>
5:13 pm - Sunday April 20, 5270

ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ..... (በኤርሚያስ ቶኩማ)

ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ
 እናቴም ልጅ የላት ለእኔም ወንድም የለኝ!!!
ኤርሚያስ ቶኩማ
በአገምጃ ሶዶ(ወሊሶ) በሚባል ቦታ በነሀሴ ወር 1854 ዓ.ም ተወለዱ ባልቻ አባ ነፎሶ በእናታቸው ጉራጌ በአባታቸው ኦሮሞ ሲሆኑ ገና በልጅነት እድሜያቸው በጦር ሜዳ ተገኝተው ነበር
የምኒልክ ጦር አሸንፎ ለምኒልክ ስለ ምርኮኞች ና ስለሞቱት ሰዎች ሲነገሯቸው ..ከእነዚህ መሃል ብልቱ ተቆርጦ የተገኘበት ብላቴና መኖሩን ሲነገራቸው አፄ ምኒልክ እጅግ አዘኑ አፄ ምኒልክም ባልቻ ሊያሳድጉት በኃላፊነት ወደ አዲስ አበባ ይዘውት ሄድ.።ባልቻ በቤተ መንግሥት ውስጥ በጦር ሙያ ተኮትኩቶ በጎልማሳነቱ የመድፍ ተኩስ ተምሮ ለአፄ ምኒልክ ከፈረንሳይ ሀገር የተሰጣቸው መድፎች የሚተኩስ የሚያስተኩስ ጎበዝ ጀግና ሆነ ባልቻ….. ኢትዮጵያ ከጣልያን 1888 ዓ.ም ባደረገችው ጦርነት የጣልያንን ጦር በርቀት በመምታት ባልቻ ጀግንነቱን አሳየ.ከአድዋ ድል በኃላ ስማቸው በወርቅ ከተፃፈላቸው ጀግኖች መሃል ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አንዱ ናቸው።
ከአድዋ ድል በኃላ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በምኒልክ ዘመን የመድፈኛ ክፍል ኃላፊ የጦር መሳርያ ና የግምጃ ቤት ሀላፊ ሆነው የኢትዮጵያ ጦር መሳርያ በየአይነት ዓይነቱ ማስቀመጣቸው ይታወቃል። ደጃዝማች ባልቻ በእድሜ በዕውቀት ሲጎለብቱ ሲዳሞን እንዲያስተዳድሩ ተደርገ። ከዚያን በኃላ የሃረር ገዢ ሆነው ሐረርጌን እንዲያስተዳድሩ በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ። ተፈሪ ከሲዳማ ማዶ ያለው የጊሚራ መሬት እንዲያስተዳድር በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ። ልጅ እያሱ ይህንን ያደረጉት ከመጀመሪያ በተፈሪ ና በባልቻ መካከል ቅሬታ በመፈጠሩ ተራርቀው እንዲገዙ ነበር. ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ሐረርጌን ለአራት አመታት አስተዳድሩ. በዚህ መሀል ተፈሪ ደግሞ የአባቴን ሀገር ሐረርጌን ላስተዳድር የሚል ጥያቄ ለእቴጌ ጣይቱ አቀረቡ? ወደ ሲዳማ ሳይጓዙ አ.አበባ ተቀመጡ።
ተፈሪ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ተብለው ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድሩ ሲሾሙ ከደጃዝማች ባልቻ ጋራ ቅሪታ ተፈጠረ በኃላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደጃዝማች ባልቻን አባ ነፍሶን ከአገር አስተዳዳሪነት ሹመት አነሷቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለባልቻ አባነፍሶና ለበላይ ዘለቀ ከፍተኛ ጥላቻ እንደነበራቸው ብሎም ከእርሳቸው ውጭ የሌላ ኢትዮጵያዊ ስም ሲጎላ ይናደዱ እንደነበር ስለሀይለስላሴ የተፃፉ መጽሐፍት ያስረዳሉ። ከንጉሥ ጋራ ወደ ሌላ ፀብ መግባት ያልፈለጉት ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ከዘመዶቻቸው ሀገር ከእነ ሙሉ ክብራቸው ተቀምጠው የተጣላውን እያስታረቁ እስከ ሁለተኛ የጣልያን ወረራ ዘለቁ። 1928 አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ በጣልያን አገዛዝ ስር ወደቀች ንጉሡም ሸሽተው ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበሩም። ጣልያን ኢትዮጵያ በድጋሚ ስትወር ደጃዝማች ባልቻ ከንጉስ ጋራ ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣልያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣልያኖች አሰቡ።
ደጃዝማች ባልቻ በንጉሱ ላይ ቅሪታ ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ ሌላ ድርድር መግባት አልፈለጉም ስለሆነም ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ እናም ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀና አቡነ ጴጥሮስ ጋራ ስለ ጦርነቱ የሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ። ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አምስት ሺ ጦራቸውን ይዘው በ79 ዓመታቸው ከትውልድ መንደራቸው ከአገምጃ ሶዶ ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ ከዛም ረጲ ተራራ ላይ ሆነው መድፋቸውን ጠምደው የሌሎችን አርበኞች መልዕክት ይጠባበቁ ጀመር። የባልቻ ሰላይ የነበሩት በባንዳ ተይዘው ሲገደሉ ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻ ጦር እየተከተሉ በጣም ብዙ ሰው ፈጀባቸው። በህይወት ዘመናቸው ጣልያንን 2 ጌዜ የተዋጉት ብዙ ሺ ወታደር የነበራቸው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ብቻቸውን ቀሩ። ባልቻ 2 ወንድም ነበራቸው ፊታውራሪ ገብረ መድህን እና ፊታውራሪ ሳህለሚካሄል ሁለቱም በጦርነት ተማርከውና ተገለዋል። እንዲህ አሉ ባልቻ
…ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ እናቴም ልጅ የላት ለእኔም ወንድም የለኝ።
 የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወደሚኖርበት እስከ ጉራጌ አገር ድረስ በመዝለቅ በእሳቸው ላይ ዘመተባቸው ህዝቡም ከዳቸው ወታደሮቹም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሿቸው ደጃዝማች ባልቻ ሁለቱ አሽከሮቻቸው ከእሳቸው ጋራ 3 ሰው ብቻ ቀረ ብዛት ያለው የጣልያን ጦር ከበባቸው ወዴትም መሄድ አልቻሉም ። በመጨረሻም እጅህን ስጥ መሳሪያክን ጣል ብሎ ጣልያኑ ሲያዛቸው ደጃዝማች ባልቻ እኔ እጄን የምሰጥ ሰው አይደለሁም ..ትጥቄን አልሰጥም ብለው ነጩን ጣልያን ገድለው በራሳቸው ጥይት የራሳቸውን ህይወት አጠፉ።
እጃቸውን እንካን ለጠላት ሳይሰጡ በራሳቸው ሽጉጥ ጥቅምት 27 1929 ዓ.ም ተሰው። ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በአካል ጉድለት ምክንያት ልጅ ወልደው ዘራቸውን ባይተኩም የጀግና ውለታ የማይረሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጃቸው ሆኖ ታሪካቸውን ሊዘክር ይገባል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በስማቸው መንገድ ሆስፒታል ትምህርት ቤት ከተሰራላቸው ጀግኖች መካከል ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ይገኛሉ። ክብር ለሀገር ለሞቱት ጀግኖች አባቶቻችን።
ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን
ምንጮች:- 
★የኢትዮጵያ ጀግኖች ውሎ (አያኖ ጉርሙ)
★ማህደረ ዜና
Filed in: Amharic