታደስ የአዛዉንት ወጣት መሆን እንዳለዉ ቄሳሮች ሆይ ክንዳችሁን ሕዝብን እየገደለ እያፈናቀለ ያለዉ ቡድን ላይ በማሳረፍ ሕዝብን አድኑ፡፡ ካልሆነ እራሳችሁንም ማዳን ይሳናችኋል፡፡ ሞት እናንተዉ ጋር ይመጣል፡፡ የተክለጻዲቅ መኩሪያ ምክርን ያልሰሙት (የዘገየ ነዉ ሊባል ቢችልም) ወዲያዉኑ ዐብዮቱ ፈንድቶ ጃንሆይንም ስንቱን መሳፍንትና መኳንንት ዓመት ሳይሞላ ደርግ ጨረሳቸዉ፡፡ ሕዝብን ይቅርና እራሳቸዉም በጅምላ ወደ ሞት ተጓዙ!
Filed in: Amharic