>

ፍትህ ይንገስ!!! (እዩማ ሙሉ)

ፍትህ ይንገስ!!!
እዩማ ሙሉ
 እኔ የሚያሳሰበኝ ስርአቱ የመኖር ዋስትና (way of life) እስኪመስለን ያሠለጠነንና የመረዘንን ሌብነትንና ነጣቂነትን(bribe) በአጭር ጊዜ እንዴት ተላቀነው እንወጣለን?  የሚለው ጥያቄ ነው!!
የአብይ መንግሥት ሰብአዊ መብት በጣሱና ሀገር በዘረፉ ላይ የሚወስደው የሕግ የማሰከበር እርምጃ የሚደገፍ ነው፡፡ መቀጠልም ይኖርበታል፡፡
ደጋፊ ኖረ አልኖረ፣  ሰው አጨበጨበ፤ አላጨበጨበ ፣ ተቃውሞ መጣ አልመጣ ፍትህ ሊነግስ የግድ ነው፡፡ ፍትህ ማስፈን ኃላፊነት ለሚሰማው መንግስት አንዱን ለማሰደሰት ሌላውን ለማስኮረፍ የሚመዘው ካርድ ሳይሆን አንዱና ዋናኛ ሥራው ነው፡፡
እውነት ለመናገር በሰብዓዊ መብት ጥሰቱም ሆነ በሀገር ዘረፋ የተባሉትና ግኝቶቹ ለኔ ብዙም አልገረሙኝም፡፡ ሁሉን በሞኖፖል የያዘ ቡድን ምንም ነገር ሊያደርግ፤ ምንም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር ይህን መሠሉ አይን ያወጣ ዝርፊያ ሞራል ቢስነት ነው፡፡አውሬነት ነው፡፡
ቆየት ባለው ጽሑፌ ‘የዚህ አገር ዋና ጠላት ድህነት ሳይሆን ሥር የሰደደው ሙስና እንዲሁም የምዝበራው ደረጃ  WORLD CLASS ነው” በሚል መግለጼ ይታወሳል፡፡ ደህነቱንም በአመዛኙ ሙስና-ወለድ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
የሙስና ጉዳይ የካዝና ብር ማጉደል ብቻ አድርገን ካየን እጅግ ምስኪኖች ነን፡፡ ሙስና መዘዙ እጅግ ሰፊና ውስብሰብ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮ ከማነጋቱም በላይ የሥራን ሞራልና ክብር  የሚያጎድል፣ ማሕበራዊ ፍትህን(social justice)  የሚያዛባ፣  ሥራ ያሳጣ፣ ቤት ያሳጣ፣ ዜጎች በሀገራቸው ባይተዋርነት እንዲሰማቸውና እንዲሰደዱ  ያደረገ፣ የዳኛውን አይን ያሳወረ፣  ፍትህን ያዛባ፣
ብዙሐኑን አጎሳቁሎ የበይ ተመልካች የሚያደረግ፣ በአንጻሩ ጥቂቶችን እጅግ ከፍ ከፍ ያደረገ ወዘተ ወዘተ ያመጣብን ይህ  ሙስና ነው፡፡
በአጠቃላይ የዜጎችንና የሀገር እድገት ያቀጨጨ፣ የጊዜያችን ዋነኛ የኢኮኖሚና  የማሕበራዊና የፖለቲካም ጭምር የቀውስ ምንጭ ይህ ሌብነትና ዘረፋ ነው፡፡
እስቲ የቢሊዮኖቹን ምደብ ተተን ወደ ታችና ወደ ጎን ስንሔድ ከቀበሌ ጀምሮ ዞን ፣ወረዳ፣ ክልል ድረስ በተፈጠረ ኔትወርክ በተለይ በተመረጡ የሥራ መስኮች በእቃ ግዢ፣ በጨረታ፣ በመሬት አስተዳደር በቤት ልማት፣ በኮንትሮባንድ በኮንስትራክሽን፣በውል ስምምነቶች፣ በሥልጣን መባለግ በመሳሰሉት ምናልባት ሚሊዮን ሌቦች አይገኙም? ይገኛሉ! ምን ጥያቄ አለው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሀገር  ስለዝረፊያ ስናወራ የጥቂት ግለሰቦችና ቡደኖች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሥር የሰደደ በሸታ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
የእስር እርምጃውን ተከትሎ ብዙዎች ድጋፋቸውን ሲገልጹ እዚህ መንደር ያሉ ተጋሩ ወገኖቼ አካባቢ የተቃውሞ እልፍ ሲልም ፉከራና ዛቻ ይሰማል፡፡ ሰዎች የፈለጉትን አቋም የመያዝ መብት ቢኖራቸውም ካፈነገጡና ከተንሸዋረረ ውሳኔዎች ራስን መጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለነርሱ ያለኝ መልእክት ቢኖር ዘመቻው ፍትህ የማስፈን ከሆነና የትኛውም ግለሰብ ከሕግ በላይ እንዳልሆነ የምታምኑ ከሆነ ብትችሉ ማበረታታት፤ ይህ ካልሆነ ዝም ብሎ ሒደቱን መከታተል እንጂ የግለሰቦችና የቡድን አጀንዳ ወደ ብሔር መልክ ቀይረው ለሚያረግቡትና ለእብሪተኞቹ ማገዶ ላለመሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ኢ-ምክያታዊነት የሚያስተዛዝብና ከሰዎቹ እስር በላይ የፖለቲካ ኪሳራ ያመጣል፡፡ እርግጥ ነው ከነዚህና መሠል ግለሰቦች ጋር ከጥቅም ትስስር የፈጠሩ ከስሜታዊነትና ከክህደት ወጥተው  ምክንያታዊው ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የት እንደምንቆም ብቻ ሳይሆን ከማን ጎን እንደምንቆም አናስተውል ወዳጆቼ!!!
 እኔ የሚያሳሰበኝ ስርአቱ የመኖር ዋስትና (way of life) እስኪመስለን ያሠለጠነንና የመረዘንን ሌብነትንና ነጣቂነትን(bribe) በአጭር ጊዜ እንዴት ተላቀነው እንወጣለን?  የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ስለሆነም ከያንዳንዱ ዜጋ አንስቶ ሁሉም ተቋማት ይህን መሰል አደጋ ገና በእንጭጩ ሊታገሉት ይገባል እላለሁ፡፡ ነገር ግን ዋናው ግባችንም መሆን ያለበት ወንጀለኛ ማሳደድ ሳይሆን ሌብነት የሚጸየፍ፣ስብአዊ መብትን የሚያከብር ማሕበረሰብና ይህንንም ያለማወላወል የሚያስከብር ስርአት መፍጠሩ ላይ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢሳት በኢትዮጵያ የነበረውን ዝርፊያና መብት ጥስት ሳያሰልስ ወደ አደባባይ በማምጣትና ሕዝብን በማሳወቅ ላደረገው ጥረት ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡
Filed in: Amharic