>

የትግራይ ህዝብና ህወሀት!!! (መሳይ መኮንን)

የትግራይ ህዝብና ህወሀት!!!
መሳይ መኮንን
የቀድሞ የህወሀት ኮማንደር የነበሩትና አሁን በጀርመን የሚኖሩት አቶ ተስፋዬ አጽበሃ በአንድ ቃለመጠይቅ ሲናገሩ እንደሰማሁት ከደርግ አንጻር በህወሀት የተገደሉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር በእጅጉን ይልቃል። ትግራይን ከእናት ሀገሯ እገነጥላለሁ ብሎ ደደቢት ላይ የተወለደው ህወሀት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው በመጠነ ሰፊ የግድያ እርምጃው ነው!

ይህን ጽሁፍ ለመሞነጫጨር ስዘጋጅ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለቀድሞው የኮሎራዶው ኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍማን ደብዳቤ ምላሽ የሰጠበትን ወረቀት ፌስቡክ ላይ ሲመላለስ አየሁኝ። ማይክ ኮፍ ማን የህውሀቱ የቶርቸር አለቃ ጌታቸው አሰፋ ላይ የማግኔቲስኪ እርምጃ ተፈጻሚ እንዲሆንበት በመጠየቅ ለአሜሪካን የውጭ ጉዳይና ለትሬዠሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደብዳቤ ጽፈው ነበር። የማግኔቲስኪ ውሳኔ ተፈጻሚ ከሆነ ጌታቸው አሰፋ ወደአሜሪካና ወዳጅ ሀገራት መግባት አይችልም። በውጭ የሚንቀሳቀስ ሀብቱ ተፈትሾ እገዳ ይጣልበታል።
ምንም እንኳን ማይክ ኮፍማን በምርጫ ተሸንፈው ከኮንግረስ ቢሰናበቱም የጻፉት ደብዳቤ ግን ምላሽ አግኝቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማይክ ኮፍማን የቀረበውን መረጃ በመመርመር ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል። ለነገሩ የዲፕሎማቲክ ምላሽ ስለሆነ እንጂ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተደበቀ ነገር የለም። የጌታቸው አሰፋን የደም ዓይነትና የጫማ ቁጥር ሳይቀር የተሟላ መረጃ አለው። የምር አሜሪካ ቃሏን ከጠበቀች መቀሌ ላይ የሚንገታገቱት አዛውንቶቹ የህወሀት መሪዎች በአራት ኪሎ ቤተመንግስት ብቻ ሳይሆን በኋይት ሀውስ ጭምር ቶምና ጄሪን መጫወት ይጀምራሉ። አሳዳጅና ተሰዳጅ።
ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ሞክሼውን ”ክንፍ የሌለው መላዕክ” አድርጎ ያወራው ትዝ አለኝ። ቃሉን ያዙልኝ። የሀሰት ምስክርነቱ ብቻውን በወንጀል ሊያስጠይቀው ይገባል። ጥፍር ሲነቅል የኖረን ጥፍር ቀለም ሲቀባ ነበር፡ ሃይላንድ ብልት ላይ ሲያንጠለጥል የከረመን በሃይላንድ ወተት ሲያጠጣ ነበር፡ የሰው ገላን ተልትሎ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገድልን የሴጣን ቁራጭ እንደክርስቶስ ለሰው ልጅ መዳን በመስቀል የሚሰዋ ጻድቅ ሰው ነበር የሚለውን የጌታቸው ረዳን የሰሞኑ ዲስኩር የክፍለዘመኑ ቅጥፈት በሚል አልፈዋለሁ። ጊነስ ወርልድ በቅጥፈት ካታጎሪ የክፍለዘመኑን ምርጥ ቅጥፈት ካላገኘ የጌታቸው ረዳን የሰሞኑን ሙልጭ ያለ ክህደትና ሸፍጥ አስተርጉሞ መስጠት ቢቻል ጥሩ ነው።
ወደተነሳሁበት ርዕሰጉዳይ ልመለስ። የትግራይ ህዝብና ህወሀት ምንና ምን ናቸው? የአንገት ሀብልና የጆሮ ጌጥ? ወይስ እሳትና ጭድ? እጅና ጓንት? ወይስ አይንና ናጫ? ባልንጀራ ወይስ ባላንጣ? በእርግጥ አንድ ናቸው የሚለው የሌላው የህበረተሰብ ክፍል ከጥርጣሬም ያለፈ ጠንካራ ድምዳሜ የሆነ መስሏል። ሰሞኑን ከአድዋ እስከሰቲት ሁመራ የቀዳማይ ወያኔን ትጥቅ ለብሰው፡ መሳሪያ ወድረው ሰልፍ የወጡትን ተጋሩች የተመለከቱት ‘’ድሮም ብለን ነበር’’ በሚል የቀደመ አቋማቸውን ረግጠው በመያዝ ቀጥለዋል።
ጄነራል ሳሞራ ”መስመር ኢዩ” ሲሉ በገለጹበት የትግርኛ ዲስኩራቸው፡ የትግራይን ህዝብ ከህወሀት፡ ህወሀትን ከትግራይ ህዝብ መነጠል ፈጽሞ የማይቻል እንደሆነ ነግረውናል። ሰሞኑን በሌብነትና በስብዓዊ መብት ጥሰት አንዳንድ የህወሀት ባለሟሎች ሲያዙ ደግሞ ነግ በኔ የሰጉት ባለስልጣናቱ ህወሀትን መንካት የትግራይን ህዝብ መንካት እንደሆነ አብዝተው እየነገሩን ነው። ከህወሀት አጥር ያልገቡ፡ ህወሀትን በዓይነቁራኛ በሚመለከቱ፡ በሌላው ጫማ ልክ ህወሀትን ለመቃወም ያልደፈሩ ጥቂት የትግራይ አክቲቪስቶች ዘንድ ግን ህወሀትና የትግራይ ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም። ለእኔም አንድ አይደሉም። ጥቂት ማሳያዎችን ልጥቀስ፥
የእርዳታ እህልን እንደፖለቲካ መሳሪያ
የህወሀት ታሪክ በግፍ የተሞላ ነው። ግፉ የሚጀምረው በትግራይ ህዝብ ላይ ነው። የህወሀትን የጭካኔ ዱላ በመቅመስ ረገድ የትግራይ ህዝብ ቀዳሚው ነው። እነመለስ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ደደቢት ላይ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ማኒፌስቶ ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ ብዙም ተከታይ አልነበራቸውም። በተለይ በትጥቅ ትግል የሚሳተፍ ታጋይ ለማግኘት በቀላሉ የሚችሉት አልነበረም። እንደጦጣ ዛፍ ለዛፍ እየዘለሉ የደርግን እስከአፍንጫው የታጠቀ ዘመናዊ ጦር ለመረበሽ የሚያስችል ቅንጣቢ አቅም እንጂ ያን ግዙፍ ጦር የሚደመስስ ሃይል ለማደራጀት ፈጽሞ የሚችሉት እንዳልነበር ነባር ታጋዮች ይናገራሉ።
ለህወሀት አዱኛ የሆነለት ትግራይ ላይ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ ነበር። ህወህቶች ይህን እድል መጠቀም እንዳለባቸው አውቀውታል። አከባቢውን የደርግ መንግስት እርዳታ እንዳያደርስ በፈንጂ አጥረው፡ ከፍተኛ መሰናክል ፈጠሩ። በዚህን ጊዜ የእርዳታ እህል ሊደርስለት ያልቻለው የትግራይ ህዝብ በረሃብ መርገፍ ጀመረ። ህወሀት የትግራይን ህዝብ እህል እንዳይደርሰው ያደረገው የትግራይ ወጣቶች ረሃብ ሲጠብሳቸው ህወሀትን ተቀላቅለው ደርግን ለመፋለም ይወስናሉ ከሚል ስሌት እንደነበር በርካታ የዓይን ምስክርነቶችን አንብቤአለሁ። እንዳሰበውም ሆነለት።
ሺዎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ፡ መንገድ ላይ በረሃብ ሲረግፉ ለህወሀት ድራማ ጥሩ ትዕይንት ነበር። ህጻን ቆዳና አጥንቱ ተጣብቆ የእናቱን የደረቀ ጡት እንደያዘ እስከወዲያኛው ያሸለበበትን ዘግናኝ ትዕይንት በቪዲዮ እየቀረጸ ለዓለም በሞላ እንዲሰራጭ በማድረግ የደርግን መንግስት ጥላሸት መቀባት፡ ራሱን ደግሞ የትግራይ ህዝብ አዳኝ አድርጎ ማሳየት ነበር ዕቅዱ። ተሳካለትም። የደርግ መንግስት ዓለም ዓቀፍ ውግዘት ሲቀርብበት ህወሀት ደግሞ እህል የሚሰፍሩ ድርጅቶችን እምነት አገኘ። የትግራይ ህዝብ የረሃብ ጉንፋን እየሳለ ሲረግፍ ህወሀት ያለርህራሄ ፖለቲካዊ ድጋፍና እርዳታ ሸመተበት። የትግራይን ህዝብ እህል ከልክሎ፡ የትግራይን ህዝብ ደጀን አተረፈበት። ምጸቱም ይሀው ነው። አንድ ሚሊየን ገደማ ኢትዮጵያዊ በረሃብ እንደቅጠል የረገፈበት ጥቁር ታሪክ ላይ የህወሀት የጭካኔ ውሳኔ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አይካድም።
በእርግጥም ህወሀት ይህን አስከፊ የሰው ልጅን ዕልቂት ለሁለት ነገሮች ተጠቅሞበታል። አንደኛው በአስርሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች በአጭር ጊዜ ሲቀላቀሉት፡ በሌላ በኩል ዓለም ዓቀፍ ግብረሰናይ ተቋማት በደርግ መንግስት በኩል የሚላከውን እህል አቁመው በህወሀት አማካኝነት ለትግራይ ህዝብ እንዲደርስ ወስነዋል። ሌላኛው የህወሀት ግፍ የሚጀምረው ደግሞ ከዚህ ወዲህ ነው። የቀድሞ የድርጅቱ የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገብረመድህን አርዓያ እንደሚሉት በህወሀት በኩል ለትግራይ ህዝብ የሚሰጠው የእርዳታ እህል ለትግራይ ህዝብ አይደርሰውም። በደላሎች አማካኝነት ሱዳን ውስጥ እየተሸጠ፡ ለመሳሪያ መግዢያና አብዛኛው ገንዘብ ደግሞ በውጭ ባንኮች ይቀመጥ ነበር። ያ ገንዘብ ለአሁኑ የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርት መወለድ እርሾ ከሆኑት መነሻ ካፒታሎች አንዱ እንደነበረ ይነገራል። እንግዲህ ህወሀት የትግራይን ህዝብ እንዲህም አድርጎት ነበር።
ተጋሩዎችን በመግደል ደርግ ወይስ ህወሀት ይልቃል?
ይህ መረጃ ለብዙዎቻችን እንግዳ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁ ዕለት ለመቀበል ተናንቆኝ ታግዬአለሁ። ሆኖ ከፈረሱ አፍ የሰማሁትን፡ በሌሎች እውነተኛ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ማረጋገጫ ያገኘሁለትን እውነት አለመቀበል የምችለው አይደለም። ለነገሩ በቀድሞ መንግስት የጦር ሹማምንት የተጻፉ የጦር ሜዳ ገድል መጽሃፍት ላይ ያነበብኳቸው አንዳንድ ታሪኮችም ይህንኑ እውነት የሚፈነጥቁ ናቸው። የደርግ መንግስት የዓለም ዓቀፉ ማህብረሰብን ተቃውሞ ለማለስለስና የተበላሸውን ስሙን ለማስተካከል በሚል በኤርትራና በትግራይ ክፍተኛ ጥንቃቄ ከማድረግ ባሻገር ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ መልኩ ለእነዚያ አከባቢዎች እንክብካቤ ያደርግ እንደነበር ይነገራል።
 ኤርትራ በነበርኩ ጊዜ የሰማሁት አንድ ታሪክም ይሄንኑ ያረጋግጣል። የደርግ መንግስት በጦርነት ቀጠናዎች ውስጥ ለሚኖረው ህዝብ በአንቶኖቭ አውሮፕላን ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ የእህል ምርቶችን በከፍተኛ ቅናሽ ያቀርብ ነበር። ከሌላው የኢትዮጵያ አከባቢ ጤፍ እንደልብና በርካሽ ይገኝ የነበረው በጦርነት ቀጠናዎች አከባቢ መሆኑንም የሚናገሩ የዓይን ምስክሮች ገጥመውኛል። የውጭውን ማህበረሰብ ወቀሳ ለማብረድም ጭምር መሰል የተለዩ እንክብካቤዎች  ይደረግ እንደነበር ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ሰምቼአለሁ። ይህ ማለት ደርግ አይገድልም፡ አልገደለም ለማለት አይደለም። የደርግን መንግስት ሜክ አፕ እየቀባሁ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ አደራ እላለሁ።
የቀድሞ የህወሀት ኮማንደር የነበሩትና አሁን በጀርመን የሚኖሩት አቶ ተስፋዬ አጽበሃ በአንድ ቃለመጠይቅ ሲናገሩ እንደሰማሁት ከደርግ አንጻር በህወሀት የተገደሉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር በእጅጉን ይልቃል። ትግራይን ከእናት ሀገሯ እገነጥላለሁ ብሎ ደደቢት ላይ የተወለደው ህወሀት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው በመጠነ ሰፊ የግድያ እርምጃው ነው። በፍርሃት ህወሀትን ያልተከተሉ የትግራይ ወጣቶች፡ ልጃቸውን ለህወሀት እንደመስዋዕት በግ ያላቀረቡ የትግራይ እናትና አባቶች በህወሀት ጥይት ሲረሸኑ እንደነበር ብዙ የህይወት ምስክርነቶች አሉ። ከአንድ ቤት ከሁለት በላይ የቤተሰብ አባል በህወሀት የጭካኔ እርምጃ የተወሰደባቸውን ቤት ይቁጥራቸው።
የደርግ መንግስት የትግራይ ልጆች ላይ እርምጃ እንዲወስድና ተከትሎም በደርግ የተቆጣው ተጋሩ ወደ ህወሀት ካምፕ ጠቅልሎ እንዲገባ በማድረግ የእጅ አዙር መጠነ ሰፊ ግድያ በመፈጸም ህውሀት የሚጠቀስለት ጉድፍ ታሪክ አለው። ለዚህም የሀውዜኑን ትራጄዲ መጥቀስ ይቻላል። በአይደር ትምህር ቤት የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊትም ከዚሁ አንጻር የሚነሳ ነው። ሃይደር ላይ ቦምብ ሊጥሉ ከአስመራ ሚጎቹ ከመነሳታቸው በፊት የኢትዮጵያው አየር ሃይል መረጃው ነበረው። የባህርዳሩ ጣቢያ እርምጃ ለመውሰድ ሲዘጋጅ ከህወሀት ዋና ማዘዣ ቢሮ በአንድ ስልክ ‘’እረፍ’’ መባሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ሰው መረጃውን አድርሶኛል። ወደፊት ይህም ታሪክ እንደሜቴክ ለአደባባይ ሲበቃ እንሰማዋለን። ታዲያ ከህወሀት ልቆ የትግራይ ህዝብ ጠላት ከወዴት ይኖር ይሆን?
ኢፍትሀዊ ልማትን እንደ አደገኛ ፈንጂ
ትግራይ እስክትለማ ሌላው ክልል ይድማ የሚለው የቆየ አባባል ተጋነነ እንጂ ፍጹም ከእውነት የራቀ አይደለም። ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ የህወሀት አድሎአዊ ልማት ትግራይን አፋፍቷታል። በጠራራ ጸሀይ ከየክልሉ ተወስደው ትግራይ ላይ ከተተከሉት አያሌ ማሽነሪዎች በተጨማሪ ሁሉም ልማት ወደ ትግራይ የሚል መፈክር በህወሀት ዘንድ ከፍ ብሎ ይራገብ ነበር። የትግራይ የተለየ ተጠቃሚነትን መካድ አይቻልም። የትግራይ ምድር እስኪሰምጥ በፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ተጥለቅልቋል።
 አንጋፋው ሙገር ተዳክሞ መሶበ የሲሚንቶ አቅርቦቱን ተቆጣጥሯል። እነድሬዳዋ፡ አርባምንጭና አዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በስልታዊ ማዳከም ከገበያ እንዲወጡ ተደርገው አልመዳ ሰፈር መንደሩን ወሮታል። ቃሊቲ ብረታብረትና መሰል ፋብሪካዎች በቁም እንዲሞቱ ተደርገው መስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጅነሪንግ ከሞያሌ እስከመቀሌ ያለውን ገበያ በበላይነት ይዞታል። በትምህርቱ፡ በጤናው፡ በመሰረተ ልማቱ፡ በየትኛውም የልማት ዘርፍ የትግራይ ክልል ከሌላው በእጅጉን ልቃ መሄዷን ዓለም ዓቀፍ ሪፖርቶች ላይም የተመሰከረ እውነት ነው።
ይሁንና ይህ ልማት ጤናማ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ደረቱን ነፍቶ የሚኩራራበት አይደለም። በላቡ ያፈራው፡ በደሙ ያወረዛው፡ እድገት አለመሆኑን ለአቅመ ማሰብ የደረሰ ሁሉ የሚረዳው ሀቅ ነው። ከሌላው ጉሮሮ እየተነጠቀ ለትግራይ የሚቀርብ ገበታ መርዝ እንጂ የሚያጠግብ እንጀራ አይሆንም። ሌላውን ኢትዮጵያዊ እያቆረቆዘ የሚፋፋ ተጋሩ እደገቱ የጤና እንዳልሆነ ካላወቀ በጊዜ ጤናውን መመርመር አለበት። የተቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል አመዳም አድርጎ የትግራይን ምድር የሚያወዛ የኢኮኖሚ ለውጥ እድሜው አጭር ነው።
ትግራይ በህወሀት ለማሁ፡ አደኩ፡ ተለወጥኩ ብላ ከበሮ ይዛ ከደለቀች መጨረሻው የከበሮው ምት ለሙሾ እንዳይሆን እሰጋለሁ። ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ እንደተባለው ህወሀቶች የምትኩራሩበት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች አንድ ቀን ምሽግ ሆነው እርስ በእርስ እንታኮስባቸዋለን። ። ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩትን የሶርያን ከተሞች ያየ በኢፍትሃዊነት አይመጻደቅም ማለታቸውን ሰምቼአለሁ። ቃል በቃል ለማለታቸው እርግጠኛ አይደለሁም። ባይሉም ግን ሀሳቡ እውነት ነው። አስፈሪ እውነት። በፍቅርና በፍትሀዊ መልኩ ያልመጣ ልማት መጨረሻው አጥፊ ነው። ህወሀት እየዘረፈ፡ እየሰረቀ ትግራይ ላይ ያከማቸው ሀብት በጊዜ ቀመር ተቀምሞ የሚፈነዳ ፈንጂ መሆኑ አያጠያቅም። ለትግራይ ህዝብ እንዲህ ዓይነት አደገኛ ፈንጂ የቀበረው የህወሀት ቡድን እንደምን ወዳጅ፡ ባልንጀራ ይሆናል?
ለማጠቃለል ያህል የሰሞኑ የህወሀት የሰልፍ ጋጋታ የትግራይን ህዝብ ይወክላል ብዬ አላምንም። የትግራይ ህዝብ የእርዳታ እህል ነፍጎት እንደቅጠል ያረገፈውን፡ ቤት ለቤት እያደነ የገደለውን፡ በእጅ አዙር ያስገደለውን፡ በእድገትና ልማት ስም አደገኛ ፈንጂ የቀበረለትን የህወሀት ቡድንን ደግፎ ሰልፍ አይወጣም። የያዘ ይዞታል። ሲለቀው ምሱን ያቀምሰዋል። ለዚህም ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል። የሰሞኑ ሰልፍ የትግራይ ህዝብ ለህወሀት ያደረገው የሽኝት ፕሮግራም ነው ብዬ ወስጄዋለሁ።
Filed in: Amharic