>

በየአካባቢው እየታየ ባለው የጎሳ ግጭት ሕገ መንግሥት ተብዬው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

በየአካባቢው እየታየ ባለው የጎሳ ግጭት ሕገ መንግሥት ተብዬው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ባገራችን  እየታየ ያለውን  መጠነ ሰፊ የጎሳ ግጭት በሚመለከት  ብዙ ሰው  «የለውጥ ሂደት»  እየተባለ የሚቀርበው ነገር  ያልጣማቸው ሰዎች እያቀነባበሩት ብቻ የሚከሰት  አድርጎ ይቆጥረዋል። ይህ እጅግ ስህተትና አገራችን ያጋጠማትን ችግር ካለመገንዘብ የሚመጣ አላዋቂነት ነው። በሁሉም የአገራች አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው የጎሳ ግጭት ማንም አራጋቢ ሳያስፈልገው አገዛዙ በተዋቀረበት ሞተር እየተነዳ በራሱ ጊዜ የሚፈነዳና  ባሕሪያዊ ነው። ይህ ማለት ግን ስርዓቱን የዘረጉት ነውረኞች እጅ እግራቸውን አጥፈው ይቀመጣሉ ማለት አይደለም። ሆኖሞ ግን ሕገ መንግሥት ተብዮው የፈጠረው የአፓርታይድ ስርዓት የጎሳ ግጭት  ማንም ሳይነካው በራሱ የሚከሰት ባህሪያዊ ነው። ሕገ መንግሥት ተብዮው የአፓርታይድ ደንብ የጎሳ ግጭት መፈጠሪያ  ማኅጸን ነው።   ስለዚህ ዛሬ ፍሬው በመለቀም ላይ የሚገኘው  ዘረኝነት ወይንም ጎሰኛነት የወለደው የርስ በርስ ግጭት  ሕገ መንግሥት ተብዮው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም።
ከሰሞኑም «ኦሮምያ ክልል» እና «ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል» በሚባሉት የአፓርታይድ ዞኖች  ውስጥ ሲፈጸም  የሰነበተው  ዘግናኝ ግድያ፣ ግፍ፣ ጭካኔ፣ መድፈር፣ ዝርፊያና የንብረት ማውደም ብዙ ሰው እንደሚያስበው «ሕገ መንግሥት» የሚባለው ነገር እየተጣሰ አይደለም፤ እንዴውም እየተተገበረ እንጂ።
ሕገ መንግሥት ተብዮው የተጻፈው «ለዘመናት ነበረ» የተባለውን የተዛባ «የጨቋኝና የተጨቋኝ »፤ «የሰፋሪና የነባር» ብሔር፣ ብሔረሰቦች ግንኙነት ለማጥፋት ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ በሚባለው ክልል ውስጥ «ነባር» ከተባሉት ነገዶች ውጪ  ሕገ መንግሥት ተብዮው ለሌላው አስተማማኝ  የሕይዎት ዋስትና አይሰጥም።
በሕገ መንግሥቱ መሰረት የክልል ተብዮው  ባለቤት ነባር የተባሉት አምስቱ  ብሔረሰቦች ብቻ ናቸው። ከነሱ  ውጭ ያለው መጤና ሰፋሪ ቅኝ ገዢ ነው ተብሏል። ነዋሪው አማራ ከሆነ ደግሞ ጨቋኝ እንደሆነ ተደርጎ ተረክ ተፈጥሯል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት መጤና ሰፋሪ የተባለው ቤንሻንጉል ጉሙዝ በተባለው ክልል ውስጥ  መኖር የሚችለው በነባር ተብዮዎቹ  ችሮታና ተከራይቶ ብቻ ነው። በሕገ መንግሥቱ መሠረት “ክልልህ አይደለም” የተባለ «ብሔር፣ ብሔረሰብ» ዜጋ አይደለም።
ዜጋ ካልሆነ ጉዳዩ የሚታየው በሰብዓዊነት እንጂ እንደ ዜጋ ተቆጥሮ አይደለም። በሰብዓዊነት ደግሞ እንደ ሰው ሁኔታ ይለያያል። ስለዚህ ሕዝበ አዳም ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር እያልህ  በሰልፍ የምትጠይቀው ሕገ መንግሥት ተብዮው የሰጠህ «መብት» እየተከበረልህ እንጂ ሕገ መንግሥቱ የሰጠህ መብት እየተጣሰብህ አይደለምና የምትጠይቀውን እውቅ!
ደግመን ደጋግመን ተናግረናል። የኢትዮጵያ ችግሮች ምንጭ  ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለም  የወለደው ሕገ አራዊት ነው። ከዐቢይ አፍ ማር ቢዘንብ እንኳ በተግባር ተፈጻሚ የሚደረገው ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው ርዕዮተ ዓለም  የወለደው ሕገ መንግሥት ተብዮ ነው። ጸረ ሰብ፣ ጸረ ሀገርና ሕገ ወጥ የሆነው የወያኔ ሕገ አራዊት እስካለ ድረስ የሕግ የበላይነት፣ ንብረት የማፍራት፣ ዜጋ የመሆን፣ የሕይወት ጥበቃ፣ ወዘተ የሚባሉ መብቶች የሉህም።
ባጭሩ የጭካኔ አስተሳሰብ የወለደው የፋሽስት ወያኔ ሕገ አራዊት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ እስካልተወገደ ድረስ ክልልህ አይደለም በተባለው አማራና ኦሮሞ ላይ ዛሬ ቤንሻንጉም ጉሙዝ ክልል በሚባለው  እየደረሰ ያለው  ሕገ መንግሥት ተብዮው የወለደው ዘግናኝ  ግፍና ጭካኔ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በየተራ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ መፈጸሙ የማይቀር ነው።
የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለምና ዋለልኝ መኮነን የሚባለው ትምህርትን ያልጨረሰ የሰፈር ጢቦ በፈጠረው እስር ቤት ውስጥ የታጎሩትን «ብሔር፣ ብሔረሰቦች» ለማስፈታት በመለስ ዜናዊ እሳቤ የተወለደችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የተፈጠረችበት የ ያ ትውልድ ጸረ ሰብ ትርክት ከነ ግሳንግሱ ከስሩ ተለቅሎ ዋጋ እንዲያጣ ተደርጎ እስካልተወገደ ድረስ አንዱ ብሔርተኛ ሄዶ ሌላው ብሔርተኛ ቢመጣ የበላውና የጠገበውን ሸኝቶ የራበውና ሁሉ ብርቁ የሆነውን ከመተካት በስተቀር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳች ጠብ የሚያደርግለት ነገር የለም። አገዛዙ  የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለምና ሕገ አራዊት ሳይወገድ እየተፈጠሩ የሚገኙነት ባሕሪያዊ  የጎሳ ግጭቶች «የለውጥ ሂደት»  እየተባለ የሚቀርበው ነገር  ባልጣማቸው ሰዎች ብቻ ማሳበቡ ለችግሮቻችን መፍትሔ ሊሆን አይችልም! እነሱ ባይኖሩም  ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት ሕገ አራዊትና ርዕዮተ ዓለም እስካልተቀየረ ድረስ  የጎሳ ግጭትና የእርስ በርስ መከሳከስ አይቀርም፤ ባሕሪያዊ ለው ናም
Filed in: Amharic