>

ግርምሽ ሲታወሱ!!! ( በእውቀቱ ስዩም)

ግርምሽ ሲታወሱ!!!
 በእውቀቱ ስዩም
ግርማ ወልደጊዮርጊስ ፕሬዚዳንት ሁኑው የተመረጡ እለት ብዙ ሰዎች ተገርመዋል  :: ከእስክንድር ነጋ ጋዜጦች አንዱ ዜናውን የዘገበችው ” ወያኔ አበደች ” በሚል ርእስ  እንደነበር ትዝ ይለኛል:: አንድ አሙስ የቀረው ሽማግሌ እንዴት ለዚህ ሚና ይታጫል በሚል እብሪት  የተቹ  አልጠፉም :: ብዙዎቻችን “ሽማግሌ  ከወጣት ቀድሞ  ይሞታል  ” የሚል ጅልነት ሰለባ ነን::
አፈሩን  የስፖንጅ ፍራሽ ያድርግለትና  አቶ  አሰፋ ጫቦ  ስለፕሬዚዳንት ግርማ ሹመት ሲተች” ወያኔ  ያልጋ  ቁራኛ ኦሮሞ ባሻንጉሊትነት አስቀምጦ….” ብሎ ፃፈ:: የታሪክ ምፀት ሆኖ አሰፋ  ያልጋ ቁራኛ ብሎ ከፈረጃቸው ሽማግሌ  ቀድሞ ሞተ::
መቼም: ቀልድን የሚያህል የድሜ ማራዘሚያ ክኒን የለም::  መቶ አለቃ ግርምሽ ደግሞ  በድካማቸው  ላይ በመቀለድ  ማንም አይደርስባቸውም :: ባንድ ወቅት ፓርላማ ላይ ቆመው ንግግር ባለማድረጋቸው ይቅርታ ሲጠይቁ  ” መቆም ያልቻልኩት በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ነው”  ብለው  የባርላማውን ተቀማጭ በሳቅ ፈጅተውታል ::
ሰውነታቸው የተሸከመው የስጋ  ጉዋዝ ከርጅናቸው ጋር ተባብሮ የቀልድ ሰለባ አድርጉዋቸው ነበር:: በተለይ – ችግኝ ተከላ ዘመቻ ላይ ሲሳተፉ ሁለት ችግኝ ተክለው  ስድስት ችግኝ ድጠው ይመለሳሉ”  የሚለውን ተረብ  ሳልፈልግ ያስቀኛል::
ወዳጄ ዘላለም ኩራባቸው በግርምሽ ዙርያ ለሚፈለፈሉ ቀልዶች ዋናው ምንጭ ነው::
ለሱ እንዳውጋኝ -አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንት ግርማ የቦብ ማርሊ ልደት ሲከበር የክብር እንግዳ ሆነው ተገኙ ይ የበአሉ ማክበርያ አዳራሽ በጋንጃ ታጥኖ ጠበቃቸው::
ንግግር  ለማድረግ ሲነሱ  ጋንጃው ናላቸውን እንዳጦዘው  አልተረዱም::
” እኔ ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ” ብለው ጀመሩ::
ታዳሚው ሲያጉረመርም::
” ይቅርታ .. እኔ   …..ግርማ ብሩ”
ታዳሚው መሳቅ ጀመረ::
በመጨረሻ  ስማቸውን ካዳራሹ መሀል ይፈልጉት ይመስል ዞር ዞር ብለው ሲያዩ ታዳሚው ሁላ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ምስል  የታተመበት ቲሸርት ለብሱዋል::
ይኸኔ-
” እኔ …..ግርማዊነትዎ”
ብዙዎቻችን ፕሬዚዳንት ግርማን የምናውቃቸው በርጅናቸው ዘመን ነው::  በዚህ ምክንያት አስተያየታችን በጉብዝናቸው ዘመን የፈፀሙትን ሙያ ያገናዘበ አይደለም::
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ በግለታሪካቸው እንደመሰከሩት ደርግ አቁሞት በነበረው የህዝብ ሸንጎ ውስጥ ያለፍርሀት ሀቅ የሚናገሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን  ያውቃሉ:: አንዱ ሀዲስ አለማየሁ  ሲሆኑ ሁለተኛው ግርማ ወልደጊዮርጊስ ናቸው:: ግርምሽ ከዚያ ልበሙሉነትና ሀቀኝነት ተነስተው በመለስ ዜናዊ   አገልግሎት ስር እንዴት ወደቁ ? የሚለውን ጥይቄ ታሪክ ይመልሰው::
በመጨረሻም ዘላለማዊ የሰላም ረፍት!!
••• ///•••
በኦሮማዩ  ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ ነፍስ ዉስጥ የምናያቸው ግርማ ወ/ጊዮርጊስ
በፍቃዱ ሞረዳ
 
በየትም ይጓዝ እንዴት፣ ሰዉ በሕይወት ዘመኑ አጋጣሚዎች የፈቀዱለትን ዕድሎች ተጠቅሞ የልቡን መሻት አሳክቶ ሲያልፍ ጥሩ ነዉ፡፡ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሉጫ ለእኔ እንዲህ ዓይነት ሰዉ ናቸዉ፡፡ በሕይወት ጉዟቸዉ ለራሳቸዉ ልክ ነበሩ፡፡ የሚያምኑበትን አድርገዉ፣ ካሰቡት ግብ ደርሰዉ ሞተዋል፡፡ ሌላዉ ሰዉ ግን፣ ስለእርሳቸዉ የራሱ ሚዛንና ብያኔ አለዉ፡፡ ጉዳዩ ነዉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሆነዉ ሁለት ጊዜ ቤተመንግሥት ተገናኝተናል፡፡ አንድ ጊዜ ነፍሳቸዉን ይማርና ከአቶ አስፋዉ ተፈራ ጋር:: ሌላ ጊዜ ብቻዬን ለቃለመጠይቅ፡፡አሁንም ነፍሳቸዉን ይማርና ከአቶ ዱጉማ ሁንዴ ገዳ ጋር በደንብ የተዋወቅነዉና ያወራነዉ ፕሬዚዳንት ግርማ ቢሮ ነዉ፡፡
 ቃለመጠይቁን ከጨረስን በኋላ ባነሳነዉ አንድ ነጥብ የተነሳ ሁለታችንም ( እኔና ፕሬዚዳንቱ) ማልቀሳችንን አስታዉሳለሁ፡፡
ግርማ ወልደጊዮርጊስ የስቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊ ሆነዉ አሥመራ ሠርተዋል፡፡ እኔ እዚያ አላየሁዋቸዉም፡፡ አንዳንዶች በበዓሉ ግርማ ኦሮማይ  በሻለቃ ታደሰ ቆርቾ ነፍስ ዉስጥ እናዳያቸዉ ነግረዉኛል፡፡
ማን ያዉቃል?  ‹‹ሰማይ ቤት›› ከበዓሉ ጋር ተገናኝተዉ በዓሉ ፣‹‹ ታደሰ ቆርቾ እንኳን ደህና መጣህ›› ሲላቸዉ ‹‹ ቆሪጥ ይብላህና ማን ነዉ ታደሰ ቆሪቾ ? ›› ይሉት ይሆናል፡፡
 ነፍስ ይማር:: ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ መፅናናትን ይስጥ፡፡
Filed in: Amharic