>
5:14 pm - Sunday April 20, 4769

አባ ዶዮን የሜጫ ኦሮሞ ህዝብ ‹‹የሰላም አባት››  (በፍቅረ ማርቆስ ደስታ) 

አባ ዶዮን የሜጫ ኦሮሞ ህዝብ ‹‹የሰላም አባት›› 
ፍቅረ ማርቆስ ደስታ 
 
 የሌተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ የአጎት ልጅ የነበሩት አባ ዶዮ ዋሚ ናቸው። “ጃጋማ ኬሎ – የበጋው መብረቅ (የሕይወት ታሪክ)” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ስለሳቸው ከተጻፈው ታሪክ ይህንን ላካፍላችሁ :-
——-
አባ ዶዮን የሜጫ ኦሮሞ ህዝብ ‹‹የሰላም አባት›› እንዲላቸው ያደረገው ተግባር ጣሊያኖች በከፋፍለህ ግዛ መርህ የህዝቡን አንድነት ለመበታተንና እርስበእርስም ለማፋጀት ያቀዱትን የዘር ልዩነት እሳት በማጥፋታቸው ነው፡፡
ይህም የኢጣሊያን ዕቅድ በእልፈታና ጀልዱ በመጠኑ ተፈጽሟል፡፡ በሜጫ ግን እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የሃገር ሽማግሌዎች ‹‹ከባላባቱ ከአባ ዶዮ ጋር እንምከርበት›› ይሉና አባ ዶዮ ቤት ለመገናኘት ይወስናሉ፡፡ አባ ዶዮም ስለ ዕቅዱ የሰሙ ቢሆንም በቀጠሮው ይስማማሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ ደግሞ የብልሁንና በህዝቡ የተከበሩትን የአባ ዶዮን ምክርና ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ተማምነዋል፡፡
የቀጠሮው ዕለት ሽማግሌዎች ወደ አባ ዶዮ ቤት ሲገቡ በሩ ላይ ቆመው የሚቀበሏቸው አባ ዶዮ ሽማግሌዎቹ በስልቻ ከተቀመጠው ሰርገኛ ጤፍ እየዘገኑ እንዲገቡ አደረጉ፡፡ እንግዶች በሙሉ መግባታቸውን ሲያረጋግጡ አባ ዶዮም ገቡ፡፡ አንደገቡ ሁሉም በእፍኛቸው ሰርገኛ ጤፉን እንደያዙ አዩ ……….
‹‹አባ ዶዮ! ምን አርጉት ብለህ ነው ሰርገኛ ጤፍ ያሳፈስከን?›› አሉ ሽማግሌዎቹ፡፡
‹‹በሉ ስብሰባችን ከመጀመሩ በፊት ነጭና ጥቁሩን ለዩልኝ›› አሉ አባ ዶዮ ኮስተር ብለው፡፡
‹‹አይ አባ ዶዮ! ትቀልዳለህ እንዴት ተደርጎ ነው ጥቅርና ነጩ የሚለየው የማይቻለውን ምነው ቀለድህብን አሉ በአንድንት፡፡
‹‹ በሉ ይቅር በሉኝ! ካስቸገራችሁ ተውት›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
ከዚያም ሚስታቸው ያዘጋጁት ምሳ ቀረበ፡፡ አባ ዶዮና ባለቤታቸው በማስተናገዱ ተፍ ተፍ ብለው ጨዋታው ደርቶ ተበላ ተጠጣ በመጨረሻም ሞሰቡ ተነሳ፡፡
‹‹በሉ ወደ ጉዳያችን እንግባ ስብሰባችን ስለምን ነው?” አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹አይ! ጣሊያን ከአማራ ነፃ የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው ብሎናል፡፡ እልፈታና ጀልዱ አማራን እያባረሩ የሚያንገራግሩትንም እየገደሉ ነው፡፡ እኛ ግን ከእርምጃችን በፊት ለአንተ እንንገርህ ካንተ ጋራም እንምከር ብለን ይኸው እንገናኝ አልንህ›› አሏቸው፡፡
‹‹ማለፊያ ሃሳብ ነው!›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹ጣሊያን ከባህር ማዶ መጥቶ ከአማራ ነፃ ሊያወጣን ነዋ! ጥሩ ነው በሉ መጣው ›› ብለው ወጡና ‹‹ልጆች! አሰፋና ካሳን ባስቸኳይ ጥሩልኝ›› ብለው ተመለሱ፡፡ አሰፋና ካሳም የአባታቸውን እግር ተከትለው ከተፍ አሉ፡፡
‹‹አማራን እንግደል ብላችሁ አይደል የመጣችሁ››
‹‹አዎ!›› ሽማግሎቹ ትንሽ ግራ ተጋብተው ተያዩ፡፡
‹‹በሉ ወደ ውጭ ሳንወጣ በፊት እነዚህን ልጆቼን ቀጥለን ደግሞ እናታቸውን እንግደላቸው›› አሉ አባ ዶዮ ጎራዴያቸውን እየመዘዙ….
‹‹ምነው ጌታዬ! ለምን የአንተን ልጆች እንገላለን!›› ብለው ጠየቁ
‹‹እህ! አሁን ምሣ አብልታችሁ የወጣችው እናታቸው እኮ የመንዝ አማራ ናት፡፡ ልጆቹም በአባታቸው ኦሮሞ ቢሆኑም በእናታቸው አማራ ናቸው፡፡ አማራን መግደል ማባረር ካለብን ከዚህ እንጀምራ›› አሉ አባ ዶዮ፡፡
‹‹ይህማ እንዴት ይሆናል አናደርገውም›› አንተስ እማናደርገውን ለምን ትጠይቀናለህ! ›› አሉ ሽማግሌዎቹ
‹‹እህ! ምን ላርግ? ቅድም ‘ሰርገኛውን ጤፍ’ ለዩ ያልኳችሁ እኮ ለዚህ ነው፡፡ አማራና ኦሮሞ እንደሰርገኛው ጤፍ ተቀላቅሏል ወንደሞቼ እዚህ ከናንተ ውስጥ ከአማራ ያልተጋባ ካለ ይንገረኝ? በተለይ ከሸዋ አማራ ጋር ተቀላቅለናል እኛ ኦሮሞዎች ጣሊያን የማያውቀው የማይገምተው የሚያኮራ የ‹‹ጉዲፈቻ›› እና የ ‹‹ሐርመ ሆዳ›› (ጡት መጥባት) ባህል አለን በዚህ ባህላችን ከተለያዩ ጎሳዎች ከመጡት ጋር አንድ ሆነናል፡፡ ይህ ባህላችን ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአንድንትና የአብሮ መኖር መሰረት ነው፡፡ ስለዚህ ጣሊያኖች ተለያዩ ቢሉን እኛ እንዴት መለያየት እንችላለን አሉ አባ ዶዮ ግራ ቀኙን በአይናቸው እየቃኙ፡፡ ሽማግሌዎች የአባ ዶዮ ሃሳብ ስላሳመናቸው በፋሽስቶች የተቀነባበረው የመተላለቅ ድግስ ተበላሸ ፤ የአባ ዶዮ ምሳሌም በህዝቡ ህሊና የማይረሳ የሰላም መላ ተደርጎ እስካሁን ይታወሳል፡፡”
****
During the short Italian occupation of Ethiopia from 1935-41, the Italian colonizers used divide & rule ; divide & conquer tactics to control the diverse Ethiopian population. They have tried in many parts of Ethiopia to create conflicts mainly between the Oromo & Amhara people. They use to tell the Oromo people that the Amhara’s were their enemies who were prepared to attack them. One day, the colonizers approached Abadoyo Wami of Ginchi, as Chieftain, Abadoyo was asked for his blessing of their planned preemptive retaliation on Amhara’s. Before answering their request, he asked each to pick up a handful of red, white & black “teff” at his door and requested they make a single pile. Once they settled before him, Abadoyo asked them to first separate the tiny grains of teff by color, which they obviously could not. Abadoyo then summoned his Amhara wife and children, gave one of the Oromo man a rifle with instructions to kill his wife and the kids. They obviously did not. Abadoyo then explained that their request to kill Amharas was as absurd as separating the teff. Just as the grains of mixed teff can not be separated, he stated, it is the same with us Ethiopians. We are mixed, can no longer be separated. This is a true story happened more than 70 years ago. For more on Information on Aba doyo please read “Yebegaw Mebrek- biography of General Jagema Kello” By Fekere Marqos Desta.
Filed in: Amharic