>
5:13 pm - Friday April 20, 2779

ህወሓትን ያየ በሌላ አይጫወትም! (ደረጄ ደስታ)

ህወሓትን ያየ በሌላ አይጫወትም!
ደረጄ ደስታ
 
ከያንዳንዷ የመንደር ጩኸት ይልቅ “ኢትዮጵያ” እምትል አንዲት አብይ ቃል እምትሰራውን ተዓምር ተመልከቱ። እና ሰሜንና ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ የሆንክ ሁሉ ለኢትዮጵያ ስትል ተውሳኮችዋን አሳልፈህ ስጣት!
ይሄ ነገር ግን እነ ክንፈን ስትጨርሱ እንጨምርላችኋላን እየተባለ ነው ወይስ ምንድነው? 
እስከመጨረሻው አቅፎ ደግፎ ይዞ መጓዝ ደብቆ ሸምቆ አብሶ ደባብሶ አድሶ ያኑን ቆሻሻ ድርጅት ሰው ፊት መልሶ ለማቆም መጣር ይገርማል። ኤዲያ! ምነው ጃል! ይህን ያህል የድርጅት ችግር አለ እንዴ? እኛ ሰፈር ድርጅት በዝቶ እዚህም እዚያም ሞልቶ ፈልቶ አንድ አልሆን ብሎ ተርፎ ተትረፍርፎ ሲያስቸግረን ፣ አንዳንዱም ተዋህድን ሲለን፣  እዚያ ሰፈር ግን አንድ ለናቱ ነው። አንድ የሆነ ቀማኛ ገዳይ ሸቃይ ወንበዴ ድርጅት አቅፎ ተቃቅፎ መተኛት ምንድነው?  ካልሆነ ግን እንደ ካርታ ጨዋታ አንድ ባንድ እየመዘዙ አሳልፎ ከመስጠት ባንድ ስሙ እሚበውዙትን በዋውዘው ሁሉንም አንድ ላይ ዘርግፈው ቢሰጡን ጨዋታው ባለቀ ነገር በደቀቀ ነበር።
ፈርቶ ነው አይባል ነገር ያ ሰፈር ጀግና ነው ተብሏል። አብሬ ተባብሬ ነው እንዳይል ከእነዚህ አረመኔ ተውሳኮች ማን ይተባበራል ተብሎ ይታሰባል? ግራ የገባ ነገርኮ ሆነ። ይሄ ሁሉ ጉድ እየተሰማ አንዲት ምናምንቴ ሰልፍ እንኳ እንዴት ቸገረች? ደብረፅዮን ብቻቸውን በምድረ በዳ ጮኸው እንዴት ይሆናል? ልጆቻችንን አትንኩብን እንወዳቸዋለን ማለትም እኮ አንድ ነገር ነው። ወይስ ሁሉም እንደ የደቡቡ ደህንነት ሹሙ አቶ ያሬድ ዘሪሁን ከአውላላው ሜዳ ቆመው የህሊና ጸሎት እያደረጉ ነው? መጨረሻው እንዲህ ሊሆን በከንቱ ላለቁት እነዚያ ሰማዕታት ይሆን ጸሎቱ?!
ለማንኛውም ትምህርት ነው። ሞት ደስ ስለሚል ብቻ አይሞትም፣ ጀብድ ጀግንነትም ዝም ተብሎ ስለተቻለ ብቻ አይፈጸምም። አሁንማ  ለጠባብ ዓላማ፣ ለጥላቻና ፣ ዘመን ለሚሽረው ከንቱ ብሔርተኝነት በብላሽ መሞቱ፣ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቢሞት፣ ምን ነበረበት ያሰኛል። አምነው የሞቱለት ቅዱስ ዓላማ ስላለ ብቻ ለዓላማው ሲሉ አምነው የገደሉት የወንድም ነፍስ መኖሩ መቸም መቸም ሰላም አይሰጥም። የሌብነቱን ብንተው ደም ያለበት ትግል ሲረብሽ ይኖራል። ቀና ቀና አያደርግም። እንግዲህ ለቅዱስ ዓላማ የሞቱትም ቢሆን ያው በሜዳ ቀሩ። ባይሆን እንኳ በፍጹም አይቀሩም ዓላማቸው ሰማእትነታቸው ከግብ እሲክደርስ እንታገላለን እሚሉ ሌሎች ተረኛ ጭልፊቶች ዳግመኛ ተነስተው እስክያጃጅሉ መቆየት ግድ ነው። እና ዛሬም አማራ ነኝ ኦሮሞ ነኝ ትግሬ ነኝ እያሉ ፣ ዛሬ አምሮ ነገ አሳፍሮ፣ እንዲህ ለሚቀር የግፍ ወረፋ ከሚሰለፉ ፣ ይልቁንስ ለመንደርና ርካሽ ዓላማ መሞቱን ትተው ሰው ለተባለ ሁሉ ለሚሠራ የጋራ አገር፣ ሰላም ፍትህና የዴሞክራሲ መሞት መቸም የሚሞት ቅድስና አይደለም መባሉ ለዚህ ነው። ሌሎች ሰዎች አብረዋችሁ እማይሞቱት አማራ ኦሮሞና ትግሬ ስላልሆኑ አይደሉም፣ ወይም ገልቱዎች ራሳቸውን በከንቱ እንደሚክቡት ህይወት አሳስቷቸው ሞት አስፈርቷቸው አይደለም።
 ያማረ የታመነበት አገርን በስሜት ከዳር እስከዳር የፈነቀለ ነገር ሲመጣ ሜዳው አልበቃ ሲል እናውቀዋለን። ከያንዳንዷ የመንደር ጩኸት ይልቅ “ኢትዮጵያ” እምትል አንዲት አብይ ቃል እምትሰራውን ተዓምር ተመልከቱ። እና ሰሜንና ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ የሆንክ ሁሉ ለኢትዮጵያ ስትል ተውሳኮችዋን አሳልፈህ ስጣት! ህወሓትን ያየ በሌላ አይጫወትም!
Filed in: Amharic