>

ብሄሬ ብሄሬ ፖለቲከኞች!!! (ታምሩ ተመስገን)

ብሄሬ ብሄሬ ፖለቲከኞች!!!
ታምሩ ተመስገን
ሴኔጋል ጎሬ ደሴት ውስጥ የሚገኝ The door of no return የሚባል አንድ ቦታ አለ፡፡ ዛሬ ዘመን በታሪካዊ ቦታነት እንዲጎበኝ ሳያደርገው በፊት ከ15ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን  ድረስ የባሪያ ንግድ ሲካሄድበት ነበር፡፡ ፊታቸውን ወደአትላንቲክ ውቂያኖስ አዙረው ወደ ቆሙ የባሪያ መርከቦች The door of no return የሚባለውን በር አልፈው የገቡ አፍሪካዊያን ዳግም ወደ ቀያቸው እንደማይመለሱ እርግጠኞች ነበሩ፡፡ በቃ ለአውሮፓዊያን አልያም ለአሜሪካዊያን በባርነት እንደተሸጡ ማረጋገጫ ማህተማቸው ነው፡፡ ወደ ቤት መመለስ አከተመ፡፡ ከልጅ ከሚስት፣ ከእናት ከአባት፣ ከአፈሩ ከአየሩ፣ ከቅጠሉ ከሳሩ፣ ከወንዙ ከሰማዩ… እንዲሁ ይነጠላሉ፡፡ The door of no return.
…….
እዚህ እኛ መንደር መንፈስ ሆነው አክቲቪስት በሚባል የጨዋ ስም የተሸሸጉ እና ስጋ ለብሰው በፓርቲ ደረጃ መሬት ላይ የሚንቀሳቀሱ ደግሞ ብሄሬ ብሄሬ ዘሬ ዘሬ ሻንጣየ ሻንጣየ እያሉ ሚሊዮኖቹን The door of no return ወደ ‘ሚባለው የባርነት ቀንበር እየነዷቸው ከሰውነት ልክ እየናዷቸው ያሉ ስንኩል ፖለቲከኞች አሉ፡፡
ወዳጄ ብሄር  አልያም ዘር በጣም ይጠባል ‘ኮ፡፡  እመነኝ የምታምነው ፈጣሪህ በሰውነትህ እንጂ በብሄርህ አያውቅህም፡፡ የምትቀራው ቁራን የምታነበው መፅሀፍ ቅዱስ ስለብሄር የሚጠቅስበት ምዕራፍና ቁጥር የለውም፡፡ ወይስ አንተ የሰይጣን አገልጋይ ነህ? አለዚያማ እንደዚህ አይነት ጉድ የለማ! እኔ የእንትና ዘር እኔ የእንዲህ ዘር እያሉ አጉል proud መሆን ትርፉ እራስ ታውሮ ሌሎችንም ማወር ነው፡፡  እመነኝ የምፅዓት ቀን በግራና በቀኝ እምትሰለፈው በብሄርህ አይደለም ይልቁንስ በዋልከው በጎ ነገር ሚዛን እንጂ፡፡
…….
በርግጥ እኔ ወደ ምልህ አመለካከት ላይ ለመድረስ ማውቅና መኖር የሚባሉ የኮፍያና የቦት ያክል የተራራቁ ነገሮችን ነጣጥለህ ማየት ይጠበቅብሃል፡፡ ምን ይባላል መሰለህ የህይወትን ትርጉም ለማወቅ ከፈለክ በህይወትህ ሁሉ ሶስት ቦታዎች መሄድህን አትርሳ፡፡
* የመጀመሪያው እስር ቤት ነው፡፡ አየህ እስር ቤት ስትሄድ  የምታየው ነገር ሰማይና መሬት ብቻ ነው፡፡ ያኔ ከነፃነት በላይ ውድ ዋጋ ያለው ነገር እንደሌለ ትገነዘባለህ፡፡
* ሂድ ደግሞ ሆስፒታል፣ እዚህ ደግሞ መራመድ ተስኗቸው እራሳቸውን ማዘዝ አቅቷቸው በሰው ድጋፍ የሚመገቡ፣ በሰው ድጋፍ የሚራመዱ ፣የሚፀዳዱ… በሽተኞችን ስታይ ከጤና በላይም ምንም ውድ ነገር እንደሌለ ትረዳለህ፡፡
* ሂድ ደግሞ መቃብር ቦታ፡፡ እንግዲህ ፎቅ ይኑርህ፣ መኪናም ይኑርህ፣ የግልህ ባንክቤትም ይኑርህ፣ ብሄርም ይኑርህ… የግዜ ጉዳይ እንጂ በቁም ያልመጣህበት ቦታ ተጋድመህ ትመጣና አፍር ትለብሳለህ፡፡ መላዕከ ሞት “ይሄ እኮ ከእንዲህ ብሄር ነው” ብሎ የሚያልፍህ መስለሆህ ከሆነ ቂል ነህ ወዳጄ፡፡
* እዚህ ደግሞ በህይወት እንደመኖር ያለ ምን አለ ስትል ልትደመም ትችላለህ፡፡ ስለዚሀ እዚህ ምድር ላይ ሁሉም ነገር ከንቱ ከሆነ፣ ሁሉንም ነገር ትተነው እንደምንሄድ ካወቅን ለምን ወደህይወታችን አስገብተን መኖርስ ያቅተናል?
ግና ችግሩ ምን መሰለህ ሞት እንዳለ ታውቃለህ ዘላለም መኖር ስትሻ ሀቁን መቀበል ይከብድሃል፣ መታመም እንዳለ ስታውቅ  ገንዘብህ ሁሉን የሚፈታ ጤናውን በሙሉ ‘ሚገዛ ይመስልሃልና ያልጋ ቁራኛ ሆኖ መቅረት እንዳለ አትገነዘብም፡፡ ጊዜ በሰው ላይ መሆኑን አታውቅምና ነፃነትህን ተነጥቀህ እስር ቤት መጣል እንዳለም ትረሳለህ፡፡
…….
ማነህ አክቲቪትና ብሄሬ ብሄሬ ፖለቲካ ፓርቲ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ከጀርባችሁ የሚንጋጋውን መንጋ The door of no returnን ከማለፉ በፊት ተቀምጣችሁ አየር ወስዳችሁ ምን እያደረጋችሁ እደሆነ በቅጡ አስተውሉ እንጂ፡፡
ፅጌሬዳ አበባን ስታዩ ምናልባት ማማሯን አይታችሁ ልትቀጥፏትና የግላችሁ ልታደርጓት ትችላላችሁ፡፡ ግን የቀጠፋችኋት ሰከንድ ከመኖር ወደ አለመኖር እያመጣችኋት እንደሆነ እንዳትረሱ፡፡ ሰውና ሃሳባችሁም ሁሉ እንዲሁ እንዲሆን ታውቃላችሁ። በእናንተ ምትክ ይህችን ፅጌሬዳ ንብ አይታት ቢሆን ኖሮ አበባዋን ቀስማ ማር በሰራችባት ነበር፡፡ ማር ደግሞ ምግብ ነው፣ መድሃኒት ነው፣ ማር የመልካም ስራ ፍሬ ነው፡፡ ማሩ እንኳን ቢያልቅ ገፈቱ ጧፍ ሆኖ መንገድ ያበራል፡፡
እናንተ ለዚህች አበባ እንደንቧ ናችሁ? ወይንስ ከመኖር ወደ አለመኖር ልታመጧት የምትሹ ከንቱ ቀጣፊዎች ናችሁ?
ብሄሬ ብሄሬ ማለት ስንኩልነት ነው፡፡ ሰው መሆን በስንት ጣዕሙ፡፡
Filed in: Amharic