>

እንዴት ናችሁ ጓዶች የዛሬ ንጹሃን የነገ ወንጀለኞች!!! (ደረጄ ደስታ)

እንዴት ናችሁ ጓዶች የዛሬ ንጹሃን የነገ ወንጀለኞች!!!
ደረጄ ደስታ
* እኔ እምለው የተከሳሹ ስም ሲጠራ አቤት ባዩ አልበዛባችሁም? 
 
ለማንኛውም ዋናው መተማመኑ ላይ ነው። ፍትህ ሰፍኖ በዝርፊያውና ግርፊያው ላይ፣ በሰረቀውና በገደለው ላይ ከተስማማን ሌባውና ገዳዩ የማን ወገን ከመሆኑ ላይ መጣላት ያለብን አይመስለኝም። “ይመለከተኛል” እያለ ራሱን በግድ ተባባሪ ከሚያደርግ ሰው ጋር የለም “አይመለከትህም!” አንተን ደግሞ አይደለም እያሉ መጋፋት ጉንጭ እንደ ማልፋት ነው። ምክንያቱም ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው። ቢሆንም ቢሆንም ግን ከባለቤቱ የሰረቀ ደግሞ ሌባ ነው። አገሩ የተሰረቀበት ወገኑ የተገደለበት ሁሌም ቁጭት ይኖርበታልና ግን እሱም ባለቤት ነው። ስለዚህ ወዲህ በኛም በኩል ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ማለቱ ያስኬዳል። የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ ማለታችን ሰው እንዴት ያየውን እያየ የሚሰማውን እየሰማ ከኔ የተወለዱ ሌቦችና ነፍስ ገዳዮች መነካታቸው በኔ ላይ የተቃጣ ዘመቻ ነው ብሎ አካኪ ዘራፍ ይላል። እውነት ነው ከፍትህ በፊት ቀድመን ያልተፈረደባቸውን ሰዎች ገዳዮች ነፍሰ ገዳዮች ማለታችን ስህተት ነው። የስህተቱ ምንጭ ግን ሀቅ ሳይሆን የፖለቲካ ጥበብና የሰብአዊ ፍትህ ቅብጥርሶ መርህ ንግግርን አለማወቅ ሊሆን ይችላል።
አሁን ማን ይሙት ነገ እነዚህን ሰዎች ፍርድ ቤቱ ቤሳ ቢስቲን አልነኩም ትንኝም አልገደሉም ብሎ እንኳ በነጻ ቢያሰናብታቸው ….ማን ከንጹሃን ተርታ ይመድባቸዋል? በእነዚህ ሰዎች ላይ ግፍ ተፈጽሟልስ ብሎ ማን ተጃጅሎ ይሟገትላቸዋል?  እኛም እነሱም ብለነው እንጂ ሲሆን አይተነው እማናውቀው ወግ ነውና ግን እነዚህ “ንጹሃን” ሰዎች ፍርድ ቤት “ወንጀለኞች” ናቸው እስኪላቸው ድረስ፣ ንጹሃን ሆነው ቢቆዩልን ደስ ይለናል። ተከሰው ያልተፈረደባቸው ሁሉ እንደዚያ ነው መባል ያለባቸው። አደባባዩ አውቋቸው ገና ያልተከሰሱ ያልተያዙት ግን እስኪያዙ ድረስ “እንዴት ናችሁ ጓዶች የዛሬ ንጹሃን የነገ ወንጀለኞች!” እያልን ይሆን… ወይስ ሌላ አጠራር ይኖረዋል? ለማንኛውም አንተ ዘራፊ፣ ቀጣፊ፣ ገራፊ፣ ሌባ..! በተባለ ቁጥር አንዳንዱ ዞር እያለ “አቤት እኔን ነው?” እሚለው ለምን ይሆን? ስም ያለው ሞኝ ነው ይሉሻል ይሄ ነው። ጎሰኝነት ለካ ሞክሼነትም ነው–  አንዱን ሲጠሩት አንድሺው አቤት ይላል!!!
Filed in: Amharic