>
5:13 pm - Wednesday April 19, 5020

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትጵያ ጦር ሰራዊት!!! ክፍል ፫ (ሻለቃ ላቀው መንግስቴ)

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትጵያ ጦር ሰራዊት!!!
ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ
 ክፍል ፫
★ከኢግዶሌ እሥከ ሀዩማን★
———–
በ1972 መጨረሻ አካባቢ የጁሊያ ዘመቻ የመጨረሻ ምእራፍ ሀዩማን የምትባለውን በቂ የጉርጓዶች ውሀ ያላትንና በጀብሀና በሻእቢያ የተያዘች የአየር ፀባይዋም ከአካባቢው በረሀማ ቦታዎች ነፋሻማ የሆነችውን ቦታ አጥቅተን እንድንይዝ አሠብ በሚገኘው ሕብረት እዝ መምሪያ አሥራ ዘጠነኛን ሻለቃን ለሚመሩት ያንጊዜ ሻለቃ ዘርጋው ወ/የሡሥ በሁዋላ ኮሎኔል የማጥቃት ውጊያ ተሠጠ፡፡
ጁሊያ ዘመቻ ለመጠሪያ ምክንያት የሆነው ጁሊያ የምትባል አነሥተኛ የሞተር ጀልባ ባህር ላይ ይንቀሣቀሡ በነበሩ ወንበዴዎች ታግታ ደብዛዋ በመጥፋቱና ለአሠብ እሥከ 45 ኪሜ ቤይሉል የምትባል የቀይ ባህር ዳርቻ ድረሥ ሻዕቢያ ከባድ መሣሪያ ጭምር እያሥጠጋ አሠብ ኤርፓርትን ጭምር ሥጋት ላይ ሥለጣለ ጁሊያ የተባለው ዘመቻ በመከላከያና በአሠብ ሕብረት እዝ ታቀደ፡፡
ዘመቻው 30ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ በላንድ ክራፍት ጦርና ከባድ መሣሪያ በምትጭን በሠው ቁመት ልክ ከባህሩ መሬት ይዞ ማጥቃቱን ለመከላከል ኢዲ የምትባለውን የጥንት ወደብ እንዲያሥለቅቅ ለ30ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ ግዳጁ ተሠጠ፡፡የሡ ዉጊያ ምን ያህል ጀግንነት እንደተፈፀመበት በሚቀጥለው በሥፋት የምመለሥበትና ከመርከብ ላይ በባህር ላይ ከምድር መከላከያ ከያዘ የሻእቢያ ሀይል ጋር የነበረ አሥደናቂ ውጊያበተብራራ ሁኔታ እገልፀዋለሁ፡፡
አሁን የምተርከው ግን የመጨረሻውን የጁሊያ ዘመቻ ማጠቃለያ ምእራፍ ይሆናል፡፡
ጢዮ ወደአረብ አገሮች በራሣቸው ጀልባዎች የሚመላለሡ የባህር ላይ ነጋዴዎች ያሉባት፡በብዛት ፍየሎችና ጨው እየጫኑ ወደ አረብ አገር ከወሠዱ በሁዋላ በምትኩ ጨርቃጨርቅ ወርቆች፡ኤሌክትሮኒክሥ መሣሪያዎች ወደ ሐገር የሚገቡባት የአፋር ብሔረሠብ የድሮ የወደብ አነሥተኛ መንደር ነች፡፡ከፍተኛ የሆነ የበረሀ ሙቀትና ወበቅ ያላት ሢሆን ሀሉም አባሎቻችን ከወገብ በላይ መልበሥ ሥለሚያሥቸግር ራቁት ይመረጣል፡፡
ነዋሪው አረባዊ መልክ ያለውና ጠይምና ጥቁር ቅልቅል ሢሆን የሙሥሊም ሀይማኖት ተከታዮች ነው፡፡የሢቶቹን ቁንጅና ለራሥ እያደነቁ አይንን ቁንጅና ላይ ጣል እያረጉ መነሁለል ብቻ ተፈቅዶልን በገጠመን የባህል ድንበር  ታሥረናል ፡፡ሀዩማንን ለማጥቃት ወደ ኢግዶሌ የምትባል ቦታ መጠቃት የነበረብን በመሆኑ ጢዮ ለቀን በግምት ወደ 40 ኪሜ በጥልቀት ወደ ውሥጥ ሠሜን ምሥራቅ አቅጣጫን ይዘን በኮ/ዘርጋው መሪነት አንድ ሻምበል ከእዝ የሥበት ሀይሉጋ በማድረግ የተወሠኑ ሁለት ሻምበሎችን ቀደም ሢል ከረንደሎ በሚባል ወዶ ገብ በሚመራው ራሡ ይዞት በመጣው ከ25 የማይበልጠው የሠው ሀይል መሪነት ኢግዶሌ ገብተን ዝግጅት ጀመርን፡፡
ሐዩማን ርቀቷ ከአርባ ኪሜ ያልራቀ ሢሆን ከኢግዶሌ የማጥቃት ትእዛዝ እሥኪሠጠን፡ቀንና ጊዜን የሥለላ ሥራ እየተሠራ መጠበቅ ያዝን ኢግዶሌ በቂ የመጠጥ ውሀ የሌላት ፡ያለችውም አነሥተኛ ውሀ፡የቆየ ከመሆኑም በላይ፡ ትላትል የበዛበት ግመሉም ፍየሎችም የሚጠጡት ፡ቀደም ባሉ ውጊያዎች አሜሪካ ሥሪት የሆኑ በፈንጂ የወደሙ ሪዮ ጀምሥና፡የራሺያ ዚል የጦር የጭነት የወደሙ ተሽከርካሪዎች፡የሚታየበትና አጫጭር የበረሀ ዛፎች አልፎ፡አልፎ የሚታይበት አየሩ ወደ እብደት የሚመራ ከፍተኛ ሙቀት የነበረው ነው፡፡
 
★ኢግዶሊ
 
የሻለቃው ኮሚሣር ሆኜ ከመጀመሪያው የጦር ሀይሎች ፖለቲካ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ኮርሥ ሆኜ ተመርጬ ከመጣሁ ገና ቀናቶች ቢቆጠሩም ቀደም ሢል ከዚሁ ክፍል ለትምህርት የተላኩ በመሆኑ ክፍሉን በሚገባ አውቀው ነበር ፡፡
ሙቀትም ቢሆን አንዱ ፈንጂ መቶት ወላልቆ ከቆመ ሪዮ ጀምሥ መኪና ጋቢና ላይ ወጥቸ ቁጭ ብዬ በየቁጥቋጦ ሥር የተቀመጡ ወታደሮችን ማየት ብቻ ሣይሆን ከመኪናው የተለያዩ ክፍሎች የሚርመሠመሡትን ገበሎዎችና እንሸላሊቶች እያየሁ፡ቁጭ ብያለሁ፡፡ በዕለቱ ደግሞ ኢሊኮፕተር ወደ እኛ እንደምትመጣ ተገልፆም ሥለነበር ከአዲሥ አበባ የቤተሠብ ደብዳቤ ከመጠበቃችንም በላይ የውጊያ ትእዛዝም ጥራዝ እንደሚመጣም ይጠበቃል፡፡ሠአቱ 11.30 ከንጋቱ ሢሆን ሐሩሩን ለመከላከል የተጠለልኩበት መኪና ግለቱ የጋለ ምጣድ ያህል ሥላቃጠለኝ ብድግ ብዬ ከመኪናው ሥወርድ አሸዋዉ ላይ ራሤ ላይ ከሞቀው ኮዳዬ ውሥጥ ሣፈሥ ያረጠብኩትን አሸዋ የሚልሥ ትልቅ ነጣ ያለ እባብ ሣልረግጠው ለጥቂት አምልጨው ራቅ ብየ መጨረሻው ሣየው ቆየሁና ለምን እገድለዋለሁ የመጣሁበት እኔ ብዬ አዛዡ ወዳሉበት ሣመራ የኢሊኮፕተሯ ድምፅ ከሩቅ አየሩን ሠንጥቆ ይሠማ ጀመር፡፡
የማረፊያ ምልክቱን የያዘው ወታደር ሜዳማና በግልፅ አብራሪው ሊያይ የሚችልበት ቦታ ቀይ ባነር አነጠፈ፡፡ሥትጠበቅ የነበረችው ሄሊኮፕተር አርፋ አናቷ ላይ የሚምዘገዘገው ተሽከርካሪ ቀዘፋውን እንዳቆመ፡የመጡ ዶክሜንቶችና የሠራዊቱን የቤተሠብ ደብዳቤዎች አራግፋ በሙቀት ምክንያት ወደ አሠብ ለከፍተኛ ህክምና የሚሄዱ ወታደሮችን ጭና በመጣችበት ሁኔታ ተመለሠች፡፡
የግል የቤተሠብ ደብዳቤዎችን ከተመለከትን በሁዋላ ከበላይ አካል ከለሊት ጀምሮ ወደ ሀዩማን የማጥቃት እርምጃ እንድንሠነዝር የሚያዘውን ትእዛዝ በአዛዡ አማካይነት ዘመቻው ፡የሻምበል አዛዦች ፡ወደው እጃቸውን ለወገን ሀይል የሠጡት የጀብሀ ተዋጊዎች መሪ ከረንደሎ፡በመሆን ቀዳሚ ሻምበሎችን የዙ 23እና የታንክ ተኩሥ ድጋፍ ሠጪ መኮንኑን ጭምር ያቀናጀ ሥብሠባ ተደርጎ ንጋት ላይ ወደ ሀዩማን በውጊያ አሠላለፍ ቀጠልን፡፡
ንጋት ላይ 0500ሠአት ላይ ከሀዩማን ከፍተኛ መሬቶች ተኩሥ ጠላት ከፈተ፡፡ ከሁዋላ ከባድ መሣሪያ ከጠላት የሚተኮሠውን ያብሪ ጥይት ውጋጋን እየተመለከቱ ሁለቱም ታንኮች የተራራውን ፒክ/አናት/ በዙ 23 ተኩሥና በመትረየሦች ያነዱት ጀመር፡፡
ከረንደሎ ቀደም ሢል አካባቢውን ያውቀው ሠለነበር የጠዋቷ ፀሀይ ከመክረሯ በፊት ወታደሮቻችን የሀዩማንን የውሀ ተቆጣጥረው የጀብሀንና የወያኔ ጥምር ማዘዣ ቦታ በጥቂት መሥዋእትነት ሣይዘጋጁ ግባችንን ተቆጣጣጠርን ቁሥለኞቻቸውን የቻሉትን ይዘው የሸሹ ሢሆን ፡እንደ ከተማ በተሠሩ በተራሮቹ መሐል የገነቡዋቸውን ምሽጎች ለእኛ አሥረክበው ድንገተኝነትን አትርፈን ጠዋት 0917 ሠአት ላይ ውጊያው ተጠናቆ ለበላይ ሪፖርት ተደረገ፡፡
★ዋጋ ያሥከፈለ ማጥቃት ★
ቀደም ሢል ሥለሀዩማን ልፅፍ ያነሣሣኝ ያደረግንው ማጥቃት ውጊያ ከባድና መሥዋእትነቱም ሊዘገብ ይገባዋል ከሚል ሣይሆን የመጨረሻው የሀዩማን ቀሪ ትግል መራራ ሥለነበረ ነው፡፡ሀዩማን ጥላ ያላቸው ትላልቅ ዛፎች ያሉዋትና በሥተምዕራብ አቅጠጫ ተደጋግፈው ክብ የሠሩ ተራሮች በመሐከል ደግሞ መተላለፊያ መንገድ ኖሮት ግመሎች በብዛት እየገቡ ወደ ኮማንድ ፖሥቱ ፊት ለፊት ትይዩ ሜዳው ላይ ያሉትን ሁለት ትላልቅ የውሀ ጉድጓዶች እየመጡ በባለግመሎቹ አማካይነት በረጃጅም ገመዶች በታሠሩ የውሀ ማውጫ ከመነዳሪዎች ከእንጨት በተሠራው ትላልቅ ገንዳዎች ላይ የፈሡላቸዋል፡፡
በየቀኑ በርካታ ሠዎችና ግመሎች የሚሠማሩ ሢሆን ተራራዉ ላይ ቦታ ይዞ የሚገኘው 117ኛ ሚሊሻ ብርጌድ ሁለት ሻለቃ የተወሠነ ሀይሉን ተራራው ላይ በመተው ሜዳው ላይ አየወረዱ የቁርቁራ ዛፍ ፍሬ ሢበሉ ከመዋላቸውም በላይ ቀዝቀዝ ያለውን የሀዩማን አየር ይኮመኩማሉ፡፡እኛም ኘንድ የተመረጠ ትልቅ ዛፍ ሥር የእዝ ጣቢያችንን የሞተ መሬት ላይ አድርገን ተጓዥ የበረሀ ነጋዴ መሥለን ሠፍረናል፡፡
የሚያሣዝነው 117ኛ ሚሊሻ ብርጌዱ ተነጣይ ሻለቆቹን የሚመራው አዛዥ ከተራሮቹ ራቅ አድርጎ አንቂ ሀይል ቀንም ማታም ሣያሥቀምጥ ተራራዉን እንደ ፎቅ ቤት ቆጥሮ ለሊት በመኝታ ቀን ደግሞ በተረጋጋ ሁኔታ ጊዜውን ያሣልፋል፡፡ከኛ በሥተቀኝ በሥተ ደቡብ አቅጣጫ በመ/አለቃ ቢንያም አዳል የሚመራው T55 የሚባሉ ሁለት ታንኮችን የታጠቀ ምድብተኛ የተራራውን የመጨረሻ ጠርዝ ተከትሎ ከተራራው ራቅ ብሎ ቦታውን ይዞአል፡፡
 የዙ23 ምድብተኞች በሥተ ሠሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የተራራውን የቀኝ ጠረዝ ተከትለው እነሡም የሞተ መሬት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ከኛ ሁዋላ የህክምና የመገናኛ የመረጃ መሐንዲሥና ጠቅላይ ሠፈሩን የሚጠብቁ የሻለቃው የመቶ አባሎች እንደ አንድ የተጠናከረ ተከላካይ ሀይል ሣይሆን ማእድን ፍለጋ እንደተሠማራ ሀይል ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ሠፍረናል፡፡
፡መጋቢት መጨረሻ ጠዋት ላይ የዘመቻ መኮንኑ ጢዮ ደርሼ መምጣት አለብኝ ብሎ በአንድ ዚል መኪና በዚያው አንዳንድ ጉዳይ ፈፅሞ ሊመጣ በሚመሥል መልኩ ወደ ጢዮ አመራ፡፡ሻለቃ ዘርጋው ወ/ሡሥ በሁዋላ ኮለኔል ቀደም ብለው ከሣምንት በፊት ፍቃድ ይሁን ለሥራ በማላሥታውሠው ሁኔታ አዲሥ አበባ ይገኛሉ፡፡
 እለቱን አካባቢውን ሥቃኝ ቆየሁ፡፡ምሽት ላይ ም/መአ አበራ አባይነህ /ዘመቻው/የማእረግ ጊዜው ደርሦ ሥለነበር ጢዮ የሙሉ መ/አ ማእረጉን አልብሠውት የደሥ ደሥ የቆርቆሮ ጭማቂዎችና የሚበሉ ብሥኩቶች እየበላን ዛፋችን ሥር አሸለብን፡፡በእለቱ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ግመሎች ለሊቱን ሁሉ ሢጓጓዙ አርፍደዋል፡፡117ኛ ሚሊሻ አዛዥ አፓርታማ የተከራየ ይመሥል ለየት ያለውን እንቅሥቃሤ ከግምት ሣያሥገባ የሞቀ እንቅልፍ ውሥጥ ገብቷል፡፡
ሻእቢያና ጀብሀ ከግመሎች ጋር ተመሣሥለው ለሊቱን በሙሉ የተራራውን ወገብ ጨርሠው የእጅ ቦንብ የውጤት ርቀት ድረሥ ተጠግተው በቂ ሀይላቸውን ተራራው ላይ አሥፍረው እንደ ተከራይና አከራይ ተራራው ላይ ከ117ኞች ጋር በደባልነት ያቺን ምሽት ተራራውን ተጋርተዋል፡፡
★በተኩሥ ብርሀን ቀድሞ የነጋው ለሊት
ከንጋቱ 0400 ሠአት ላይ በእጅ ቦንብና በነፍሥ ወከፍ መሣሪያ በ117ኛ ሚሊሸያ ብርጌድ ሁለት ሻለቆች ይዞታ በብርሐን ፍጥነት ወዲያው በቁጥጥር  ሥር ውሎ ውጊያው መልኩን ቀየረ፡፡በእንቅልፍ አለም ውሥጥ የነበሩት ተዋጊዎቻችን በእጅ ቦንብ አካላቸው ተበጣጥሦ ከነፍሥ ወከፍ መሣሪያዎች ድምፅ ጋር ያሥተጋባል፡፡መትረየሦቻቸውን ጠምደው ቁልቁል ኮማንዱ ላይመተኮሥ የጀመሩት ጀብሀና ሻእቢያ በመጀመሪያ እልምታቸው ውጊያውን ለመምራት ተጣድፎ የተነሣው አበራ አባይነህ ላይ አንገቱን በሥታ ደሙ ተረጨ፡፡አልተንቀሣቀሠም፡፡
የማእረግ እድገቱ ደሥታ የሐዘን ማቅ ለበሠ፡፡እኔ ወደ ታንክ ምድብተኞች እንደ በረዶ በሚዘንብብኝ የመትረየሥ ተኩሥ ታጅቤ ታንኮቹን ወደሁዋላ እንድንሥባቸው መ/አ ቢንያም አዳል ጋ ተገናኘሁ፡፡የሞተው መሬት ላይ ባለው ሠራዊት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ደረሠ፡፡ሬዲዮ ኦፕሬተሩ አበራ አባይነህ ሥለተሠዋ ውጊያውን ጌታየ ያሥተባብሩ ብሎ  ሀላፊነቱን አረዳኝ ለማንኛውም ከሕብረት እዝ ጋር ግንኙነት መሥርቶ ሁኔታውን እንዲያሣውቅ አድርጌ ነብሥ ያልዘራውን ውጊያ ለማሥተካከል መሯሯጥ ያዝን፡፡
ጠላት ወደ መሬት እንዳይወረድና  ሁኔታውን በትክክል አይተን ውጊያውን እሥክንመራ ሁሉም ቦታ ይዞ ወደ ከፍታው መሬት ላይ እንዲተኩሡ አድርጌ ግራና ቀኝ በሥፋት ተዋጊው ሀይል እንዲይዝ ትእዛዝ ሠጥቼ በተለይ ጠላት ውሀ እንዳያገኝ ቦታው በዙ23እልምት ሥር ታሥሮ ንጋቱ ወገግ እሥኪል ፍልሚያውን ቀጠልን፡፡
ንጋት ላይ መ/አ ቢንያም ታርጌቱ በትክክል ይታየው ሥለነበር ከተራራው አናት ቋጥኝ ቁልል ጋር እየገመሠ ያወርዳቸው ጀመር፡፡ከረንደሎን በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሥፋት ሄዶ ከጀርባ ተኩሥ እንዲከፍትና በግራ በኩል ደቡቡን ክፍል በመ/አለቃ/ጌታቸው ዳባ በጀርባ አሥፍቶ እንዲገባና በተራራው የፊት ለፊት ደረት የሀምሣ ካሊበር ተኩሥ ጭንቅላታቸውን እንዲደፉ አድርገን ከፊት እያጫወትን በጎንና ጎን በጥልቀት የከበባ መሠል ውጊያ ማድረግ ቀጠልን፡፡
በእልህ የተቆጣጠረውን ቦታ ላለመልቀቅ ጀብሀ የሞት ሞቱን ይታገላል፡፡ቦታውን ለመቆጣጠር ተራራውን ብቻ መያዙ በቂ ነው የሚል አቋም የያዘው ጀብሀ ትልቅ ሥህተት የፈፀመ ይመሥለኛል፡፡አብዛኛው ሀይላችን ሙትና ቁሥለኛ ሆኖአል፡፡ሥለ ሀዩማን ሠራዊቱ በድል ከአሥራአምሥት ቀን በፊት ለሕዝብ በተገለፀ ወር ባልሞላ ጊዜ መልሦ መያዙ ውርደቱ እጅግ ከባድ ነበር፡፡
አሠብም አዲሥ አበባም ከፍተኛ ሽብር በዘመቻ ማእከሎቻችን ተፈጠረ፡፡ኮለኔል ጥላሁንን የአየር ሀይል ተዋጊ ጀቶቻችን አብረው ይደምሥሡን ብዬም ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እሣቸው ግንየተወሠኑ ሠአታት ሞክሩ አይዞህ የሁለተኛ ብርጌድ አንድ ሻለቃ በመ/አ ታደመ በላይነህ ወዳንተ ተንቀሣቅሧል በርቱ አሉን፡፡ውጊያው በሞራል ቀጠልን ፡ ፀሐዩዋ ማቃጠል ጀምራለች ቁሥለኞች በየቦተው የሥቃይ ድምፅ ያሠማሉ ፡ጠላት ውሀ መጠጣት አልቻለም ታንኩንና ዙ23ቱን በሚገባ እየተጠቀምን ከረንደሎና ጌታቸው ዳባ ከሁዋላ በጀርባው ከፍተኛ ምት ያደርሡበት ጀመር ቀሥ እያለ፡ተኩሥና ማፈግፈግ/አንድ እግር በመሬት እየሠሩ መሽሽ ጀመሩ በመጨረሻ የምልክትና ሀይልን የማሠባሠብ ተኩሥ እየተኮሡ ከተራራው ላይ ተንደው ወረዱ፡፡የማሣደድ ውጊያው እንዲቀጥል አድርጌ ሞተን ድል ተቀዳጀን፡፡
የአበራን አሥከሬን ሣየው ከግራ በኩል የገባ የመትረየሥ ጥይት በቀኝ በኩል አንገቱን ቦትርፋ የወጣች ሢሆን የተቃጠለ ደም አሸዋው ላይ ፈሧል፡፡ሙሉ ለሙሉ በደረቱ ተኝቶ አንገቱ ላይ የነበረችው የወርቅ ባለመሥቀል ሐብል የተቃጠለው ደምላይ ተዘርግታለች ያደረገዉን ማእረግ ከትከሻው ላይ ከማንሣቴ በፊት ተገቢውን ሠላምታ ሠጥቼ ማእረጉን ፈታሁ፡፡ተኝቶ ባደረበት የድንኳን ቨራ አልብሼው ወደሌላው ሥራዬ ሄድኩ ቁሥለኛ መሠብሠብ ያዝን ተራራው ላይ ሥንወጣ በየምሽጉ ጠላትም ወገንም ተናንቀው ወድቀዋል፡፡
ወደ ጀነራል ጥላሁን ሬዲዮ አድርጌ ቦታውን መልሠን መቆጣጠራችንን ገልጬ እየመጣልህ ነው የተባለው ጦር ቶሎ እንዲገፋልኝ አሣሥቤ  በተረፈ ሀይል ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ማሥያዝ ጀመርን፡አመሻሽ ላይ ታደመ አንድ ሻለቃ ተጨማሪ ጦር ይዞ ተቀላቀለን ሢዋጋ የዋለውን ጦር ከተራራው ላይ አሥወርጄ ቀብር እንዲፈፅሙና ቁሥለኛ በየጥላው ሥር አሥጠግተው መርዳት የሚቻለውን ያህል ለመርዳት ሞከርን፡፡የእለቱ ክንውን በአሣዝኝነቱ ውሎ አዳርም ቀጠለ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ረፋዱ ላይ አንድ ሂሊኮፕተር አየር ላይ ሆና ጀነራል ጥላሁን ላቀው ያንተን አይነት ሥራ የሚሠራውን ሠው፡ሥም ንገረኝ ብለው እርግጠኛ ቦታው መልሦ በእኛ እጅ ለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆኑ ጠየቁኝ፡፡ ጌታዬ የእኔ አይነት ሥም ነው ያለው አልኳቸው አለቃዬ አሠብ ሻለቃ ላቀው ወ/ሠንበት ሥለነበር በአየር ላይ ተግባብተን ላንድ አደረጉ፡፡ጀነራል ጥላሁን ኮ/ዘርጋው አብረው መጡ፡፡
እንደወረዱ አንገታችንን እያቀፉ ከጉድ አወጣችሁን በሚል የሥሥት አይን እያዩን ለሥብሠባ ተቀመጥን ሂሊኮፕተሯም በምልልሥ ቁሥለኞቹን አመላለሠች፡፡ሀዩማን የነበራት ንፁህ አየር በሠዎች ሬሣ ሽታ አካባቢዋ ተቀይሮ መሠንበቷ ቀጠለ፡፡
★ፋሢካን በጣርማ  በር★
605ኛ ኮር በሜጀር ጀነራል ጥላሁን አርጋው እየተመራ ጣርማ በር ላይ ማዘዣ ጣቢያውን አድርጎ  የፋሢካ እለት 1982 ከመዘዞ ፡ከሠላ ድንጋይ በ120ሚሊ ሜትር በያኔ የሚተኮሠውን መድፍ ማሥተናገድ የጀመረው የቀሪው የኢትዮጵያ የክርሥትና እምነት ፆሙን ገድፎ መልሦ አረፍ ለማለት በሚመቻቾበት ንጋት 04:30ሠዓት ላይ ነበር፡፡
 የወያኔ ግዳጅ መዘዞንና ከሠላ ድንጋይ ሠሜን ያሉትን ከፍተኛ መሬቶች በመቆጣጠር ደብረ ሢና ወርዶ ዋናውን መንገድ በመቆጣጠር ከደሤ ጀምሮ ያለውን ኮምቦልቻ፡ከሚሤ፡አጣዬ፡ሸዋሮቢት፡ድረሥ የመንግሥትን ግንኙነት ማቋረጥና በደሤ ፡በኮምቦልቻ አጣዬ ካራቆሬ የነበሩ የኮሩን ወታደራዊ ክፍሎች እንደጋንግሪን ከጥቅም ውጭ አድርጎ በቀላሉ የርእሠ መንግሥቱን መቀመጫ አዲሥ አበባን ለመቆጣጠር ነበር፡፡
ወያኔ፡ የካቲት፡ አሉላና ፡ ቀይ ኮከብ፡እንዲሁም ኢህዲን የኦህዲድ ተዋጊ ሀይሎች ፡ኢህዲን እንደውም ሠንገዴ ብሎ ያደራጀው ሀይል ተሣትፈው ነበሩ፡፡
በኛ በኩል በተለያዩ ውጊያዎች የተዳከመው 11ኛ ክ/ጦር ፡ካራቆሬ ከፊል ሀይሉን ወደጣርማ በር እንዲሥብ የተደረገው 2.81አንደኛ ሥፖርታ ብርጌድ የኮሩ ጠቅላይ ሠፈር ልዩ ጥበቃ ሻለቃና ቃኚ ሻምበል ወዘተ ተሠልፈው ወናውን ውጊያ መዘዞ ላይ ተይዘውታል፡፡የኮሩ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ከሠላ ድንጋይ በሥተቀኝ የተጠመዱ ከባድ መሣሪያዎች መፈናፈኛ የከለከሉን ሢሆን የዋናውን መንገድ ተከትሎ አንኮበር ተብላ ዝንጀሮች የሚወጡና የሚወርዱባትን ከከባድ መሣሪያ አደጋ የሚከላከል የተፈጥሮ መሬት በመያዝ ጀነራል ጥላሁን የመዘዞውን ውጊያ ይመራሉ፡፡
በአየር ለማሥደብደብ የማይመቸው ይሄ ግንባር በንፁህ ገበሬዎችና ቤተሠቦቻቸው ላይ አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄም ይጠይቅ ነበር፡፡ ውጊያው በጣም በተፋፋመ መልኩ የጀመረ ቢሆንም እኛን እያወከ በነበረ የወያኔ መድፍና የዙ23መሣሪያ ላይ በኛ መድፈኞች የተኩሥ ቀጠናቸው እይታ ውሥጥ በመግባቱ በሥብሥብ የተጣመረ የመድፍ የአፀፋ መልሥ አፍህን ያዝ ተብሎ ዝምታን መርጧል ፡፡
የመዘዞን ተረተር ይዞ የጣርማ በርን መንገድ ዘግቶ ድሉን ሊጨብጥ ያሠበው ወያኔ ውጊያውን ወደሚመሩ አለቆቹ ጬኸት ጀመረ፡፡ሀይል ከሁዋላ ቢያሥጠጉለትም በጀነራል ጥላሁን አረጋው ያለማንም ጣልቃገብነት ይሠጥ የነበረው አመራር ተዋጊውን ጦራችንን እንደ ብረት አጥር አጠንክሮ ወያኔ የማይሞከረውን ሞክራ ሙትና ቁሥለኛዋን አዝረከረከች፡፡
የደብረ ብርሀን አሥተዳዳሪ በከባድ መሣሪያ እየተቀጠቀጥን በነበረ ጊዜ ፋሢካን ብቻዬን ለምን ብለው ማዘዣ ቦታ ለነበርን ምግብ አሠርተው የመጡ ቢሆንም በችግሩ ውሥጥ አብረውን ሊፈተኑ የግድ ነበር፡፡ጀነራል ጥላሁን ወደ መጡበት እንዲመለሡ ቢወተውቱም አሻፈረኝ አሉ፡፡የመዘዞና የሠላ ድንጋይ ድንጋይ ድምፁ እየራቀ ወያኔ እየሸሸ የነበረው ኪሣራ በቀላሉ ይጠገናል በማይባል መልኩ ከረፋዱ 11.30 አካባቢ የውጤታችንን ዜና በድል አብሥረን ቢያንሥ ለአንድ አመት የዚህ አይነት ምኞት እንዳያልሙ ሆነ፡፡
ሁኔታው እንደተረጋጋ በፆም ያረፈደ ሆዳችንን ጥያቄውን ለመመለሥ ምንም እንዳልተፈጠረ በሚመሥል ሁኔታ የጓድ ጌታቸው አገልግል ተፈቶ ለመመገብ ሥንዘጋጅ ወደ ደብረ ሊባኖሥ የሚያመሩ ቢጫ የመነኩሤ ቆብን ቢጫ የመነኩሤ ቀሚሥ ያጠለቁ በግራ ትከሻቸው በቆዳ በተለበጠ መያዣ ዳዊት አንግተው አንድ በጭቃ በተሠራ ባዶ ቤት ቁጭ  ወዳልንበት እንድንዘክራቸው ተማፀኑ፡፡ ጀነራል ከፖሊሦቻችን አንዱን ወደ እዚህ ጥሩዋቸው አሉና ትእዛዝ ሠጡ፡፡ ይቀጥላል
Filed in: Amharic