ዳዊት ሰለሞን [ጋዜጠኛ]
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ የሆነውና በቅርቡ ሐገርና ፖለቲካ የሚል መጽሐፍ ለንባብ ያበቃው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሐብታሙ አያሌው ዛሬ ማለዳ ከመኖሪያ ቤቱ እንደወጣ ቦሌ ፍላሚንጎ አካባቢ በፖሊሶች ተይዞ መወሰዱን የአይን እማኞች ይፋ አድርገዋል፡፡
ሐብታሙ በምን ምክንያት በፖሊሶች እንደተያዘና ወዴት እንደተወሰደ የአይን እማኞቹ ባያረጋግጡም የፓርቲው አመራሮች በአሁኑ ሰዓት ፍላሚንጎ አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣብያ በማምራት ጉዳዩን ለማጣራት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
የሺዋስ አሰፋ ማዕከላዊ ሲወሰድ ሐብታሙ አያሌው ያለበት አልታወቀም
ቤት ፈታሾቹ የየሺዋስን ቤት በሚበረብሩበት ወቅት የየሺዋስን ባለቤት ጭምር ወደ ውስጥ እንዳትገባ ማድረጋቸው አግራሞትን ፈጥሯል፡፡
በዚሁ ዕለት ማለዳ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት በማምራት ላይ የነበረው አቶ ሐብታሙ አያሌው ቦሌ ደምበል አካባቢ እንደደረሰ ብዛት ያላቸው የደህንነት አባላት በፌደራል ፖሊስ መንገዱን በመዝጋት ሐብታሙን ይዘውት ሄደዋል፡፡የአንድነት አመራሮች ወደ ተጠቀሰው ቦታ በማምራት ድርጊቱ ሲፈጸም ከተመለከቱ ሰዎች የሐብታሙ መያዝን አረጋግጠዋል፡፡እስካሁን ድረስ ግን ሐብታሙን ይዣለሁ ያለ አካል አልተገኘም፡፡