>

የኢትዮጵያ የድንበር ግጭት አፈታት ሕግ፡ ተርሚነስን ፍለጋ!!! (በውብሸት ሙላት)

የኢትዮጵያ የድንበር ግጭት አፈታት ሕግ፡ ተርሚነስን ፍለጋ!!!
በውብሸት ሙላት
– ገለልተኛ የድንበር ኮሚሽን እንደ አማራጭ)
ኢትዮጵያ እልባት ያላገኙ በርካታ የድንበር ጉዳዮች አሉባት፡፡ከአዋሳኝ አገራት ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጥም በክልሎች እና ከዚያ በታች በሚገኙ አስተዳደራዊ እርከኖች ላይ የድንበር ጉዳይ አሁንም ቢሆን እየቆየ የሚነሳ ወይንም ደግሞ የሚያገረሽ ግጭትን እያስከተለ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ከሁሉም አዋሳኞቿ ጋር ያላለቀ የቤት ሥራ አለባት፡፡ በመሆኑም፣በውጭም በውስጥም ግጭት ያስነሱ ወይንም ሊያስነሱ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡
ከውጭ ከኤርትራ ጋር በድንበር ተጋጭተናል፡፡ ከሱዳን በተለይም በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ ጉዳዩ አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ከኬንያ በኩል የሚነሱ ጥቃቶችም እንዳልቆሙ ይታወቃል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋርም እንዲሁ የጎሳ ግጭቶች አሉ፡፡ የሶማሌም ቢሆን አለመጠናከሯ በጀ እንጂ በድንበር አካባቢ ግጭት አይነሳም ማለት በደርግ ጊዜ የነበረውን ጦርነት መርሳት ነው፡፡ ተመሳሳይ ብሔሮች በኢትዮጵያና በአዋሳኝ አገራት መገኘታቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያወሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ክልል ከክልል ጋር ያላለቁ የድንበር ወይንም ወሰን ጉዳዮች አሉ፡፡ ግጭት ያስነሱ እና አሁንም በግጭት ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ ክልሎቹ እንደ አንድ የመስተዳድር መዋቅር እና እንደ መንግሥት ግጭት ውስጥ ባይሆኑም እንኳን የብሔር ግጭቶች ግን አሉ፡፡ በወልቃይት የሚኖሩ አማሮች የክልል ለውጥ በማንሳታቸው ግጭት ተከስቷል፡፡በአማራና በአፋር፣በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ (ከሲዳማ፣እንዲሁም ከጌዴዮ ብሔሮች ጋር) በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ውዝግቦች ንብረት ወድሟል፤የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡
በተለይ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሰው ሕይወት እንደጠፋ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደ ተዘገበው ደግሞ በግጭቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ ኃይል ፖሊስም ተሳትፎ ተጨምሮበታል፣ ይላሉ፡፡ ግጭቱ አሁንም ቢሆን አልቆመም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም የድንበር ግጭት ሕጋዊ መፍትሔዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ይሁን እንጂ መፍትሔዎቹ ከግጭቶቹ መንሥኤ፣ በግጭቱ ውስጥ ከሚሳተፉት አካላት ማንነት፣ ግጭቶቹን የመፍታት ድርሻ ያለባቸው አካለት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ እነሱም በስሱ ይዳሰሳሉ፡፡ የሕጎቹን ክፍተት እና የተቋማቱን ጎደሎነት ለማጠየቅ እና መፍትሔዎችን ለመጠቋቆም የሚያስችል እገዛ ለማገኘት ሲባል የአንዳንድ አገራትን ተሞከሮ መቃረማችን አይቀርም፡፡
ስለ ድንበር ግጭት ምንነት እና  መንሥኤዎች፤
የድንበር ግጭት ስንል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚጋጩት አካላት ብሔሮች ናቸው፡፡ ብሔርን የደረቡ የድንበር ግጭቶችን ወይንም ቢያንስ ማንነትን (የጎሳ፣የነገድ…) መሠረት ያደረጉትን ማለታችን ነው፡፡ ጥቅል የሆነው የግጭቱ ይዘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ወይንም የግዛት ሊሆን ይችላል፡፡ የግጭቱ መነሻ ምንም ይሁን ምን ሕይወት ይቀጠፋል፤የሰብኣዊ መብት በተለያየ መልኩ ይገሰሳል፤ንብረት ይወድማል፡፡ ብሔርን ወይንም ማንነትን መሠረት ወዳደረገ የርስ በርስ ጦርነትም ሊያድግ ይችላል፡፡
በአገር ውስጥ የሚከሠቱት ግጭቶች በአብዝኃኛው ከሃብት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሃብቶቹ፣ የግጦሽ ሳር ወይንም ውሃ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን ደግሞ ከሀብት ወደ ግዛት ይገባኛልነት እየተቀየሩ መምጣታቸውን በቅርብ ይፋ የተደረጉ ሌሎች ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከአስር ዓመት በፊት በኦሮሚያና የቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የተከሠተውን ግጭት በአስረጅነት በማቅረብ ዶክተር አስናቀ ከፋለ ለዘመናት አብረው በአንድነት  የኖሩት ድንበር ሲካለል መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሞዎች መካከልም ቢሆን  በተለይ ጉጂ፣ጋሪ እና ገብራ ጎሳዎች አብረው ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ቢሆንም ድንበር ወይንም መለያ ሲሰራ አልፎ አልፎ ጥል መፈጠሩ ገሃድ ሆኗል፡፡ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ቦታዎችን ማካለል ሀብትን  እንደ ቀድሞው ለመጋራት በስምምነት ለመጨረስ ወይንም ተስማማተው ለመኖር፤ ብሔርን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ሲመሠረት ትብብሩም፣ስምምነቱም ከሚመሳሰሉት ብሔሮች ወይንም ቡድኖች ጋር ብቻ ስለሚሆን እና ድንበርን መተላለፍ ስለሚመጣ ግጭት ያመጣል፡፡
ጉዳዩ የበለጠ የሚባባሰው ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ ብሔሮች ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚገናኙበት አካባቢን (ethnic frontier) በድንበር ለመለየት በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ለዘመናት ተቀላቅለው በመኖራቸው የፈጠሩትን የእርስ በርስ ግንኙነት የፖለቲካ ወሰን ሲሰመርባቸው የቀደመው የኑሮ ይትባሃላቸው በቀላሉ ስለማይቆም ግጭትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ወሰን ሲካለል ሕዝቦች ወደ የትኛው የአስተዳደር ቀጠና መካለል እንደሚፈልጉ ወይንም እንዳለባቸው ማንነታቸውን ከተለያዩ ጥቅም ጋር አቆራኝተው ከወሰኑ (utilitarian self-identification) በኋላ በድጋሜ ማንነትን መቀየር (identity switching) ሊመጣ ስለሚችል፣ ማንነታቸውን መቀየር ሲፈልጉ ግጭት ይፈጠራል፡፡
ማንነትን ለመቀየር የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች በእነዚህ አከባቢዎች ይበዛሉ፡፡ ከተለያዩ ብሔሮች መወለድ ዋናው ነው፡፡ ለመቀየር የወዲያው ምክንያት የሚሆኑት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መለያየት፣ በመሠረተ ልማት መለያየት፣ በተሻለ የሥራ ዕድል መኖር ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ እነዚህን ሁኔታዎች ከማንነት ጋር መያያዝ ይከተላል፡፡ በመሆኑም፣ ድንበሩ ረግቶ ላይቆይ ይችላል፡፡
ግጭቶቹ የድንበር ሆነው በክልሎች ውስጥም ሊነሱ ይችላሉ፡፡ መነሻቸው የማንነት ይታወቅልኝ፣ ራሴን የማስተዳድርበት ወረዳ፣ ዞን ይከበርልኝ ሊሆን ይችላል፡፡ አካባቢውንም የራስ አድርጎ የመቁጠር ነገር እና ሌሎቹን ማግለል እና መጤ ማድረግም  አለ፡፡
ዝርዝር የድንበር ግጭቶቹ  እንደ ማኅበረሰቡ የአኗኗር ሁኔታም ሊለያይ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር አርብቶ አደር የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ግጭቶቹ ይበዛሉ፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወራቸው አንዱ መነሻ ቢሆንም ለወዲያው የሚያጋጫቸው ግን የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡በአኗኗር ዘይቤ በሁለቱም ወይንም በአንድ በኩል ያሉት ብቻ አርብቶ አደር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አርብቶ አደር ሲባል በአንድ አካባቢ ረግተው የማይኖሩትን  ለማለት ነው፡፡ ለግጦሽ የሚሆን ምግብ እና ውሃ የመፈለግ እና ውድድርም ውስጥ የመግባት ሁኔታ የብሔር ልዩነቱን እያሰፋው እንደሚመጣ ግልጽ ነው፡፡ ፍለጋውም፣ ጥቃቱም፣ መከላከሉም እንዲሁ ብሔር መሠረት አድርጎ ስለሚከናወን ማለት ነው፡፡
አርሶ አደር የሆነው ሕዝብ ባለበት አካባቢ በርካታ ግጭት ሲከሰት አይስተዋልም፡፡ ለዘመናት መሬቱን በገበሬዎች የተያዘ ስለሆነ መገፋፋት እና መንቀሳቀስ  ስለማይኖር ሊሆን ይችላል፡፡ አልበለዚም ግጭቱ በግለሰብ ደረጃ የሚወሰን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ልካለል በሚል ምክንያት ሲከሠት ይስተዋላል፡፡ መነሻው የመልካም አስተዳደር እጦት እና በማንነት መጨቆን ሊሆን ይችላል፡፡ ድንበሮች በግጭት ማግስት በጥልቀት ሳይታሰብባቸው እና ጥናት ሳይደረግባቸው የተካለሉበት ሁኔታ ስላለ እና የነዋሪው ፈቃድ በትክክል ስላልታወቀ ወይንም የክልሎችን ባሕርይ ማለትም ከቀድሞው በምን እንደሚለዩ ካለመወቅ በመነጨ ስምምነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ድንበር የመለወጥ ፍላጎት ይመጣል፡፡
ከእዚህ በተጨማሪም ከውስጥም ከውጭም ያለው የፖለቲካ ትኩሳትም (ለአብነት ነጻ አውጭ ድርጅቶችን ማንሳት ይቻላል) ግጭት ኮትኳች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡በዚህም ይሁን በሌላ ምክንያት ውሎ ሲያድር የብሔር ማንነትን አጥብቆ መፈለግና ወደሚመሳሰላቸው ክልል ለመካለል መሻት ሲነሳ ሊያጋጭ ይችላል፡፡
 
 ድንበርን የሚመለከቱት ሂደቶች
የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ሁለት ላይ እንደተገለጸው  የአገሪቱ የግዛት ወሰን (ድንበር) የክልሎቹ ወሰን ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ ይሄም አንቀጽ በዚህ መልኩ መደንገግ እንደሌለበት፣ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሉዓላዊ አገራት ሁሉ፣ የራሷ የሆነ ዳር ድንበርና አዋሳኞች ሊኖሯት እንደሚገባ ክርክር እንደነበር ከተለያዩ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይቀር የሚወሰነው በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት ነው እንደማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ክልሎች አዋሳኞቻቸውን ብሎም ድንበራቸውን የደነገጉ ቢሆንም የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ግን የክልሉ ወሰን የዞኖቹ እና የወረዳዎቹ ነው በማለት ደንግጓል፡፡
ይሁን እንጂ እንኳንስ ወረዳ እና ዞን ይቅርና ከልሎችም ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ስለማይችሉ ይህ ዓይነቱ በክልል፣በዞን እና በወረዳ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን በተለይም ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር የምትዋሰንባቸውን ድንበሮች መለየት ለአፈጻጸምም አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልሎቹ ከሉዓላዊ አገራት እና ከሌሎች ክልሎች ጋር ይዋሰናሉ፡፡ ከሌሎች አገራት ጋር በሚዋሰኑበት ጊዜ ጉዳዩ ዓለማ አቀፍ ሲሆን፣ ከሌላ ክልል ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ምክንያት የሚነሱት ጉዳዮች ደግሞ የፌደራል ይሆናሉ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው፣ ድንበርን በተመለከተ ጥቅልል አድርጎ የክልል ማድረግ ተጠየቃዊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ፌደሬሽን ግዛቷ (territory)  የክልሎቹ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የግዛት ወሰኗ ደግሞ በጥቅሉ የክልሎቹ ሳይሆን ክልሎቹ ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር ያላቸው ድንበር (border or boundary) ነው፡፡ ስለሆነም፣ክልሎቹ ከሌሎች አገራት ጋር የሚዋሰኑበትን የድንበር አከላለል እና ተያያዥ ጉዳዮች በፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር እስካልሆኑ ድረስ ሁኔታዎቹን የበለጠ ውስብስብ ያደርጋቸዋል፡፡
ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አገራትን በሚመለከት ዓለም አቀፍ  ስምምነቶች እና አሠራሮች፣ የአገራትን መብት እና ግዴታን አስመልክቶ በ1933 የተደረገው የሞንቲቪዶ ስምምነት፣ አገራት እርስ በርሳቸው ያደረጓቸው ውሎች፣ እና ሌሎች መርሖችን በመከተል እልባት መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
በክልል እና በክልል መካከል የሚነሱ የድንበር ውዝግቦች ለመፍታት የሚረዱ የተለያዩ ሕጋግትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችለው የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48 ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የድንበር አለመግባባት በሁለት ክልሎች መካከል ሲፈጠር በቀዳሚነት ክልሎቹ በስምምነት እንዲጨርሱ ነው የተደነገገው፡፡ በራሳቸው መስማመት ካልቻሉ በፌደሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ውሳኔ ይሰጣል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ምክር ቤቱ በብሔር፣ብሔረሰብ እና ሕዝቦች መከካከል አንድነት እና  መፈቃቀድ እንዲድግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በክልሎች መካከል አለመግበባት ሲፈጠር ውሳኔ የመሥጠት ሥልጣኑም የእሱው ነው፡፡ በሁለት ክልሎች መካከል ውዝግብ አለኝ የሚል ክልል ለሌላው ክልል ክልል በጽሑፍ እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መጥሪያው የደረሰው ክልልም በአርባ አምስት ቀናት ውስጥ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ማሳወቅ ይተበቅበታል፡፡ ድርድሩንም ወይንም ውይይቱን የፌደሬሽን ምክር ቤት ይከታተለዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ መፍተሔ ካልተገኘ አሊያም አንዱ ክልል ለውይይት ዝግጁ ካልሆነ ለምክር ቤቱ አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ምክር ቤቱም ለጊዜው ተገቢ የመሰለውን ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይ ግጭቶች ካልቆሙ ለማስቆም የሚያስችል ተገቢ የሆነ ጊዜያዊ ውሳኔ/እርምጃ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡የመጨረሻ ውሳኔ ለመሥጠት ግን ማስረጃዎችን መመርመር እና መልስ ከሌላው መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ በድንበርም ወይንም በሌላ ምክንያት ለሚነሳ አለመግበባት በጥቅሉ የተቀመጠ አሠራር ነው፡፡
የድንበርን አለመግባበትን በተመለከተ ተጨማሪ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ይሄውም  ከውሳኔ በፊት የሕዝቡን አሠፋፈር ማጥናት እና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ግድ ነው፡፡ በሕዝቡ አሠፋፈር ብቻ መወሰን የሚቻል ከሆነ በዚያው ያልቃል፡፡ በዚህ የሚቋጭ ካልሆነ ግን ወደ ሕዝቡ ፍላጎት መሄድ ሁለተኛው ደረጃ ነው፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት ለማረጋገጥ ደግሞ በቀበሌ ደረጃ በሚከናውን ሕዝበ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ይፈጸማል፡፡ ድምጽ ለመስጠት የሚችለው በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ሲሆን በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀለ ሰው ግን ድምጽ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በውጤቱም መሠረትም አካባቢው የማን እንደሆነ ይለያል፡፡
ከፌደሬሽን ምክር ቤት በተጨማሪ፣ የፌደራል እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥልጣንና ኃላፊነት በክሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት፣ በክልሎች ጠያቂነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት እንዲፈቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ የመቀየስና የመተግበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም፣ከፌደሬሽን ምክር ቤት በመለስ ማለትም ዳኝነት ከሚመስሉት በስተቀር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንም ይመለከተዋል፡፡
ስለድንበር ለውጥ ሲነሳ፤
የድንበር ውዝግብ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዋናነት ግን የወጥነት መርሕ ማለትም ቀድሞ ድንበር ከተደካት መሥፈርት ጋር የሚጣጣም እና የማይቃረን መሆኑ ነው፡፡ ብሔርን መሠረት አደርጎ ከነበር በለውጥም ጊዜ እንዲሁ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሲከለል ማንነትና አሠፋፈር ከነበሩም ኋላም በለውጥ ጊዜ እንዲሁ ማለት ነው፡፡
 በኢትዮጵያ ለክልልነት መሥፈርቶቹ ማንነት፣ቋንቋ ፣ የሕዝብ አሰፋፈር እና ፈቃድ ናቸው፡፡ የድንበር ውዝግብን ለመፍታት ግን  አሰፋፈር እና ፍላጎት ብቻ ናቸው፡፡ አሰፋፈር የሚለው ቋንቋን እና ማንነትን ያካትታል እንዳይባል ደግሞ ቀድሞ ክልል ለመመሥረት የብቻቸው ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በመሆኑም፣ የሕዝቡ አሰፋፈር ማለት ምን እንደሆነ ዝርዘር ነገር ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡
ወጥነቱን ለማሥጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ አሰፋፈር የሚለውን መለኪያ አላግባብ ሥራ ላይ በማዋል ግጭትን ሊያባብስ ስለሚችልም ጭምር፡፡ በተለይ ደግሞ ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩት ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ሕዝቦች መካከል በመሆኑ ይህንን መሥፈርት በተገቢው መንገድ መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ በበርካታ አገራት እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሠት ተጨማሪ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡
በአንድ በኩል የፌደራል ሥርዓቱ የተዋቀረበት ወይንም ክልሎች የተከለሉበት ሁኔታም መሥፈርትም ውሎ ሲያድር ሊያጋጭ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ብሔሮች የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት ወይንም ለማስፋት በመፈለግ ሊከሠት ይችላል፡፡ ታሪካዊ ይዞታን መጠየቅም ሊከተል እና ግጭት ሊወልድ ይችላል፡፡ የፌደሬሽኑ አባላት (ክልሎች) እኩል መብት እንዳለቸው የማይጨበጥ መብት (legal fiction) ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ልዩነት ይፈጥራል፡፡
የልዩነቱ መነሻም የሕዝብ ብዛት ከፍና ዝቅ ማለት፣ የሃብት መበላለጥ፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፊትና ኋላ መሆን፣ የክልሎች መልክአ ምድራዊ ግዛት ስፋትና ጥበት የተወሰኑት ናቸው፡፡ እነዚህን ልዩነቶች ለማጥበብ ሽሚያ ይፈጠራል፡፡ ሽሚያው ጠብም ይጭራል፡፡ በእነዚህ እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሕዝቡ አሠፋፈር በሚል ጥቅል መለኪያ እና የሕዝብ ፍላጎት ብቻ መወሰን ግጭቱ እንዳይቀጥል ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ይህንን ደግሞ በተሌዩ ጊዜ ውሳኔ የተሰጠባቸው አካባቢዎች ላይ በድጋሜ ያገረሹትን አለመግባባቶች ማንሳቱ በቂ ነው፡፡
ገለልተኛ የድንበር ኮሚሽን መቋቋም እንደ አማራጭ
በመሆኑም እስካሁን ያሉትን አሠራሮችም ይሁን  ተቋማት ዳግም የመፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ የድንበር ጉዳይን በተመለከተ በዓለም አቀፍም ይሁን በፌደራል ሥርዓት አሠራሩም ይሁን ጽንሰ ሐሳቦቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ዋናው ልዩነቱ የሚመነጨው ግጭት ሲፈጠር ተፈጻሚ የሚሆኑት ሕጋገት ላይ ነው፡፡ ግጭቶቹን ለመፍታት ግን ኮሚሽን ማቋቋም የተለመደ ነው፡፡
አንድ አገር በተለይ ከአሃዳዊነት ወደ ፌደራል ስትዋቀየር ቀድሞ የሚነሳው የፌደሬሽኑ አባላት የሚሆኑት፣ ክልልም ይባሉ ሌላ፣ እንዴት እንደሚካለሉና እንደሚዋቀሩ  መሥፈርቶቹን  የመለየት ጉዳይ ነው፡፡ መሥፈርቶቹን ከለዩ በኋላም የሚነሱ ሁለት ተግባራት አሉ፡፡ የክልሎቹን ድንበር በወረቀት ማለትም በካርታ  እና በስምምነት ማስቀመጥ (delimitation) እና በወረቀት ላይ የተቀመጡትን በተግባር ወደ መሬት በማውረድ የማስመር እና ማካለል ወይንም ድንበር መደካት (demarcation) ሥራዎች ናቸው፡፡
አገራት አስቀድመው አስቀድመው የድንበር ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎች እና ወሰናቸው የሚያርፍበትን ቦታ ጭምር ለይተው በማቅረብ የሕገ መንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ምሳሌ ናት፡፡ ከበርካታ የሙያ ዘርፍ የተውጣጡ የፖለቲካ ሹመኞች ሆነው የማያውቁ ሰዎች የተካተቱበት አንድ ኮሚሽን በማቋቋም ስንት ክልሎች እንዲሁም ምን ምን ጉዳዮችን መሥፈርት በማድረግ እንደሚወቀሩ ባቀረቡት አስተያየት መሠረት አገሪቱ ከእንደገና ተዋቀረች፡፡ በተለይም ዘርን፣ ቀለምን፣እና ብሔር ጋር የተያያዙትን እንዲቀሩ አሳሳበ፡፡
ሕገ መንግሥታቸው ከጸደቀም በኋላ ቢሆን በሕገ መንግሥቱ ስለ ድንበር ለውጥና አከላለል እንዲሁም ስለ ድንበር ኮሚሽን ያካተቱም አሉ፡፡ ናሚቢያን ብንወስድ፣ እንደምን በማድረግ ክልል መዋቀር እንዳለበት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሚመራ ኮሚሽን አቋቁማ በተለይ ዘርን ለፖለቲካ አስወግደው ከእንደገና በተሳካ ሁኔታ አገራቸውን አካልለዋል፡፡ የክሎቹን ብዛት እንዲሁም ዋና መሥፈርቱ አገራዊ የልማት እና ማኅበራዊ ትስስር መሆን እንዳለበት ባስቀመጠው መሠረት ተፈጸመ፡፡
ናይጀሪያ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የድንበር ለውጦችና ክልሎችን እንዲካለሉ አድርገዋል፡፡ ከሦስት ወደ ሰላሳ ስድስት ሲድጉ ብዛታቸውንም ድንበራቸውንም በሕገ መንግሥቱ በሌሉ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በተቋቋሙ ኮሚሽኖች አሳክተዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ በተለየ የናይጀሪው በአንድ ክልል ውስጥም ይሁን በፌደራል ደረጃ የብሔር የበላይነት እና የበታችነት እንዳይኖር ተግተው በመሥራት አቃልለውታል፡፡
በግብነት ይዘውት የነበረውም ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማፋጠን፣ አስሳታፊ ዴሞክራሲ፣ የተመጣጠነ ውክልና ያለበትና የተረጋጋ የፌደራል መንግሥት፣ የብሔር የበላነትና የበታችነትን ማስወገድ ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት በብሔሮች መካከል የነበረው ጥላቻና ጥርጣሬ ስላደገ  እሱን ለመቀነስና ለመቅረፍ ተጠቅመውበታል፡፡
ቀድሞ የተለያዩ አገራት ኋላ ላይ በፌደሬሽን ሲዋሃዱ ብዙ ጊዜ ችግር አይከሰትም፡፡ ቢሆንም ግን፣ በክልሎች መካከል የሚነሳን የድንበር ውዝግብ ለመቅረፍ ሲባል የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የድንበር ውዝግብ የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ስላልሆነ በስምምነት ከሚፈታው በመለስ ላለው ጉዳይ ኃላፊነቱ የፌደራል መንግሥት ስለሆነ ሕግ ማውጣትም መቆጣጠርም መከታተልም ይጠበቅበታል፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ዋቢ ነው፡፡
የድንበር ኮሚሽን ማቋቋም፣ ዝርዝር ኃላፊነትና ተግባር በሕግ መሥጠት፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያዎችን እንዲያካትት ማድረግ፣ ለኮሚሽኑ ተገቢ ጊዜ በመስጠት ስለ ድንበር ሁኔታ እንዲያጠና ማድረግ ይገባል፡፡ ልማትና እድገትን፣መሠረተ ልማትን፣ ብሔርን፣የተፈጥሮ ሃብትን፣ የቦታ አቀማመጥን አስተዳደራዊ ምቹነትን እና ትራንስፖርትን ማሰብ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት በዋናነት ኃላፊነት አለበት፡፡
የምርጫ ወረዳን ለማካለልም እንዲሁ ይሔው ተቋም ጠቀሜታ አለው፡፡ እየተከሠቱ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንደ ድሬዳዋ ዓይነት መስተዳዳሮችን መዋቀርንም ማሰብ ይገባል፡፡ በተለይ ሁሉትና ከዚያ በላይ የሆኑ ብሔሮች ተዋህደው በሚኖሩባቸው እና ግጭት በሚፈጠርባቸው ቦታዎች ሆነው  በግልጽ ወደ አንዱ ክልል ማጠቃለል የማይቻል ሲሆን፡፡
ለማጠቃለል
በአሜሪካ ድንበር የሚካለለው በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር እና ክትትል መሆን እንዳለበት ሕገ መንግሥታቸው በአንቀጽ  4(3) ላይ ተደንግጓል፡፡ በሌላ ሕጋቸውም ድንበር ሲባል መሬት ላይ በቀያሾች አማካይነት የሚቀመጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ብሔሮች ተሰራጭተው ሲኖሩ ማንነታቸውን መሠረት በማድረግ መከለል ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ሲሆን የተለያዩ መሥፈርቶችን በአንድነት መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ቅማንት እንደሚገኝበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ድሬዳዋ እንደ ከተማ መስተዳደር የተዋቀረችበትንም አጋጣሚ ማንሳት ይቻላል፡፡ ወደ አንድ ክልል ማካተት ሲከብድ እንዲህ ዓይነት ዘዴ መፈለግም ያስፈልጋል፡፡
የአርብቶ አደሮች (ተዘዋውሮ አደሮች) ስለ ድንበር ጉዳይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደርጉ የማድረግ አስቸጋሪነት እና ኑሯቸው ከአየር ሁኔታ መለዋወጥ ጋር የሚለዋወጥ መሆኑ መፍትሔውን ዘላቂ እንዳይሆን ስለሚያደርገው በዚህ መንገድ የሚሰጠው ውሳኔም ሊጤን ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ድንበር ሲካለል በወረቀት ማለትም በካርታ እና በውል መቀመጥም ይገባዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በቋሚ ምልክት ድንበሩን መለየት ይገባል፡፡
 እዚህ ላይ አሁንም የሚስቸግረው በአርብቶ አደሮች ዘንድ ቋሚ መስመር ማስቀመጥ በራሱ ፈታኝ ነው፡፡ ለማኅበራዊ መሠረታቸው  የሚስማማ ማለትም የጎሳ መሪዎችን ፈቃድ በተለያዩ መንገድ ማገኘት ለወዲያው መስማማት የመጣ ቢመስልም ውሎ አድሮ ግን መልሶ ማፍረስ የተለመደ መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡
ተርሚነስ፣ በጥንት ዘመን የሮማውያኖች የድንበር አምላክ ነበር፡፡ ገዥም ይሁን ተራ ግለሰብ በሚኖረው ግዛት ወይንም መሬት እንዲሰፋለት ስለሚፈልግ ድንበር ማስፋት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ድንበር በማገፋት ምክንያት በርካታ ሕይወት መጥፋትም እንዲሁ፡፡ይህን በድንበር አማካይነት በሚመጣ ግጭት ሕይወት እንዳያልፍ፣ ንብረት እንዳይወድም ብሎም ድንበራቸውን እንዲጠብቅላቸው የሚገብሩለት አምላክ ነበራቸው፡፡
በዘመናችን ደግሞ እንደ ተርሚነስ አገራት ሕግጋት እና አሰፈጻሚ ተቋማት አሏቸው፡፡ ሕይወት እንዳይቀጠፍ ንብረት እንዳይወድም የሚጠቀሙባቸው፡፡ኢትዮጵያም እንዲሁ ቢኖራትም ቅሉ ውጤታማነታቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሆነ አለመግባባትን የሚፈታ ተርሚነስ ያስፈልገናል፡፡
Filed in: Amharic