>

አንዳንድ ጊዜ ሀገር 'አርብ' ላይ ትሆናለች!! (ዳንኤል ክብረት)

አንዳንድ ጊዜ ሀገር ‘አርብ’ ላይ ትሆናለች!!
 ዳንኤል ክብረት 
ሀገርም እንዲህ ትሆናለች፡፡ አርብ ላይ ስትሆን ፀሐይ የጨለመባት ጨረቃም ደም የለበሰችባት ትመስላለች፡፡ መድኃኒት አልባ ተስፋ አልባ ትመስላለች፡፡ ክፉዎች ኃይል አግኝተው ቅኖች የተሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ወንጀለኞች ደስታ ተጎናጽፈው ንጹሐን መስቀል ሥር ያለቅሳሉ!
አርብ አዳም እየዳነ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ እየተገረፈና እየተሰቀለ ነው፤ ፀሐይ ጨልማለች፣ ጨረቃ ደም ለብሳለች፤ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ሐዋርያት ሸሽተዋል፡፡ መጻጉእ በሐሰት መስክሯል፡፡ ጲላጦስ የእውነት ፍርድ ለመፍረድ ተቸግሯል፡፡ በጥብርያዶስ ባሕር ሲበላ ‹ካልነገሥክ› ያለው ሕዝብ ተገልብጦ ‹ካልተሰቀለ› እያለ ነው፡፡ ያቺ ቀን የክርስትና የመጨረሻዋ ቀን ትመስል ነበር፡፡ የክርስቶስ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ይቀጠቀጣል፡፡ ለዚህም ነበር ወጣቱን ማርቆስን ያባረሩት፡፡ ሐናና ቀያፋ ጉልበት አግኝተዋል፡፡ የጭካኔያቸውን ልክ ሁሉ እያወረዱት ነው፡፡ ዮሐንስ ያለቅሳል፣ እመቤታችን በኀዘን ቆማለች፡፡ ሁሉም ነገር ያበቃና የተቆረጠ መስሏል፡፡
በዚህ መካከል ግን የሚነሡ ሙታን ነበሩ፣ የሚቀደድ የጥል መጋረጃ ነበር፣ ፈያታዊ ዘየማን ገነት እየገባ ነበር፤ ዮሐንስ ለእመቤታችን ልጅ ሆኖ እየተሰጠ ነበር፤ የጲላጦስ ሚስት ስለ እውነት እየመሰከረች ነበር፡፡ ሮማዊው መቶ አለቃ ስለ ክርስቶስ እውነቱን እየተናገረ ነበር፡፡ ግን እነዚህን ጣፋጭ ድምጾች ሌሎች የክፋትና የጨለማ ድምጾች ውጠዋቸው ስለነበር በቂ ሰሚ አላገኙም፡፡ በቂ ሰሚ ያገኙት በኋላ ነው።
ሀገርም እንዲህ ትሆናለች፡፡ አርብ ላይ ስትሆን ፀሐይ የጨለመባት ጨረቃም ደም የለበሰችባት ትመስላለች፡፡ መድኃኒት አልባ ተስፋ አልባ ትመስላለች፡፡ ክፉዎች ኃይል አግኝተው ቅኖች የተሸነፉ ይመስላሉ፡፡ ወንጀለኞች ደስታ ተጎናጽፈው ንጹሐን መስቀል ሥር ያለቅሳሉ፡፡ ትናንሽ ጭላንጭሎችን የሚያያቸው፣ ጥቃቅን ብርቱ ድምጾችን የሚሰማቸው ያጣሉ፡፡ ሁሉም የዋጠውን ጨለማ እንጂ የተሰቀለውን ብርሃን አያይም፡፡ ግን አርብ ያልፋል፤ ቅዳሜም ይነጋል፡፡ እርሱም በዝምታ ይመሻል፡፡ እሑድም ይደርሳል፡፡ ትንሣኤም ይመጣል፡፡ አርብም በእሑድ ትተካለች፡፡ ከአርብ ወደ እሑድ ለመሻገር ግን እንደ እመቤታችንና እንደ ዮሐንስ ያሉ ጽኑዓንን ይፈልጋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ አርብ ላይ ናት፡፡ ግን በቅዳሜ በኩል ተሻግራው እሑድ እንደምትደረስ እናምናለን።
ደግ ደጉን እናስብ፣ በጎ በጎውን እንስራ፣ መልካምነት መልሶ ይከፍለናልና!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!
Filed in: Amharic