>

"ነጻነት" (ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም)

“…የሚጣፍጥ ዲስኩር ወደሚመር ተግባር ሲለወጥ ደጋግመን አይተናል፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራበው የአገሩ ባለቤት መሆን ነው፤ …ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠማው በአገሩ ላይ ባለሥልጣና ባለመብት መሆን ነው፤ ….ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀው ቃልና ተግባር የተጣጣመበት ሥርዓት ነው”

 

– መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር)

 

“ነጻነት እንደሳሙና ሙልጭ፣ ሙልጭ እያለ ሲያጓጓን ትውልዶች አልፈዋል፤ ዛሬ ደግሞ አዲሱ የዓብይና የለማ ለውጥ ነጻነትን እያውለበለበ እንቁልልጭ እያለን ነው፤ መብት እንደሰንበቴ ጠዲቅ የሚታደል እየሆነብን ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ትግል ያስከበረው መብት ትዝ አይለኝም፤ የሰራተኞች ማኅበር፣ የመምህራን ማኅበር፣ …ከየት ተነሥተው የት ደረሱ እናውቃለን፤ ድራሻቸው ጠፋ!

ከባህላዊው የአፄ አገዛዝ ወዲህ ጨካኝ የአረመኔ አገዛዞች እስከዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ እየረገጡ ኖረዋል፤ አሁን ለውጥ መጣ እየተባለ በሚወራበት ጊዜ ሲደረግ የምናየው የዜግነት መብትንና ነጻነትን የሚረግጥ ነው፤ በምንም ዓይነት መስፈርት የሕዝቡን አስተያየት ሳይጠይቁ የአገር መሪ (የአገር መሪ) ሾሙልን፤ ምንም ዓይነት መንገድ የጠበቆች አስተያየት ሳይጠይቅ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትም ሾሙልን፤ ሁለቱም እንቦጭ ነው።

ለውጥ ማለት ከዱሮው አሠራር የወጣ፣ በፊት ተነፍገው የነበሩ መብቶችንና ነጻነቶችን የሚያስገኝ ሥርዓት ሲዘረጋ ነው፤ በአዲሶቹ ሰዎች የዱሮው ሥርዓት ሕዝብን መንዳት እንደፈቀደ ቢቀጥል ለውጥ የለም፤ የሚጣፍጥ ዲስኩር ወደሚመር ተግባር ሲለወጥ አይተናል፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የራበው የሀገሩ ባለቤት መሆን ነው፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠማው በአገሩ ላይ ባለሥልጣንና ሕዝብ አልማኩን የሚለምነው በአገሩ ላይ ያለውን ባለቤትነትና ባለሥልጣንነት የሚያውቅለት ሕጋዊ ሥርዓት ነው፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀው ቃልና ተግባር የተጣጣመበት ሥርዓት ነው። …”

[መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር)፣ ዛሬ ለንባብ በበቃችው ፍትሕ መጽሄት ላይ “ነጻነት” በሚል ርዕስ ካሰፈሩት ጽሁፍ ውስጥ የወሰድኩት ሃሳብ – ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

Filed in: Amharic