>

ሀጥአንን በድንጋይ መውገር ጻድቅ አያሰኝም!!!  (በድሉ ዋቅጅራ)

ጥአንን በድንጋይ መውገር ጻድቅ አያሰኝም!!! 
በድሉ ዋቅጅራ
.
የሰራዊትንና የቤቲን ቃለምልልስ ተመለከትኩት፡፡ ሁለቱም ከህዝቡ ጀርባ፣ የትናየት ርቀው ነበር፤ ሁለቱም ሀሳብ ሳይሆን ድፍረት ታጥቀው ነበር፡፡ ሰራዊት የቤቲን ርቀት ተጠቅሞ፣ ዳግም በህዝብ ላይ አላገጠ . . . .
.
• ‹‹የአላሙዲን እስር . . . . እንደማንኛውም ሰው እስር አሳዝኖኛል፡፡›› ሲል (‹‹ከህዝብ ወገን የነበሩ እነተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አንዱአለም አራጌ . . . ሲታሰሩ አዝነህ፣ ምን ብለሀል?›› ብላ አልጠየቀችውም፡፡
• ‹‹እኔም እኮ ህዝብ ነኝ፡፡›› ሲል፣ (እንደ ግለሰብ እየሞገተችው እያለ፣ በህዝብና በግለሰብ መካከል ያለውን ልዩነት ጠቅሳ ልትሞግተው አልሞከረችም)
• ‹‹የሚገባኝን ክፍያ አግኝቼ አላውቅም›› ሲል ‹(በአንድ ዝግጅት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘቱን ለምሳሌ ጠቅሳ፣ የሚገባው ስንት እንደነበር አልጠየቀችውም)
• ‹‹ህወሀት ከሚባል ድርጅት ጋር ሳይሆን ኢህአዴግ ከሚባል መንግስት ጋር ነው የሰራሁት›› እያለ ሲያላግጥ፣ (መሪው ህወሀት እንጂ ኢህአዴግ እንዳልሆነ ማስረጃ አቅርባ አልሞገተችውም፡፡)
.
ቤቲ በኤል ቲቪ ዝግጅት ማቅረብ የጀመረች ሰሞን ‹‹ተመንደጊ›› የሚያሰኙ ፕሮግራሞችን አቅርባ ነበር፡፡ ተመልካች ደስ አለው፤ አደነቃት፡፡ የመረጃና የሀሳብ ዝግጅቷ ያቀዳጃት አድናቆት፣ ከባዶ ድፍረት የመነጨ መሰላት፡፡ መረጃና ሀሰብን እየተወች፣ ባዶ ድፍረት ይዛ ቀረበች፡፡ አነሆ ከሰራዊት ጋር ባደረገችው ንትርክ፣ ከፌስቡክ በተለቃቀመ ሀሜት ስትነታረክ ምንም አዲስ መረጃ ሳናገኝ፤ እሱም ወደልቦናው ሳይመለስ ተለያዩ፡፡ . . . . የፌስቡኩንና የሀሜቱን ፊት ለፊት በቲቪ ማቅረብ አንድን ሰው ጋዜጠኛ አያደርግም፤ ሀጥአንን በድንጋይ መውገር ጻድቅ እንደማያሰኝ፡፡
.
ሰራዊት እራሱን አንዴ እንደማስታወቂያ ሰራተኛ (ነጋዴ)፣ አንዴ እንደአርቲስት ሲያቀርብ ለቤቲ ልዩነት አልነበረውም፡፡ የውይይቱ መጀመሪያ መሆን የነበረበት ግን ይህ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ነጋዴና አርቲስት ያለባቸው ማህበረሰባዊ ሀላፊነት እጅግ ይለያያል – ይራራቃልም፡፡  . . . . ነጋዴ ከሆነ፣ ለማትረፍ እስከየት ይሄዳል? የህዝብን መብት፣ ነጻነት . . . እስከመሸቀጥ?
.
አርቲስት ነኝ ካለ፣ ስለህዝብ መብት መረገጥ፣ ስለሙስናና ኢፍትሀነት ድምጹን ማሰማት አልነበረበትም ወይ? ከዚሁ ጋር ሰማያዊ ፈረስ፣ ሂሮሽማና ወርቅ በወርቅ የተሰኙት ፊልሞቹ (እሱ እንዳለው ለፊልም እድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ ካለ) ምንድነው? ሁሉም ገቢን አላማ አድርገው የተሰሩ የይድረስ ይድረስ ከተፋ ውጤቶች አይደሉም ወይ? . . . . ቤቲ ከድፍረቷ ይልቅ ይህን መሰል የመረጃ ዝግጅት ቢኖራት፣ ምን አልባት ሰራዊትም ወደ ልቦናው ተመልሶ ካስቀየመው ህዝብ ጋር፣ በይቅርታ ይታረቅ ነበር፡፡
.
ባለፈው ጊዜ በዚሁ ፕሮግራም ላይ ቴዎድሮስ ተሾመ ቀርቦ ከተናገረው እውነት አንዱ፣ ‹‹እኔ ነጋዴ ነኝ›› ማለቱ ነው፡፡ ሰራዊትም ነጋዴ ነው፤ ስነጥበብን እንደነዚህ ላሉ ነጋዴዎች እንዲቸረችሩት አሳልፈው የሰጧቸው የሙያው ባለቤቶችና ተቋማት፣ ከእነሱ የበለጠ ለስነጥበብ መሞትና አሉታዊ ማህበረሰባዊ ሚና መጫወት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡
Filed in: Amharic