>
5:13 pm - Monday April 18, 7932

"አስፈላጊ ከሆነ ስልጠና እሰጣችኋለሁ" የተባሉት ተፎካካሪ ድርጅቶችና ጠ/ምኒስትሩ!! (ፋሲካ ገብርዬ)

“አስፈላጊ ከሆነ ስልጠና እሰጣችኋለሁ” የተባሉት ተፎካካሪ ድርጅቶችና ጠ/ምኒስትሩ!!
ፋሲካ ገብርዬ
ለመሆኑ ጠ/ም አብይ መራሹ ኢህአዴግ የምርጫ ዘመቻውን የጀመረው መቼ ይመስልዎታል? አንዳንድ የዋሆች ገና መቼ ይሉኝ ይሆናል:-
1- በእኔ እይታ ዝግጅቱ የጀመረው ጠ/ሚ አብይ ስልጣን በተረከበበት ዕለት ባደረገው ንግግር ነው። በዕለቱ፥ በማይካድ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ያለነውን ጭምሮ፥ የመላው ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የገዛበት ንግግሩ፥ እንዲሁም አርቲስቶችን ሰብስቦ ትምህርታዊ ገለጻ በሰጠበት ወቅት ዝግጅቱ ለህዝብ ይፋ እንዲሆንና የጠ/ሚኒስትሩን ሰፋ ያለ ግንዛቤና ክህሎቶች ህዝብም እንዲያውቀው መደረጉ
2- በግፍ እስርና ሰቆቃ ሲማቅቁ የነበሩትን እስረኞች ተራ በተራ እንዲለቀቁ መደረጉ፥ በየክልሎቹ እየተዘዋወረ፥ በተለይ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ  እጅግ በተጠላባቸው ክልሎች ከህዝቡ ጋር ያደረጋቸው ስብሰባዎችና የአደባባይ ዝግጅቶች፥ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሄደበት አስገራሚ ፍጥነትና ህዝብን ያስደነቀ የሁለቱ መሪዎች መቀራረብ
3-በሰሜን አሜሪካ ከተሞች ተዘዋውሮ ተቃዋሚውንም የቀድሞው “ኢህአዴግን” ደጋፊዎችን ሁሉ አሰባስቦ ወይም በጠ/ሚ አብይ አገላለጽ ደምሮ እልል ባስባለባቸው ዝግጅቶች
4- ለተቃዋሚ/ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ አገራቹ ግቡ ወዳጅና ጠላት የለም፥ እኔ አሻግራችኋለሁ ሲል፥ ይህን የሚለው በእውነት በወያኔ ቤት ያደገ ሰው ነው እንዴ? በማለት ሰው በድርጅቱ ጨርሶ ተስፋ እንዳይቆርጥ አቻቻይና አገራዊ ራዕይ ያለው ስብስብ ሆኖ መውጣቱ
5- በክርስቲያኑም ሆነ በሙስሊሙ እምነት ተቋማት መሃል ያለውን መከፋፈል እና ግምብ ንዶ ፥ ጭራሹኑ የውጪውን ሲኖዶስ ሊቀጳጳስና ልዑካቸውን ይዞ ወደ አገር የተመለሰበት የአደባባይ ሂደት
6- በሙሉ ዝርዝር የአገር ውስጥ ጉዳዮች ለመግባት ባይመችም፥ ከጉዞው በፊትም ሆነ በኋላ ፥ ተፎካካሪ ድርጅቶች አንድ በአንድ በሚዲያ ለህዝብ እንዲታዩ ሆኖ መግባታቸው፥ ፈረንጆቹ “confidence building” የሚሉትን፥ ኢህአዴግ ምን ያህል በራሱ ቢተማመን ነው የሚል የሞራል የበላይነትን በህዝብ አዕምሮ ውስጥ መፍጠሩ
7- ጭራሹኑ፥ በኢህአዴግ የሀዋሳው ስብሰባ ላይ ተፎካካሪ ድርጅቶችን በእንግድነት ጋብዞ ለህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ፥ የኢህአዴግን መታደስና አገራዊ ድርጅት ሆኖ ለመውጣት ጉዞ መጀመሩን በመድረክ ዝግጅትና በጠ/ሚ ንግግር ጭምር መገለጹ፥ እንዲሁም ተፎካካሪ ድርጅቶችን አስፈላጊ ከሆነ ስልጠና እንሰጣችኋለን ያለበት ንግግር፥ (ይሄ ክስተት የconfidence buildinጉን ነገር ትንሽ ያጦዘው መስሎኛል)
8- ከአውሮፓው ጉዞ በፊት፥ ከ50% በላይ የሴቶች ካቢኔ ያውም ከተለያዩ የብሄር ተዋጽኦ አሰባጥሮ መሾሙ፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግ፥ ፕሬዝዳንቷ፥ በቅርቡ ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን (ያውም ቀድሞ በወያኔ መራሹ ኢህአዴግ ስንት መከራ የደረሰባትን ሴት) መሾሙ
9- በበርሊን አጭርም ብትሆን ህዝቡን ለማግኘት ከመንገዱ ወጥቶ መሄዱ፣ በፍራንክፈርት ስታዲዮም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገበት ንግግሩ፣ እንዲሁም በተለያየ የውጪ ጉዞዎቹ ጉዳት የደረሰባቸውን ኢትዮጵያዊያን በአደባባይ ማግኘቱ (ምሳሌ፥ ሳውዲ እናትና ልጅን፣ ጀርመን ደግሞ አሲድ ፊቷ ላይ የተደፋባትን ሴት፣ በአገር ውስጥ ደግሞ አበጥር ወርቁን ወዘተ)
10- ወደ አገር ከተመለሰ በኋላም በሙስና ላይ በአዲሷ የጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተዳደር የተከፈተው ዘመቻ፥ የጠ/ሚኒስትሩ አስተዳደር ውጤት ሆኖ እንደሚመዘገብ አንርሳ፥ በአገር ላይ ከባድ ዘረፋ የፈጸሙ ግለሰቦች ወደ ህግ እንዲቀርቡ የተጀመረው ሂደት
11- ከሰሜን አሜሪካው ጉዞው ጀምሮ አብሮ ሚጓዘው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት (በአቋሙ ላይ ህዝብ ያለው የተለያየ አተያይ እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ዳንኤል የቤተ ክህነት ሰው፥ ደራሲና ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን እንዳንረሳ)፥ እንዲሁም የጠ/ሚ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ወ/ት ቢልለኔ (ሌላ ሴት ተሿሚ) በአማርኛና በእንግሊዘኛ ስለ ጠ/ሚ አብይ አስተዳደር የሚያደርጉትን የትዊተርና ፌስቡክ ገለጻዎች ስመለከት የኦባማን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች (campaign team) እያስታወሱኝ ነው
12- ወደአገር ውስጥ ከገቡት የቀድሞ ተቃዋሚ የአሁን ተፎካካሪ ድርጅቶችና ግለሰቦች መሃል፥ በሶማሌ ክልል የተሾመው ግለሰብ፣ የአዴሃን ወደ ኢዴፓ፣ ኦነግ ወደ ኦዴፓ የተሰባሰቡበት ሂደት፣ እንዲሁም በትናንትናው ዕለት ከ80 በላይ ተፎካካሪ ድርጅቶችን ጠ/ሚኒስትር አብይ ሰብስቦ፥ ወደ 4 ወይም 5 ፓርቲዎች እንዲጠቃለሉ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት አዲሷ ኢህአዴግም እንደ አንድ አማራጭ ጠቅላይ ፓርቲ እንደቀረበች እንዳንረሳ
“እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው” ብሏል ሃይሌ ገ/ስላሴ:)
አዎ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፥ ፋና እና ኢቢሲ ወዘተ… የሚዲያ አማራጮች ለገዢው ፓርቲ በእጁ ነው፣ ለመንግስት ስራ የሚደረጉ ጉዞዎች ገጽታንም ለመገንባት ያገለግላሉ፣ የመሰብሰቢያ ቦታ ወይም ህዝብን በተፈለገው ጊዜና ቦታ የማግኘት ችግር የለባቸውም፣ የአገራችን አከላለል የብሄር በመሆኑ፥ ገዢው ፓርቲ በየክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ በየብሄሩ ውክልና አለው፣ ድርጅቱ መታደሱን በተለያየ ክስተቶች ለህዝብ እያሳየ ነው፣ ችግሮች በየአካባቢው ሲፈጠሩ መልስ ለመስጠት ሲታትሩ እያየን ነው (የእምቦጭ አረምን፥ የላሊበላ እና የአባ ጅፋር ቤተመንግስት መታደስ ጥያቄን ለመመለስ የተገባውን ቃል ልብ ይሏል)፣ አዲስ አበባ ላይ መሃል ለገሃር ላይ፥ በ3 ዓመት ውስጥ ሊሰራ የታቀደው መሰረተ-ልማት ዕቅድና አፈጻጸም ኢህአዴግን ከገጠር ልማት ተኮር መንግስትነት ያወጣዋል
በድጋሚ ምን ለማለት ፈልጌ ነው:)
ተፎካካሪ ድርጅቶች ገና ፓርቲ ሆነው ሳይሰበሰቡና ሳይመዘገቡ፥ ጠ/ሚ አዲሱን ካቢኔያቸውን ይዘው እየገሰገሱ ነው። ህዝቤ በየአጀንዳው ተሰባስቦ በደንብ እንኳ ሳይመክር፣ አዲሷ ኢህአዴግ ግስጋሴዋን ቀጥላለች፥ ጭራሽ ተፎካካሪ ድርጅቶችን በጉያዋ እየሸጎጠች ነው። ለወትሮው የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረገው፥ ለህዝብ ከመረጣችሁኝ ይህንን እፈጽማለሁ፥ ይህንን አከናውናለሁ እየተባለ ነበር። የጠ/ሚ አብይ መንግስት ቀዳዳዎችን በመድፈን ለተፎካካሪዎች ብዙም አማራጭ ማቅረቢያ እየተወ አይደለም። ይሄ ሂደት ለአገርና ለወገን እስከጠቀመ ድረስ ክፋት አይኖረውም።
ነገርግን አሁን ኢህአዴግ ካለው ቁመናና ድርጅታዊ አሰራር ጋር ለመለካካት በደንብ የተጠና፣ ቀልጣፋ፣ አሳታፊ፥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት፣ የዘመነ፣ አዳዲስ ራዕዮችን የሰነቀና፣ የተቀናጀ አሰራር ከተፎካካሪ ድርጅቶች በአስቸኳይ ይጠበቃል። ምርጫው ቢራዘምም እንኳ ወደ ተግባር ተሰናድቶ ለመግባት ጊዜ ያስፈልጋል። አሸናፊ ራዕይና ቁመና ይዞ እውነተኛ ፉክክር ለማድረግ ካልሆነ ደግሞ፥ ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ሃይል ማባከኑ ትርጉም አይኖረውም።
ለሶስተኛ ጊዜ፥ ምን ለማለት ፈልጌ ነው:)
ጎበዝ ይታሰብበት! ይሄኛው ኢህአዴግ የቀድሞው አይነት የአላዋቂዎች ስብስብ አይደለም። እናም ሲሆን የሚመጥን ከተቻለም የሚልቅ ተፎካካሪ ስብስብ በአፋጣኝ ማደራጀቱ ግድ ይላል። አለዚያ ለሚቀጥለው 7 ዓመት አስቦ ከወዲሁ መዘጋጀት ይሆናል የሚያዋጣው።
Filed in: Amharic