>
5:13 pm - Friday April 19, 2543

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩትን የወርቅነህ ገበየውን ጉዳይ እንዴት እንየው? (ያሬድ ሀ/ማርያም)

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩትን የወርቅነህ ገበየውን ጉዳይ እንዴት እንየው?
ያሬድ ሀ/ማርያም
* ባላየ ይታለፍ ወይስ ከደሙ ነጻ ናቸው?
 
እንግዲህ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የፈጸሙ የመንግስት ባለሥልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ከሆነ የዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፤ የትላንቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየው የነበራቸው የተሳትፎ ደረጃ በአግባቡ ሊጣራ ይገባል። እኚህ ሰው ድርጅቱን እየመሩ ባለበት ወቅት በሳቸው ትዕዛዝ በርካታ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በምርጫ 97 የተከሰተውን ብቻ መጥቀስ ይቻላል። ከሁለት መቶ ያላነሱ ሰዎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲገደሉ፣ ከሰላሳ ሺ በላይ ሰዎች ታስረው ሲደበደቡ እና ሲሰቃዩ ድርጊቱን ይፈጽም የነበረውን የፌዴራል ፖሊስ ይመሩ የነበሩት እኚህ ሰው ናቸው።
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በፌደራል ፖሊስ በተፈጸሙ በርካታ የመብት እረገጣዎች ላይ እኚህ ሰው እጃቸው እንዳለበት በመብት ተሟጋቾች እና በተበዳዮች ሲገለጽ ኖሯል። የእኚህን ሰው ጉዳይ ችላ ማለት አይቻልም። ይህን ነገር ሳያጸዱ ግለሰቡን በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት እንዲቀጥሉ ማድረግም አግባብ አይመስለኝም።
ወርቅነህ ተደምሯል፣ ለውጡን ተቀብሎ፣ ተጸጽቱዋል የሚሉት መከራከሪያዎች ውሃ የሚቋጥሩ አይደሉም፧፧ እነዚህ ጉዳዮች ምናልባት በፍርድ ቤት ከጥፋተኝነት ውሳኔ በኋላ የቅጣት ማቅለያ ነው የሚሆኑት፧ እኔ እየጠየኩ ያለሁት በተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ግለሰቡ የነበራቸው ተሳትፎ በአግባቡ ይጣራ ነው።
ከደሙ ንጹም ከሆኑም ተጣርቶ ይነገረን።
ጋዜጠኞችም እኚህን ሰው በዚህ ጉዳይ ቢያናግሯቸው እና የራሳቸውን ሃቅ ቢነግሩን ጥሩ ነው፡፡
Filed in: Amharic