>

"የነብርን ጭራ አይዙ፤  ከያዙም አይለቁ " (ንጉሱ ጥላሁን)

“የነብርን ጭራ አይዙ፤  ከያዙም አይለቁ “
ንጉሱ ጥላሁን
የጀመርነው ለውጥ እንዳይቀለበስ እንተባበር፣ እንረዳዳ አንድነታችንን እናጠናክር ስንል ትናንት ያየነውን ዘገናኝ ድርጊት የፈፀመ ጭንቅላት ይህ ጉድ እንዳይጋለጥ እና ፀሀይ እንዳይመታው ለማድረግ ማንኛውንም እርምጃ ሊወስድ እንድሚችል ስለምንገነዘብ ነው::
ይህንን ሀቅ ለማዳፈን ይረዳው ዘንድየተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ “ጭር ሲል አልወድም ” ማለቱ አይቀርም:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ የደለበ የተዘረፈ የሁላችን ሀብት በእጁ አስገብቷል::
ይህንን ገንዘብ ለፈለገው አላማ ይርጫል:: በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር ሊወጣ ሲል የሚያዘው ገንዘብ እና ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ የሚያዙት የጦር መሳሪያዎች አላማቸው ልማት ወይም ሀገር እና የወገንን ደህንነት መጠበቅ ሳይሆን ለውጡን መቀልበስ ብቻ ነው::
አንዳንድ ሰዎች ወገኖቻችን የደረሰባቸውን ግፍ ሚዲያዎች ቀንጭበው ሲያቀርቡ ” በዛ፣ ተደጋገመ፣  ተጋነነ ወዘተ ” ሲሉ ይደመጣሉ:: ነገሩን በተጎዱት ወገኖች ቦታ ሆኖ ማየት ደግሞ ምንም እንዳልተነካ መመስከሩ አይቀሬ ነው:: አንዳንዶቹ ከእስር ቤት እንደወጡ የሆነውን ሙሉ ሳይሆን በጣም በጥቂቱ ሲገልፁልን እንደ ሰው አልቅሰናል፣  እንደ አመራር ደግሞ የምንመራው ህዝብ እንዲህ ሲሆን የት  ነበርን፣ ምንስ ስንሰራ ነበር፤  የሚል የከፋ የወንጀለኝነት ተሰምቶናል:: ለነገሩ በለውጡ እኛም ራሳችን ነፃ ወጣን እንጂ ከእነዚህ ወገኖቻችን ጋር መቀላቀላችን የማይቀር መሆኑን እንረዳ ነበር::  አሁን የነብሩን ጭራ ይዘናል እና በፍፁም አንለቀውም::
አሁን መላው የሀገራችን ህዝብም የነገሩን ክፋት የበደሉን ጥግ  የተገነዘበ በመሆኑ ይህ ለውጥ እንዳይቀለበስ በባለቤትነት መንፈስ ይደግፋል የሚል እምነት አለኝ:: ይህንን ግፍ የፈፀመ፣  ያስፈፀመ፤ የሀገር ሀብት የዘረፈ እና የተጠረጠረ ሁሉ ከያለበት ለህግ በማቅረብ የማይረባረብ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አልገምትም:: በዚህ ጉዳይ በመረጃ እጥረት ወይም የጅምላ አስተሳሰብ አቋም የያዘ ሰው፣ ህዝብ ወይም አካባቢም አቋሙን ይለውጣል፤  ፍትህ ለተገፉ የሚል ግልፅ መልዕክት ያስተላለፋል  ብዬ አስባለሁ :: ምክንያቱም የትናንቱን ዶክመንተሪፊልም ያየ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ማዘኑ አይቀርምና::
Filed in: Amharic