>

ከትግራይ እንዴት "አይበጅም" ባይ ሰው ይጥፋ? (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ከትግራይ እንዴት “አይበጅም” ባይ ሰው ይጥፋ?
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
እውን የትግራይ ማህጸን ደርቆ ነው? ትግራይን ከሌላው የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ጋር አዋዶ እና አስማምቶ የሚመራ ልጅ አጥታ ነውን? የትግራይ ልጆች ከትህነግ የተሻለ ሀሳብ ማመንጨት አቅቷችሁ ነውን? ከትህነግ የተሻለ ድርጅት ባይኖራችሁ እንኳን እነሱን ተው የሚል ተሰሚነት ያለው ስብሰብ መፍጠር አቅቷችሁ ነውን? እንደው ሌላው ቀርቶ ሰው ጠፍቶ ነው ደብረጽዮንን <ኣዮኻ ናይና> የምትሉት?
.
ትህነግ ወደ ጫካ ገባሁት የሚልበት ምክንያቱ በወቅቱ የነበረውን የትግራይ ወሰን አንሶት ሳይሆን ዲሞክራሲ አጣን፣ የአማራ ባላባታዊ ጭቆና አስመረረን በማለት ነበር። ትህነግ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የራያ መሬቶች በጎንደርና በወሎ ክፍለ ሀገራት ስር መሆናቸው አሳስቦት አልነበረም ጫካ የገባው። አሁን አጥንታችን ይከሰከሳል እያሉ ቢያቅራሩም ያኔ የወሰን እና የድንበር ነገር ጉዳያቸውም አልነበረም። ትህነግ አሁን በያዘው አካሄዱ ወደ ፊት ገና መዓት ችግር በትግራይ ላይ መፍጠሩ አይቀርም፤ መጨረሻው ደግሞ ሽንፈት ነው። ሲሸነፉ ደግሞ ሱዳን ገብተው የእርጅና ጊዜያቸውን ማሳለፋቸው አይቀርም።
.
የትግራይ ልሂቅ በተለይ ወጣቱ መጭውን ጊዜውን ማሰብ አለበት፤ እነዚህ ካንሰሮችን ኣዮኻ ናይና በማለት የልብ ልብ ከመስጠት ተፋቱን ሊላቸው ይገባል። ትህነግ ጦርነት ለመፍጠር የማያደርገው ነገር የለም፤ ጠሚ ዓቢይ ይኼ ሁሉ እብሪታቸው ጠፍቶት አይደለም። የፌድራሉም ሆነ የሌሎች ክልሎች መንገስታት ትዕግስት ምክንያቱ በትህነግ አቅጣጫ መሄድና ማሰብ ለትልቋ ኢትዮጵያ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ነው።
.
ትህነግ <ካልበላሁ ጭሬ ላፍስሰው> መንገዱን ካላቆመና፤ እኛ ካልመራን አገር ይበተን የሚለውን ነገር የሚቀጥል ከሆነ ትርፉ እሰከ መጨረሻው መውደቅ ነው። ሁሉንም የሚያሰፈራው ሲወድቅ ሌላ ይዞ እንዳይወድቅ ነው። ይኼን የትህነግ የሞኝ መንገድ ሊያስቆም የሚችለው አርቆ አሳቢ የሆነው የትግራይ ሕዝብ እና ለነገ የሚጨነቁ ከማህበረሰቡ የወጡ ልሂቃን ካሉ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic