>
5:13 pm - Saturday April 20, 2593

ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል...!! (ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ)

ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል…!!
 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ 
በዘ ሚካኤል ጆርጅ
☞“የኢትዮጵያ ህዝብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የፍትህ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ መንግስትም የህዝብ ጥያቄ መመለስ ውዴታው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም እንደሆነ ገልፀዋል።
☞በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግስት መኖርን የግዴታ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ፍትህን ማረጋገጥ እንደሆነም ገልፀዋል።
☞ፍትህ የሚረጋገጠውም ንጹሃን በኩራት ቀና ብለው የሚሄዱበትና ወንጀለኞች ደግሞ የትም የማይደበቁበት ስርዓት መፍጠር ስንችል ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
☞ኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች እንጂ ወንጀለኞች በኩራት የሚኖሩባት ሀገር መሆን የለባትም፡፡
☞ወንጀል ለፈፃሚው መጀመሪያ ጥቅም ያስገኘለት ቢመስለውም እየቆየ ግን ራሱን እየበላ ሄዶ መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል።
☞አራዊት እንኳን የማይፈፅሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሰው ዘር ላይ የሚፈፅም ሰው በምን አንጀቱ ለወገኑ ይራራል፣ በየትኛው ልቡ ለወገኑ ያስባል በየትኛውስ አእምሮ ለወገኑ ይቆረቆራል ሲሉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥
ወንጀለኛ ማሰቢያው ጥቅም ብቻ ነው፤ ጥቅም ካገኘ ይዘርፋል፤ ያጠፋል፤ ይገላል፤ ያሰቃያል ያወድማል በማለት ነው ያብራሩት።
አሁን የተጀመረው ስራ ሀገር የገደሉ ወንጀለኞችን እነርሱ ለሌላው በነፈጉት ፍትህ ፊት የማቅረብ ስራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የተያዙ ሰዎችም በተገቢ ደረጃና አያያዝ የሚገባቸውን ፍትህ እንዲያገኙ ይደረጋልም ብሏል፡፡
እያንዳንዱ ማህበረሰብ የተሸሸጉትን ወንጀለኞች አጋልጦ ለህግ በማስረከብ ወንጀል የሚያሳፍር መሆኑን እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፥ የህዝቡ ትብብርም እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡
☞የወንጀለኞች መኖሪያ መሆን ያለባቸው ማረሚያ ቤቶች እንጂ ብሄሮች ብሄረሰቦች አይደሉም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የቅጣቱ ዋና ዓላማ አጥፊዎችን መቅጣትና ድርጊቱን መኮነን ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይከሰት መከላከልም ጭምር ነው ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
Filed in: Amharic