>

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ጂኒዎቹን ከየወጡበት ጠርሙስ መመለስ ቡሹንም መክደን ግድ ይላል!!! (መሳይ መኮንን)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ጂኒዎቹን ከየወጡበት ጠርሙስ መመለስ ቡሹንም መክደን ግድ ይላል!!!
መሳይ መኮንን
ዛሬ ብዙ ነግሮች ሆነዋል። የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ94ዓመታቸው አርፈዋል። ነፍስ ይማርልን። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአንድ የአፍሪካ መጽሄት መመረጣቸውም ተሰምቷል። እንኳን ደስ አልዎት። በተረፈ ከየአቅጣጫው የሚሰማው ነገር ጥሩ አይደለም። በዚሁ መድረክ የሚመላለስ አንድ አሰቃቂ ቪዲዮም ስሜቴን ሲረብሸው ውሏል። የባለፈው የካሜሮኑ ዓይነት አሳሳች ወይም ፌክ ቪዲዮ አይመስለኝም። የእውነት የሆነ ነው። አሳፋሪው ገበናችን ለአደባባይ በቅቶ አንገታችንን የሚያስደፋ ሆኗል። ገዳዮቹም፡ ሟቾቹም የእኛው ናቸው። ሀዘናችን ቅጥ አጣ። የሞተው ባልሽ የገደለው ወንድምሽ አይነት ነገር ሆነብን።
ሰሞኑን ሞያሌ ህመም ላይ እንደሆነች አውቃለሁ። የአንድ ሀገር ልጆች በዘር መስመር ላይ ወጥተው፡ የጎሳን መፈክር እያራገቡ መገዳደላቸውን ቀጥለዋል። በቪዲዮው ላይ የምንመለከተው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ልብ የሚያደማ ነገር ነው። አቶ ለማ መገርሳ እንደ ሀገር ሰላም የለንም፡ ከዚህም ከዚያም የሚወረወሩት የሚጠግኑን፡ የሚሰበስቡን አይደሉም ብለው ሰሞኑን የተናገሩት ደግሞ ልብ ይነካል። የሃይማኖት አባቶችን በጎን ሸንቆጥ ባደረጉበት በዚሁ ንግግራቸው በአንድ እጅ ወንጌል በሌላው ደግሞ የጎሳ ፖለቲካ የሚያቀነቅን የሃይማኖት አባት አስቸግረውናል ያሉበት ከድምጸታቸው ጋር ስሜት ይቆነጥጣል። ሀገራችን የደረስችበትን ጽኑ ህመምም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በእውነት ወዴት እየሄድን ነው? የዛሬ ስምንት ወር ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር ቦግ ያለችበት የተስፋ ብርሃን እንዲጨልም ለምን ተፈለገ?
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በኢሳት ላይ የተናገሩትና ከአቶ ለማ መገርሳ ጋር ከተወያዩት የሃይማኖት አባቶች መሀል አንደኛው መንግስትን የመከሩት ለእኔ ቁልፉ መፍትሄ ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚሰብኩት ፍቅር፣ ሰላምና ይቅር ባይነት በህጋዊ ሰይፍ ካልታገዙ እነሱንም ሆነ ህዝቡን ወደ መከራ የሚያስገባ በመሆኑ አድሎ የሌለበት ህጋዊ ርምጃ መውሰድ የግድ ነው ብለዋል ፕ/ር መስፍን። የህወሀት/ኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣናትን በአንድ ቪላ ቤት ውስጥ ጥሩ ወጥ ቤት ተቀጥሮላቸው ከዚያ እንዳይወጡ ተደርገው መሰብሰቡ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል። እውነታቸውን ነው።
በረከት ስምዖን ከመቀሌ እየፎከረ ነው። መቀሌ በተናገረው ቪዲዮ ላይ በረከት የቀድሞ ጉልበት አብሮት እንዳለ ነገር ዘራፍ ይላል። የት ልኑር፡ የት ልረፍ ጭንቀት ውስጥ የተዘፈቀው በረከት ለራሱ መሸሺያና መጠጊያ እያየፈላለገ አሜሪካን ላይ ይዝታል። ጌታቸው አሰፋ መታሰር አለበት ያሉትን የአሜሪካን ኮንግረስ ማን ሲዘረጥጣቸው የሚሰማበትን ቪዲዮ ለተመለከተ የፕ/ር መስፍን ሀሳብ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑ ላይ አይጠራጠርም። በረከት ህወሀት መሸነፉን አላመነም ወይም መቀበል አልፈልገም። ለበረከት መለስ መቃብር አልወረደም። ለበረከት ኢህአዴግ የሚባለው የህወሀት የፈረስ ስም በቀደመ አሽከርነቱ ያለ ይመስለዋል። አሁንም ራሱን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አድርጓል። ስልጣን እንደከዳው፡ ቃሊቲ እነጄነራል ክንፈ እየጠበቁት እንደሆነ አላወቀ ይሆን? ያቺኑ ድሪቶውን ይዞ ከመቀሌ ይደሰኩራል። ”መጽሀፌ ላይ እንዳልኩት…” ይላል በየጣልቃው። ለማንበብ የሞት ቅጣት ያህል የሚከብደውን መጽሀፉን።
አቶ ስብሃት ነጋም ከወራትዝምታ በኋላ ብቅ ብለዋል። ከአክሱም ሆቴል ውስኪ የተራረፈችውን አቅማቸውን ተጠቅመው አዲሱ አመራር ላይ የጭቃ ጅራፋቸውን እየወረወሩ ነው። ጠ/ሚር አብይ የኢህ አዴግ ሊቀመንበር የሆኑት በአሜሪካ ጣልቃገብነት ነው። የአሜሪካው ዲፕሎማት ዶናልድ ያማማቶ አብይን አስመርጠው ተልዕኮአቸውን ፈጽመዋል ዓይነት የረፈደ ለቅሶ እያሰሙ ነው። በረከትና ስብሃት አሜሪካ ላይ ጣቸውን መቀሰራቸው የሚያስገኝላቸው ፖለቲካዊ ነጥብ አልታየኝም። በሻዕቢያ ትከሻ፡ በአሜሪካን አንቀልባ ታዝለው አራት ኪሎ ቤተመንግስት የገቡት ህወሀቶች ቀን ሲጨልምባቸው ያጎረሳቸውን እጅ መንከሳቸው ውለታ ቢስነታቸውን እንጂ ሌላ የሚነግረን እውነት የለም። የመንግስት ልብስ አጥልቀው የአሜሪካን ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው የቆዩ፡  ከዳርፉር እስከ ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን ልጆች እያስፈጁ ቅጥረኛነታቸውን በሚገባ አስመስክረዋል። ስለአሜሪካ አገልጋይነት ከሆነ ከእነሱ በላይ የአሽከርነቱን ካባ ያጠለቀ የለምና ጉንጭ አልፋ ሙግታቸውን እዚያው አክሱም ውስኪ ቤት ቢጨርሱት ጥሩ ነው።
የፕ/ር መስፍን ሀሳብ የጊዜው ፍቱን መድሃኒት አድርጌ ውስጄዋለሁ። ሶማሌ ክልል ባለራዕይ የሆኑ አስተዳዳሪ አግኝተው እየተነኮሷቸው ያሉት የህወሀት የጦር ጄነራሎች ናቸው። በቅርቡ ቴሌና ንግድ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን በቦምብ ለማጋየት ከተጎነጎነው ሴራ ጀርባ የህወሀት እጅ አለበት። የጋምቤላው አዲሱ ፕሬዝዳንት በወጉ ስልጣኑን አልያዙም።፡ በክልሉ ቢሮዎች በአማካሪነት፡ በአጃቢነትና ሹፌርነት የተሰገሰጉ የህወሀት ሰዎች በየመንገዱ እሾህና አሜኬላ እያሰቀመጡ አስቸግረዋል ነው የሚባለው። አፋር ላይ ገና አልጠራም። የህወሀቱ ቢተው በላይ ጠዋትና ማታ እየተመላለሰ እንደሆነ ይሰማል። ቤንሻንጉል የህወሀት የጥፋት ድር በቀላሉ የሚበጣጠስ አይመስልም። በዚህ ላይ ደግሞ የህወሀት መሪዎች እንደፈለጋቸው በሚዲያ ላይ እየወጡ የጠ/ሚር አብይን መንግስት አቅመ ቢስ እንደሆነ አድርገው እንዲደሰኩሩ ተለቀዋል። ብቻቸውን አይደሉም። እንደእስስት የፖለቲካ መስመራቸውን መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚለዋውጡ የጎሳ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ከጎናቸው ሆነዋል። እናም የጠ/ሚር አብይ መንግስት አሁን ላይ ለነገሰው ስርዓት አልበኝነትና የሰላም እጦት ፍቅርና ይቅርታ ብቻውን መድሃኒት ነው ብሎ ያምናልን?
በእርግጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። የህወሀትን መንደር በጥፍሩ ያስቆመው የእስር እርምጃ ካሮት ብቻ ሳይሆን ዱላም ያለው መንግስት እንደሆነ ካሳዩት ክስተቶች አንዱ ነው። የህወሀት መሪዎች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ መቀሌ ሲገቡ፡ በቦሌና በባሌ አፍትልከው የወጡ ገራፊዎችና አስገራፊዎችን በተመለከተ ከኢንተርፖል ጋር በመሆን ካሉበት ማንቁርታቸው ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ ከወዲሁ እየተመከረበት መሆኑ አንድ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው። በመቀሌው የህወሀት ፌሽታ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰው ዘጋቢ ፊልም በራሱ ቀላል የማይባል ውጤት እንዳስመዘገበ በህወሀት መንደር የተነሳውን ጫጫታ በማየት መግለጽ ይቻላል። መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊያደርጉ ከነትጥቃቸው ቤተመንግስት ያመሩ ወታደሮች ላይ የተላለፈው ብይንም የአብይ አስተዳደር ጥርስ ያለው መሆኑን ያመላከተ ነው። ሌሎች እርምጃዎችም አሉ። ግን ሀገሪቱ እየሄደችበት ካለው አደገኛ አዝማሚያና የጥፋት ሃይሎች ሀገር ለማተራመስ ካላቸው ቁርጠኝነትና ፍጥነት አንጻር ገና ምኑም አልተነካም።
ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ጋር የተወያዩት የሃይማኖት አባቶች ”የመንግስት ትዕግስት በዛ” ሲሉ ምክንያት ነበራቸው። ትዕግስትን አብዝቶ መስበክ ካለበት የሃይማኖት መሪ በዚህ ደረጃ ጠንከር ያለ አቋም ሲወሰድ የሆነ ነገር አለ ማለት ነው። አንድ አባት እንደውም ”መንግስትን የመናቅ ነገር አለና ትንሽ ቁንጣጫ ያስፈልጋል” ብለዋል። ተስፋና ጽልመቱ በእኩል መስመር አንድ ላይ በሚጓዙባት ኢትዮጵያ ጽልመት ቀናችንን እያጨለመው በአሸናፊነት እንዳይጓዝ መደረግ አለበት።
አዎን! የተለቀቁት ጂኒዎች ወደ ጠርሙሳቸው መግባታቸው የህልውና ጉዳይ ሆኗል። እዚህም እዚያም የተለቀቁት የህወሀት ፈረሶች ሉጋም ተበጅቶላቸው ወደ ጋጣቸው እንዲገቡ ማድረግ ለነገ የሚተው ስራ አይደለም። ፕ/ር መስፍን እንዳሉትም የህወሀት/ኢህአዴግ መሪዎችን ሰብስቦ በአንድ ቪላ ቤት ውስጥ ማቆየት ግድ ይላል። ሀገር እየተተራመሰች ባለችበት ሁኔታ የትኛውንም እርምጃ በመውሰድ ከጥፋት መታደግ የመንግስት ሃላፊነት ነው። ህወሀቶች የለውጡን ሃይል ለማዳከም በፊት ለፊት በፕሮፖጋንዳ፡ በስተጀርባ ደግሞ እሳት በመጫርና በማቀጣጠል እያደረጉ ያሉትን መጠነ ሰፊ የጥፋት ተግባር ማስቆም የመንግስት ብቸኛ የወቅቱ ስራ መሆን አለበት። ሀገር ስትኖር ነው ሁሉ ነገር የሚያምረው። ሁሉም ነገር በሀገር ነውና።
ለማጠቃለል የአብይ አስተዳደር አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ያስፈልገዋል። መከላከያ ሰራዊቱ ራሱን እያጠራ ቢሆንም አንድ ገጽ ላይ መናበብ የሚችሉ የሰራዊቱ መሪዎች የሚቆጣጠሩት አዋጅ በአስቸኳይ ታውጆ ጂኒዎች ከየወጡበት ጠርሙስ ተመልሰው እንዲገቡ መደርግ አለባቸው። ጠ/ሚር አብይ ለዚህ ቁርጠኛ መሆናቸውን ሰሞኑን የመድሃኒት ያህል ከወሰድነው ጽሁፋቸው ለመረዳት ችለናል። ጠ/ሚሩ በእርግጥም ቆርጠዋል የሚያሰኝ መግለጫ ነው ያወጡት። ግፍ ሰርቶ መደበቅ፡ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም ብለዋል ጠ/ሚሩ። ቃላቸውን ወደ መሬት ያወርዱታል ብለን እንጠብቃለን።
Filed in: Amharic