>

የመከላከያ ኃይል መታገት ጉዳይ (ሀብታሙ አያሌው)

የመከላከያ ኃይል መታገት ጉዳይ
ሀብታሙ አያሌው
በኢትዮ – ኤርትራ የሰላም ስምምነት መውረዱን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ በድንበር ሰፍሮ የቆየው ከፍተኛ የመከላከያ ኃይል ከቦታው እንደሚለቅና ለሌላ ግዳጅ እንደሚሰማራ በቅርቡ የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች መግለፃቸው ይታወሳል።
ያንን ውሳኔ ተከትሎ ትላንት ዕለተ ሰኞ አመሻሽ ላይ ኢትዮ ኤርትራ ድንበር አከባቢ የነበረው ሰራዊት ከባድ እና ቀላል የጦር መሳርያ የጫኑ መኪኖችና የሰራዊቱ አባላት ወደ ተሰጣቸው አዲስ ስምሪት መጓዝ ሲጀምሩ ህወሓት  በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን  ስምሪቱን  ለማስቆም ሞክራለች።
ይሁን እንጂ የመከላከያ ኃይል ጉዳዩን በማያዉቁ ንፁሃን ዜጎች በተለይም ህወሓት ሆን ብሎ ከፊት ባሰለፋቸው ህፃናትና አዛዉንት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በታገተበት ቦታ ዛላ አንበሳ ድንበር አካባቢ ለሊቱን በትዕግስት ካሳለፈ  በኋላ  አስገዳጅ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ህወሓት የዘጋችውን መንገድ እንድትከፍት አስገድዷል።
የህግ የበላይነት ማስከበር የሚችል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ከመቼውም በላይ ያስፈልጋል !!
እዚህ ጋር ደግሞ ሌላ ትኩሳት !!
ከአዲስ አበባ – ጁቡቲ መንገድ  ለመዝጋት እየተሞከረ ነው !
“ከመቋዲሾ ሱማሌያ በመነሳት ጥቃት እየፈፀመብን ያለው አልሸባብ ነው”  የሚለው የአፋር ክልል የገዋኔ አካባቢ ነዋሪዎች ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ጉዳዩ ሌላ መዘዝ ይዞ ብቅ እያለ ነው።
ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ  ዋነኛ የወደብ መተላለፊያ  የሆነው የኢትዮ- ጁቡቲ መንገድ በገዋኔ ህዝብ መዘጋቱን መረጃዎች  ያመለክታሉ።  ከዛላ አንበሳ መከላከያ እንዳይንቀሳቀስ ያግዳሉ በቻሉት አቅም በየክልሉ ፀጥታ ያደፈርሳሉ ። አገርን በቀውስ አምሰው ወደ ስልጣን ለመመለስ ትግላቸው የሞት ሽረት ሆኗል። ጌታቸው አሰፋን አሳልፈው እንደማይሰጡ መግለፃቸውንም ዛሬ በፓርላማ ሪፖርት ያቀረበው የአቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ኃላፊው ይፋ አድርጓል።
አስገራሚው ነገር በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ  “ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ተኩሰን ሌላ ሰው አንገድልም” ያሉትን የአቃቤ ህጉን ንግግር ብንቀበል እንኳን፤ በእርግጥ እንደሚባለው በረከት ስምዖን ለተባበሩት መንግስታት ለመስራት እንዲሾም የዶክተር አብይ መንግስት የድጋፍ ደብዳቤ ፅፎ ከሆነ ስሜታችን ከትዝብት በላይ መሻገሩ ተፈጥሯዊ መሆኑ አይቀሬ ነው።  ማንኛውም ዜጋ ለተባበሩት መንግስታት ተቀጥሮ ለመስራት የግለሰቡ አገር መንግስት የድጋፍ ደብዳቤ መፃፉ አስገዳጅ ህግ ነው።
የበረከት ስምዖን ጉዳይ ከጭምጭምታ ተሻግሮ ጥርት ያለ አስተማማኝ መረጃ፤  አልተገኘበትም።
ለማንኛውም ከህወሓት ድርድር እያሉ መልመጥመጥ ዋጋ ያስከፍላል።  ድርድር ብሎ ጊዜ መግዛት ማዘናጋትና አርዶ ማጥፋት የተካኑበት የማይለወጥ ባህሪያቸው መሆኑን ለዶክተር አብይ መንግስት ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪው አረዱት ቢሆንም  ኋላ ግን “ወደሽ ከተከፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ”  እንዳይተረት ማሳሰቡ ተገቢ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic