>
5:13 pm - Tuesday April 19, 0603

ኢትዮጵያዊያንን አይመጥንም!!!  (ቅዱስ ማህሉ)

ኢትዮጵያዊያንን አይመጥንም!!! 
ቅዱስ ማህሉ
የብሄር ብሄረሰብ በዓል ማህበረሰቡን በነበረበት የድሮ አስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ አስሮ ለመሻሻል የሚኖረውን ፍላጎት በመግታት ኋላቀርነቱን እና ድህነቱን አኩሪ ባህሉ አድርጎ እንዲኖር የሚያበረታታ ኮምኒስታዊ ሾው ነው። ታዲያ ይሄንኑ በዓል የለውጥ አራማጆቹ ኢሕአዴጎች ለምን ሊቀጥሉት እንደፈለጉ አልገባኝም።  የብሄር ብሄረሰብ በዓል ማለት በአጭሩ ‘ሶሻላይዜሽን ኦፍ ጎሰኝነት’ ማለት ነው። ይህም ደግሞ በተለያዩ ትምህርታዊ ዘመቻዎች ማህበረሰቡን በማንቃት ማሻሻል የሚገባውን ሗላቀር ልማድ እና የአኗኗር ዘይቤ  ርስት አድርጎት እንዲኖር የሚያበረታታ የኢሕአዴግ ሞራላዊ ዝቅጠት ነጸብራቅ ነው።
በፕሪሚቲቭ አስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘይቤ የታሰረን ማህበረስብ አንድ ላይ ሰብስቦ ‘ባህሌን እዩልኝ’ ማለት ለተመልካቹ ከሁሉም ቀደምት የነበረችው ኢትዮጵያ የትየለሌ የኋሊት ተጉዛ ያለችበትን ኋላቀርነት ገበናዋን ገፎ የሚያሳይ አሳፋሪ ድግስ ነው። በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖር በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሽህ ያህል አዳዲስ ስራ መፍጠር የሚጠበቅባት ኢትዮጵያ ይሄን የትራይባል ሜንታሊቲን እና መንጋዊ አስተሳሰብን የሚያጠናክር ድግስ በ100ሚሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥታ መደገሷን ዓለም ቢሰማ በትክክልም በዓሉ የኋላቀርነታችን ብቻ ሳይሆን የድንቁርናችን ማሳያም ጭምር ይሆናል።
 የኋላ ታሪክ አሻራችን እና የቀደምት ስልጣኔያችን ማሳያ የሆነው ላሊበላ ሲፈርስ “እባካችሁ ታደጉልን” ብለን ደጅ የጠናንባቸው ፈረንጆች ነገ ዞረን ስናየው ምንም እሴት ጥሎልን ለማያልፈው የብሄር ብሄረሰብ  በዓል 100ሚሊዮኖችን ስናወጣ ሲያዩ ለነገሮች የምንሰጠው እሴት/ቫልዩ መለኪያ ምን ያህል እንደዞረብን ያሳያል።
በነገራችን ላይ 100ሚሊዮን ብር አዲስ አበባን ወይም ኢትዮጵያን ይጎዳል ብየ ሳይሆን ሃገራችን እዚህም እዚያም በሚነሱ ግጭቶች ውስጥ ሆናና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተገቢውን ምላሽ ያገኙ ዘንድ የመንግስት ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ እየታወቀ፣በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ያልተከፈለ የውጭ ሃገራት እዳ ጀርባዋ ጎብጦ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ስራ ፈላጊ በሃገሪቱ ተንሰራፍቶ ለእንዲህ ዓይነት ድግስ ይሄን ያህል ብር መውጣቱ የመጣውን ለውጥ ሌላ ሳይሆን ሌላ ሳይሆን ራሱ መንግስት ለማደናቀፍ አሉታዊ አበርክቶ እያደረገ  መሆኑን ጠቋሚ ነው። ወይም በተዘዋዋሪ ለውጡን ለማይፈልጉ ድጋፍ እያደረገ ነው።
እናም ይሄ ስህተት እንዳይደገም እና ተመሳሳይ ቸበር ቻቻዎች ከመደረጋቸው በፊት ሁለት ሶስቴ ሳይሆን 10 ጊዜ ቢታሰብበት መልካም ነው ባይ ነኝ።በጥቅሉ ይሄ በዓል ለውጡን ፣ የለውጥ ሃዋሪያቱን እንዲሁም በርግጠኝነት ኢትዮጵያዊያንን ይመጥናል ብየ አላምንም።
Filed in: Amharic