>

ትግራይና ኢትዮጵያ ሁለት አገራት? ወይስ አንድ አገር? (አንተነህ ሙሉጌታ)

ትግራይና ኢትዮጵያ ሁለት አገራት? ወይስ አንድ አገር?
አንተነህ ሙሉጌታ
 ይህንን ጥያቄ እንድጠይቅ ያረገኝ ሰሞኑን ኤርትራ በትግራይ በኩል ያለውን ድንበር ዘግታ ከኢትዮጵያ ጋር ግን በአፋር ክልል በቡሬ በኩል ያለውን ድንበር ክፍት አድርጋ የሁለቱ አገራት ዜጎች ያለምንም ችግር እየተጠቀሙበት ነው።
ይህንን ተከትሎ ኤርትራ ድንበሩን የዘጋችው በኢትዮጵያ ላይ ነው ወይስ በትግራይ ላይ? በትግራይ ላይ ከዘጋችው በኢትዮጵያ ላይ እንደዘጋችው አይቆጠርም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር ያላት ግንኙነት ጥሩ የሚባል ብቻም ሳይሆን ፍቅር በፍቅር ሁነዋል የሚያስብል ነው። ከትግራይ ጋር ግን ያው የቆየው አይነት ግንኙነት እሳትና ጭድ ሁነዋል ባይባልም የጎሪጥ ግን እየተያዩ ነው።  በምክንያት እየተጠቀሰ ያለው ደግሞ ያው የተለመደው የትግራይ በሽታ ነው። የትግራይ በሽታ / Tigray sindrome ምን እንደሆነ ሁላችሁም ኢትዮጵያዊያን አሳምራችሁ ስለምታውቁት ማብራራት አይጠበቅብኝም።
በኤርትራና በትግራይ መካከል ያለው የድንበር መዘጋት ችግር የኢትዮጵያና የኤርትራ ችግር ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን የሚመልሰው የትግራይና የኢትዮጵያ ግንኙነት ነው። ትግራይ ዛሬም  የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አገር አካል ነች ወይስ አይደለችም? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ነው ቁልፉ።
ታድያ ትግራይ ዛሬም የኢትዮጵያ አካል ነች ሲባል በወረቀት ላይ በሰፈረው ሕግ ወይም ሕገመንግስት ተብዮው ወረቀት ላይ በተጻፈው ብቻ ሳይሆን በተግባርም የኢትዮጵያ አካል ስትሆን ነው። ማለትም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ፌደራላዊ በሆኑ ጉዳዮች ልክ እንደ ደቡብ: እንደ ኦሮሚያ: ወይም እንደ አማራ ክልሎች ሁሉ ትግራይ ላይም የሚፈጸም ስልጣን/ ተግባርና ሀላፊነት; በእንግሊዝኛው jurisdiction (ጁርስዲክሽን) ሲኖረው ነው።
የፌደራል መንግስት በፌደራላዊ ጉዳዮች ትግራይ ላይ ልክ በሌሎች ክልሎች ያለውን አይነት ስልጣን/ጁርስዲክሽን በተግባር ማዋል ካልቻለ ትግራይ የፌደራሏ ኢትዮጵያ አካል ነች ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቸግራል። በወረቀት ላይ የሰፈረው መሬት ላይ ተግባር ላይ ካልዋለ ችግር አለ ማለት ነው።
እስኪ የፌደራል መንግስት ትግራይ ላይ ጁርስዲክሽን አለው ወይስ የለውም ለማለት አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ።
1.  በአሁኑ ሰዓት አንድ ሰው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚያስከስሰው ፌደራላዊ ወንጀል ሰርቶ የፌደራል መንግስቱ ለፍትህ እንዳያቀርበው ሸሽቶ ከለላ የሚያገኘው በትግራይ መንግስት ነው።
በወረቀቱ ላይ በተጻፈው ሕግ ቢሆን ኑሮ የፌደራል ፓሊስ የፌደራል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ይዞ ትግራይ
በመሄድ ተከሳሹን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ይችል ነበር። ወይም የፌደራል ፍርድ ቤቶች የትግራይ ክልል ፓሊስን ተከሳሹን አስሮ  አዲስ አበባ እንዲያቀርበው ማዘዝ ይችሉ ነበር። በተግባር ሁለቱም ተሞክረዋል። ውጤት ግን አላስገኙም።
የፌደራል ፍርድ ቤት ማዘዣ የያዙ የፌደራል ፓሊሶች ትግራይ ሂደው ከትግራይ ክልል እንኳንስ ትብብር ሊያገኙ ይቅርና በተቃራኒው ለሳምንታት ታግተው በብዙ ድርድርና ማግባባት ነው ተለቀው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ትግራይ ላይ ሕገመንግስቱ የሚፈቅድለትን ፌደራላዊ ጉዳይ ከሚያስፈጽም ይልቅ ኬንያ: ሶማሊያ: ጅቡቲ ወይም ሱዳን ሂዶ ቢያስፈጽም ይቀለዋል። ከእነዚህ አገሮች ጋር የዲፕሎማሲ መርህን በመከተል ጉዳዩን ማስፈጸም ይችላል። ትግራይ ላይ ግን ዲፕሎማሲም ሕግም አይሰራም።  በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት  በፌደራላዊ ጉዳዮች ትግራይ ውስጥ ተግባራዊ ስልጣን የለውም። የፌደራል መንግስቱ ትግራይ ውስጥ በወረቀት / በሕገመንግስቱ የሰፈረውን ፌደራላዊ ስልጣኑን መጠቀም አይችልም።
2.   የአገር መከላከያ ሰራዊት ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የፌደራል መንግስቱ ጉዳይ ነው። በሰራዊቱም ሆነ በጦር መሳሪያው ማዘዝ; ማሰማራት; መመደብ; ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ስልጣን ሙሉ በሙሉ የፌደራል መንግስቱ ስልጣን ነው። ክልሎች ቅንጣት ታክል ስልጣን የላቸውም።
 አንድ የጦር ክፍል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዘዋወር ማገት; ወይም ከባድ የጦር መሳሪያውች ከእኔ ክልል ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀስ አይችሉም ብሎ ማገት እንኳንስ መብት ሊሆን ቀርቶ ከባድ ወንጀል ነው።
ትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ሰሞኑን የትግራይ ክልል ባለስልጣናት እና የትግራይ ሕዝብ በመተባበር የመከላከያ ሰራዊትና የጦር መሳሪያው ከትግራይ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይንቀሳቀስ ሀይልን ተጠቅመው አግተውታል። ትግራይ ላይ በፌደራል መንግስት አካላት ላይ እገታ መፈጸም የመጀመሪያ እንዳልሆነ ከላይ ገልጨዋለሁ። የፌደራል ፓሊስ  አካላት ለሳምንታት ታግተው በልምምጥ እንደተለቀቁ ይታወቃል። አሁንም የታገተውን የመከላከያ ሀይልን ጉዳይ ፌደራል መንግስቱ ድርድር ጀምሯል።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር እጅግ ሲበዛ ትግስተኛ ስለሆኑ እንጅ (ትዕግስታቸው አንዳንዴም መጠን ያልፋል) የመከላከያ ሰራዊቱን ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅመህ እገታህን አስለቅቀህ ጥሰህ ውጣ ብለው ትዕዛዝ ቢሰጡ ኑሮ እነዚህ እብሪተኞችን በጥቂት ደቂቃዎች አመድ አድርጓቸው የእድሜ ልክ ትምህርት ሊሰጣቸው ይችል ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን አሁንም የተከተሉት ድርድር ወይም ልምምጥ ነው።  የመከላከያ ሰራዊቱና የአጋቾቹ የትግራይ ሀይሎች የሀይል ምጥጥን የአንበሳና የቀበሮ ፉክክር አድርጌ ነው የማየው። ጥጋብ የወጠራት ቀበሮ አንበሳን ጦንነት ካልገጠምን ብላ እንደምትፎክረው አይነት ማለት ነው። ወይም የአገሬ ሰዎች አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች እንደሚሉት ማለት ነው።
3.  የትግራይ መንግስት እና የህዎሃት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ እና የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሰላም ለማደፍረስ እየፈጸሙት ያለው ተግባር የአደባባይ ምስጢር ነው። ከሞላ ጎደል በመላው ኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉት ግጭቶች: የጅምላ ፍጅቶች ወዘተ ስፓንሰር የሚደረጉት በህውሃትና በትግራይ ክልል ባለስልጣናት ነው። በሰላም እታገላለሁ ብሎ ከገባ በኋላ ይህን ሁሉ ችግር  እየፈጠረ ያለው ኦነግም አይዞህ የተባለውና ድጋፍ የሚያገኘው ከትግራይ ነው።
ትግራይ ይህንን ሁሉ ችግር በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመች ያለችው  ከላይ የትግራይ በሽታ/ Tigray Syndrome ብየ በጠቀስኩት በሽታዋ ምክንያት ነው። በአሁኑ ሰዓት የህውሃትና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ኢትዮጵያን የማፈራረስና ውስጣዊ ሰላሟን የማደፍረስ ተግባራቸውን ማስቆም ለፌደራል መንግስቱ ፈተና ሁኖበታል። የህውሃትና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ከኢትዮጽያ ሕዝብና ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር የኢትዮጵያን አንድነትና ውስጣዊ ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ መቆም ይቅርና በተቃራኒው አጥፊና ጠፊ ሁነው ነው ያሉት።
ትግራይ ኢትዮጵያን የማፈራረስና ውስጣዊ ሰላሟን የማደፍረስ ተግባሯን አላቆምም ብላ ከቀጠለች ፌደራል መንግስቱ ትግስቱ ሲሟጠጥበት የኢትዮጵያን አንድነቷንና ሰላሟን ለመጠበቅ በትግራይ መንግስት እና በህዎሃት ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እስከመውሰድ ድረስ ሊሄድ ይችላል። የፌደራል መንግስቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ውስጣዊ ሰላም ለመጠበቅ ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መከላከያ ሰራዊትንና ፌደራል ፓሊስን በመጠቀም  በህዎሃትና በትግራይ መንግስት ባለስልጣናት ላይ እርምጃ መውሰድ ይችላል።
የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ; የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካልም ነኝ ብሎ ካመነ የኢትዮጵያን አንድነትና ውስጣዊ ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል የኢትዮጵያ ፌደራላዉ መንግስት በህዎሃት ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ሲወሰድ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሊተባበር ይችላል።
አይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም; የኢትዮጵያ አንድነትና ውስጣዊ ሰላም ጉዳይ አይመለከተኝም; ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያን እያጠፉ ያሉ የህዎሃት ባለስልጣናት የእኔ ትክክለኛ ወኪሎች ናቸው ብሎ ካመነ ከህዎሃት ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሊከፍት ይችላል። የትግራይ ሕዝብ ለህዎሃት ባለስልጣናት ብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ካወጀ የኢትዮጵያና የትግራይ አንድነት ድጋሚ ላይመለስ እስከመጨረሻው ይበጠሳል።
በነገራችን ላይ ከአማራ ክልል በሀይል ወደ ትግራይ የተወሰዱት አውራጃዎች ማለትም ወልቃይት; ጠገዴ; እና ራያም የሚመለሱት በዚህ መንገድ ነው።
እስከዚያው ድረስ ትግራይና ኢትዮጵያ በወረቀት አንድ አገር በተግባር ግን ሁለት አገራት ሁነው ይቀጥላሉ።
Filed in: Amharic