>

መጭውን ምርጫ ለማሰናከል ከወዲሁ እየተቀመጡ ያሉ እንቅፋቶች!!! (መሳይ መኮንን)

መጭውን ምርጫ ለማሰናከል ከወዲሁ እየተቀመጡ ያሉ እንቅፋቶች!!!
መሳይ መኮንን
እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ጥርጣሬን የሚጭር ነው። ቋሚ አድራሻ የሌለው ሰው ነዋሪ አይደለም። በቃ! ነዋሪ ላልሆነ ሰው በየትኛውም ፎርምና መስፈርት በጊዜያዊነትም ይሁን በሌላ መታወቂያ የሚሰጥበት አሰራር ህገወጥ ነው ። መስተዳድሩ ይህን እርምጃ ለመውሰድ የፈለገበት የትኛውም ምክንያት ህጋዊ አይሆንም። ነዋሪ ላልሆነ ሰው መታወቂያ በጊዜያዊነት መስጠቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉት መስተዳድሩ የሚጠፋው አይመስለኝም። ከህዝብ የተደበቀ ሌላ አጀንዳ ከሌለ በስተቀር።
በተለይ የአዲስ አበባ ጉዳይ አወዛጋቢ በሆነበት በዚህን ወቅት ሌላ ቀውስ የሚፈጥር ተግባር መፈጸም ተገቢ አይደለም። ምርጫው በተባለው የጊዜ ሰሌዳ የሚካሄድ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ግልጽ ያልሆነ አሰራር የምርጫውን ታአማኒነት ከወዲሁ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል። በመጪው ምርጫ የአዲስ አበባን መዋቅር ለመቆጣጠር አሰፍስፎ ያለው ሃይልን የሚጠቅም ውሳኔም ይመስለኛል።
የአዲስ አበባ መስተዳድር መረጋጋትን የሚያውኩ፡ ግጭትን የሚጭሩ ውሳኔዎችን በዚህን ወቅት መውሰድ የለበትም። ጊዜው መሰከንን የሚጠይቅ፡ በከፍተኛ ሃላፊነት የተሞላበት እርምጃና ሀገራዊ ስሜት የሚሻገሩት እንጂ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬን የሚያነግሱ ውሳኔዎች የሚሰጡበት አይደለም። መስተዳድሩ የቋሚና ነባር ነዋሪዎች መሰረታዊ የሆኑ እንደተራራ የተከመሩ ጥያቄዎችና ውስብስብ አንገብጋቢ ችግሮች ከፊቱ ተደቅነው ቋሚ አድራሻ ለሌላቸው መታወቂያ እሰጣለሁ ብሎ መወሰኑ የጤና አይመስለኝም። የሚቀድመው ይቅደም።
ልዩ መታወቂያ ማለት ምን ማለት ነው!!
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቢሮ ልዩ መታወቂያ ለመስጠት መመሪያ እያዘጋጀ እንደሆነ ሰማሁ።በረቂቅ መመሪያው መሰረት መታወቂያ የሚያገኙት   ተንቀሳቃሽ ነጋዴወች፣ከቀድሞ መኖሪያቸው መሸኛ ማምጣት የማይችሉ፣የጎዳናተዳዳሪወች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ከመከላከያ የተቀነሱና የመሳሰሉት እንደሆነ ተገልፅዋል።
በሀገራችን በቅርቡ ሊካሄድ ከታሰበው የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም ከሁለት አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚካሄደውን ምርጫና የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ዋና መነጋገሪያ በሆነበት ሰአት ከቀድሞው አሰራር የተለየ መመሪያ አውጥቶ መታወቂያ ማደል የአዲስ አበባን ህዝብ ስብጥር በመወሰን ረገድ ጥርጣሬን ስለሚያስነሳ ሊታሰብበት ይገባል።
በኔ እምነት ከሰማይ የሚወርድ የቀድሞ አድራሻ የሌለውና መሸኛ ማምጣት የማይችል ሰው ልዩ መመሪያ ወጥቶ ልዩ ድጋፍ ለማድረግ የምንጣደፍበት ጊዜ ላይ አይደለንም ። የመጀመሪያውን ረቂቅ መመሪያ የአዲስ አበባ ከንቲባ የህግ አማካሪ በተገኙበት በሳሬም ሆቴል ውይይት መደረጉን ሰምተናል።
Filed in: Amharic