>
5:13 pm - Friday April 18, 8814

ኧረ የጠላት ያለህ - ባክህ ጦር አውርድ!!!  (ሳምሶን ጌታቸው)

ኧረ የጠላት ያለህ – ባክህ ጦር አውርድ!!! 
ሳምሶን ጌታቸው
* ቆይ ቆይ ኧረ.. ግን እንዴት አንድ መስዕዋት ፈረንጅ አጣን እንደ ሞሶሎኒ ያለ፣ ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር ወሮ በጋራ አቁስሎን፣ በጋራ የሚጣላን። እኛም በጋራ ፎክረን፣ በጋራ ገድለነው፣ በጋራ የሚያፋቅረን? ፍቅራችንን የምናስደግፍበት የጋራ ጠላት አጥተን እኮ ነው፣ እንዲህ የምንባላው። አንድ የጋራ ጠላት ዕብሪተኛ ፈረንጅ ከየት እናምጣ? ….
በዚያ ዘመን ከጠፈር ላይ ተሁኖ ወደ ምድር ሲታይ የድሮዋ ኢትዮጵያ ግዛት በቅርጿ ልክ የአበባ ማሳ መስላ ትታያለች። በልዩ ልዩ አበቦች እንዳጌጠ የመስከረም ወር አጋማሽ ላይ እንደሚገኝ በቀለማት ያሸበረቀ ጋራ አይነት። ነገሩ ወዲህ ነው። ጉዳዩ የባንዲራ እርሻ ነው። በየጎጆው የሚውለበለበው የባንዲራና የአርማ መአት፣ በሰው ልጆች ታሪክ የተመዘገበ የሀገር ቅርምት ውጤት። ፈረንጆቹ በሕብረት የገነቧቸው ልማቶቻቸው ከሕዋ ይታያል እያሉ ይፎክራሉ፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በደቦ ያፈረስነው የሀገር አንድነት ፍርስራሽ በባንዲራ ተወክሎ ከጠፈር ላይ ይታያል።
ጠዋት ጠዋት ከየጎጆው እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ በሚል ፉክክር የተነሳ ጮክ ተብሎ የሚሰማው ብሔራዊ (ቤተሰባዊ) መዝሙር ብዛትና ልዩነት የሚፈጥረው ጩኸት በምዕራብ እስከ ቤርሙዳ ትራያንግል፣ በምሥራቅ እስከ ቻይና ባሕር ሲደርስ፣ ወደ ሰማይ ሲወጣ የተቋጠረ ደመና ይበትናል። እግዜር ምን ይል ይሆን የደጁ ደመና በጩኸት ሲበተን? ለነገሩ፣ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል” ብሎ አስቀድሞ የጻፈው ራሱ ነው፣ ገና ድሮ።
ያኔ የጎጆ መንግሥታት ሲመሠረቱ እኔ በበኩሌ፣ ከእኝህ አየለ ጫሚሶ ከሚባሉት ሰውዬጋ እንደ ሀገር ምንም አይንት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አይኖረኝም። በአየር ክልሌም ሆነ በምድር ወሰኔ እንዲያልፉ አልፈቅድላቸውም። እንዲያውም ከሳቸው የበለጠ ጠንካራ ሀገረ ጎጆ ስለሚኖረኝ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ እጥልባቸዋለው። በሳምንት ሁለቴ ድንበራቸው አቅራቢያ እየደረስኩ የጦር ልምምድ እያደረኩ አጨናንቃቸዋለሁ። እነ ቢቢሲ “የጎረቤት ሀገራቱ የእነ ሀገረ አየለ ጫሚሶ ሪፐብሊክ መፋጠጥ አስግቷል” እያሉ እስኪዘግቡ አንላቀቅም። ሀገር እያለን መጫወቻቸው አድርገውን ጎጆ ስንሆን እኛም በተራችን አንለቅም። እኚህ…
ዛሬ እንዲህ ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ሥር ሆነን የተጫወቱብን ሁላ ያኔ በተናጠል ስንገናኝ፣ ብድራቸውን ያገኛሉ። እያንዳንዱን ወመኔ ሀገረ ጎጆው ድረስ እየኼዱ ማነጋገር ያስፈልጋል። ደሞ ይኼንንም ቅድመ ዛቻ እየተደረገብን ነው ብላችሁ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአሁኑ ክሰሱ አሉ። ምንም አታመጡም፣ የበለጠ ቂም ነው የምታተርፉት። ሕግ ድሮ ኢትዮጵያችን እያለች ቀረ። የተባበሩት መንግሥታት የሚያገባው በነባሩ የሀገር ትርጉም መሠረት ለተሰባሰቡት እንጂ ለጎጆ ስብስቦች አይደለም። ብትለመኑ ብትለመኑ እምቢ ብላችሁ ሀገራችንን አህጉር አደረጋችኋት አይደለም? እና ምን ይሁን ነው የምትሉት? አሁን በጉልበት እንመራራለን። በሀገረ ጎጆ ሕግ መሠረት። አለቀ።
ከጎጆዎች በፊት ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ ክ/ከተሞች ቀድመው ሀገር መሆንን ይጀምራሉ። ያኔ በሳይንሱም ላይ ጉዳት ይደርስበታል። በተለይ የአውሮፕላን ነገር በጣም ያሳዝናል። እንዴት ማለት ጥሩ። ለምሳሌ በአዲሳባ ያሉ ክ/ከተሞች ወደ ሀገርነት ሲቀየሩ፣ አንድ አውሮፕላን ከሀገረ የካ ተነስቶ ወደ ሀገረ ቦሌ ሲሄድ፤ እንኳን ወደ ሰማይ ሊበር በቅጡ ሳይንደረደር የሚሄድበት ሀገር ይደርሳል።
እንደጓጓ ሳይበር ይቀራል። ልክ ሊያስነጥስ ፈልጎ አፍ ከፍተው፣ ዐይን ጨፍነው፣ አፍንጫን አኮማትረው ሲጠብቁት ሸውዶ እንደሚቀር፣ ተንኮለኛ ንጥሻ። ይኼኔ አውሮፕላኑ ብስጭት ይላል። ቢበሳጭም የዘመን ምርኮኛ ነው፣ ምን ያመጣል። መብረር ድሮ በኢትዮጵያ ጊዜ ቀረ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚል ሰማያዊ ማዕረግ። አሁን ከጎጆ ወደ ጎጆ ምን በረራ አለ። የመብረር መብቱ ተጥሶ በእግሩ የሚነዳ ለማዳ አውሮፕላን ተደርጎ ተሰናክሏል።
የእኛ ነገር የሰለቸው የአለም ሕዝብም፣ እንዲህ ሆነን ሲያየን “ኦው ዩ አር ጂኒየስ” ብሎ በታከተ ድምፅና በተጣመመ ከንፈር አሸሙሮን ያልፋል። እኛ ደግሞ ያወድሱን እንጂ ባልሆነው ነገር ሲያሞግሱን የምንፈነጥዘው ነገር አለን። ፍንጥዝ። አዝማሪ ቤት ሄደን ከፍለን የምንወደስ፣ የምንደሰት። 50 ኪሎ የማይመዝን ኮሳሳ ሀበሻ አዝማሪ ቤት ገብቶ:-
የትከሻህ ግዝፈት የደረትህ ስፋት፣ 
ለፈረስ ሜዳ ነው ለመኪና አስፋልት። ከተባለ ጃንሆይ ላይ ባልታየ ኩራት ተጀንኖ፣ ቤት ኪራዩን አውጥቶ ሊከፍል ይችላል። ታዲያ ማን ከእኛ ጋ ይዳረቃል። “በጣም ልዩ ናችሁ፣ በዕውቀትና በጥበብ የሚደርስባችሁ የለም” ከተባልን፣ ነገሩ አከተመ። አውራ ዶሮ ምን ይኮራል። የቀልባችንን ክንፍ ጥለን በኩራት ስፍፍ እንላለን። በእብሪት ከፍ ያለ ሥፍራ ላይ ቆመን ኩኩሉ እንላለን። ኩኩሉ።
ቁጥራችን በሚሊዮን ስለሆነባቸው እንጂ እንደነገረ ሥራችንማ ፈረንጆቹ በሆነ ዘዴ ቢፈጁን ደስ ሳይላቸው አይቀርም። ከእኛ ጋ የአንድ አለም ሕዝቦች ተብሎ መቆጠራቸው በራሱ እንደሚቀፋቸው ያስታውቅባቸዋል። ፈረንጅ ደግሞ ንቀቱና ዕብሪቱ ሀበሾች መሆናችንን ይዘነጋዋል መሰለኝ። ባዕዳን በተንኮል ሲመጡብን ንድድ እንደሚለን ተዘንግቷል። እርስ በርስ እንጂ ፀባችን ባዕድ ልኮሳተርባችሁ ካለንስ የጋራ ደማችን በጋራ ይፈላል። እናቱንና። እደግመዋለው እናቱንና። ቆይ ቆይ ኧረ.. ግን እንዴት አንድ መስዕዋት ፈረንጅ አጣን እንደ ሞሶሎኒ ያለ፣ ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር ወሮ በጋራ አቁስሎን፣ በጋራ የሚጣላን። እኛም በጋራ ፎክረን፣ በጋራ ገድለነው፣ በጋራ የሚያፋቅረን? ፍቅራችንን የምናስደግፍበት የጋራ ጠላት አጥተን እኮ ነው፣ እንዲህ የምንባላው። አንድ የጋራ ጠላት ዕብሪተኛ ፈረንጅ ከየት እናምጣ? ጨረታ እናውጣ ይሆን፣ ጠላት እንፈልጋለን የሚል።
Filed in: Amharic