>
5:13 pm - Saturday April 19, 3428

‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ የቀየረችው ታሪካዊት ቀን!!!››  (ልዑል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል)

‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ የቀየረችው ታሪካዊት ቀን!!!›› 
ልዑል አምደ ጽዮን ሰርጸ ድንግል
የወልወል ግጭት 84ኛ ዓመት መታሰቢያ – 
ፋሺስት ኢጣሊያ … ኢትዮጵያን ለመውረር እንደሰበብ የተጠቀመችበት ታሪካዊው የወልወል ግጭት (Wal-Wal Incident) የተከሰተው ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት (ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም) ነበር።
ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት (Italian East Africa Colony) አካል ለማድረግ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅና ጊዜ ስትጠብቅ ቆየች፡፡ እ.አ.አ በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የውርደት ማቅ እንደሚበቀልና ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አካል እንደምትሆን መዛት የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡
ለዚህም እንዲያመቸው የኢጣሊያ መንግሥት ራስ ተፈሪ መኮንን ኢጣሊያን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ቪቫ ኢትዮጵያ›› እያለ ወዳጅ መስሎ ሸነገላቸው፡፡ እስከ አፍንጫው የታጠቀ በርካታ ጦር በኤርትራና በሌሎች  የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካባቢዎች ላይ ያከማች ጀመር፡፡ የጦሩን ውጤታማነት አስተማማኝ ለማድረግም ሀኪሞችን፣ ሰላዮችንና ሌሎች ሙያተኞችን አብሮ አጓጓዘ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን›› የግዛት ባላባቶችን በጥቅም በመደለል ማስኮብለሉንና መረጃ መመንተፉንም ተያያዘው፤ በጨካኝነታቸው የታወቁትን እነ ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ፣ ፒትሮ ባዶሊዮ፣ ሩዶልፎ ግራዚያኒና ሌሎች የጦር አለቆችን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ላከ፡፡
ጣሊያን ይህንን ዝግጅት ካጠናቀቀች በኋላም ኢትዮጵያን የምትወርበት አጋጣሚ መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ረቡዕ ዕለት፣ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ (British Somaliland) መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው፡፡ (ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ) … ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል ሰውነት ቆሰለ፤አካል ጎደለ … የሰው ሕይወት ጠፋ፡፡ ኢትዮጵያም ስሞታዋን ለኢጣሊያ መንግሥት ስታቀርብ፤ የኢጣሊያ መንግሥት ይባስ ብሎ የተበደለ መሆኑን በመግለፅ የሚከተሉትን ‹‹የመደራደሪያ ጥያቄዎች›› አቀረበ፡፡
፩. የወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም ወልወል ድረስ ሄደው እዚያ የሚገኘውን የኢጣሊያ የጦር መሪ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ አንድ የኢትዮጵያ የጦር ጓድ ለኢጣሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጥ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለተደረገው የማጥቃት እርምጃ ኃላፊ የሆኑት ባለስልጣኖች ሁሉ ተይዘው የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እጅ ነስተው እንዲሻሩና ተገቢውን ቅጣት በአስቸኳይ እንዲያገኙ፣
፪. የኢትዮጵያ መንግሥት ለቆሰሉት፣ አካላቸው ለጎደለውና ለሞቱት የኢጣሊያ ወታደሮች ካሣ የሚሆን 200ሺ ማርቴሬዛ (ጠገራ ብር) እንዲከፍል እንዲሁም
፫. በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈፅመው ከባድ ጥፋት ያደረሱት ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ተይዘው ለኢጣሊያ መንግሥት እንዲሰጡ … በማለት የለየለት የትዕቢት ጥያቄ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሃሳብ ሳይቀበል ቀረ፤ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካ ቀረ፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረሯ እንደማይቀር ሲታወቅ፣ ከዓድዋ ድል በኋላ ራሷን በኢኮኖሚ ሳታበለፅግ ለ40 ዓመታት ያህል ባለችበት ቆማ የቀረችው ኢትዮጵያ መሳሪያ ለመግዛት እንቅስቃሴ ብታደርግም ቄሳራውያኑ ኃይሎች በመመሳጠር እንዳይሳካላት አደረጉ፡፡
ከዚህ በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅበት የቆየችውን እቅድ እውን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን መውረር ጀመረች፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግጋት ፈፅሞ የተከለከሉ የጦር መሳሪያዎችን (የጦር አውሮፕላን፣ የመርዝ ጋዝ፣ …) ጭምር በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የጦር ወንጀል ፈፀመች … የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ታሪክ የቀየረ ክስተት።
የወልወል ግጭት ኢጣሊያ ለብዙ ዘመናት ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ለመውረር የነደፈችውን እቅዷን ለማሳካት እንደሽፋን የተጠቀመችበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
የዘንድሮውን የወልወል ግጭት መታሰቢያ ልዩ የሚያደርገው ግጭቱ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም ሲከሰት ዕለቱ ረቡጭ ነበር፤የግጭቱ 84ኛ ዓመት መታሰቢያ (የዘንድሮው) ረቡዕ ዕለት ላይ መዋሉ ነው፡፡
የመረጃው ምንጮች … 
፩. መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)
 
፪. የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት (ጳውሎስ ኞኞ)
 
፫. የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት (አምባሳደር ዘውዴ ረታ)
 
፬. የኢትዮጵያ ታሪክ ፡ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ፡ ከወልወል እስከ ጎንደር (ተድላ ዘዮሐንስ ዘውዴ) 
 
፬. ልዩ ልዩ ድረ-ገፆች
Filed in: Amharic