>

ሸገር ደርሶ መልስ ፫ (ክንፉ አሰፋ)

ሸገር ደርሶ መልስ

ክንፉ አሰፋ

          ታማኝ በየነ ይዟት የመጣትን ላፕቶፕ እንደያዘ ወደ አሜሪካ ተመልሷል። ያልተቋጨ የትግል ምዕራፍ ቢኖር እንጂ፤ እሱም እንደ አጅሬ ኖት-ቡኩን ለቲም ለማ ያስረክብ ነበር እያሉ ያራዳ ልጆች ሲቀልዱ ሰማሁ። ትልቁ ችግር መፍትሄ ያገኘ ቢመስልም፤ በትናንሾች የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች ገና አልተፈቱም። እርግጥም ትንሽ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ከባድ ችግርን መፍታት ቀላል ነው። እነኚህ ትናንሽ ቀውሶች ተጭነው የመጡት በኮምፒውተር ቢሆን ኖሮ በርክክቡ ቅጽበት መፍትሄ ይገኝ ነበር። ላፕቶፕ በቀኝ እጅ፤  ሜንጫ ደግሞ በግራ ተጭኖ ገብቷል። ቲም ለማ አንዱን ሲረከብ ሌላውን ግን እስካሁን አልተረከበም….

አዲስ አበባ አሁንም በፖለቲካው ጭስ እንደታፈነች ነው። የጫጉላው ወቅት የነበረው ቡለቃ ቀዝቀዝ ብሏል።   የመደመሩ ፖለቲካ ገና ተነግሮ ሳያልቅ፤ ከሌላኛው ጫፍ በሚሰማ የመቀነስ ስሌት መበረዙ በግልጽ ይታያል። በረጅሙ በርቶ የነበረውን የተስፋ ብርሃን፤ በአንድ ግዜ  ጽልመት ለብሷል። ያልተወራረደ ሂሳብ ባናታቸው ላይ ተሸክመው ቁጭ ያሉ የዚህ ስሌት መሃንዲሶች፤ በስውር የያዙት ክፋት ጠልፎ እስኪጥላቸው ድረስ አውዱን እየበከሉ መጓዛቸውን ቀጥለዋል። ራሳቸውን እንደ ሌላ መንግስት የሰየሙ ወንድሞቻችን፤  በሌሎች መስዋዕትነት የተገኘችን የዚህች የነጻነት አየር ከለላ በማድረግ እንደ ምስጥ ውስጥ ውስጡን የሚሰሩት ደባ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ግን አይደለም። ከየአቅጣጫው በሚሰማው ግድያ እና እልቂት ጀርባ የነሱ እጅ አለበት። የመንግስት ቸልታ ግን እጅግ ያስደነግጣል። የሕዝብ ዝምታ ደግሞ ያስፈራል።

በተደመሩት የተደመምነውን ያህል የሚቀነሱትንም  እያየን እጅግ አዝነናል።

እየተናነቀን የምንውጠው አንድ ሃቅ ቢኖር፤ ሸገር ላይ የነበረው የመደመር ድባብ ወረት ሆኖ መቅረት መቻሉ ነው። ልክ እንደ ግንቦት ዘጠና ሰባቱ ጎርፍ። ስሜቱ በሃይለኛው መጥቶ፤ በስሱ እየበነነ እንደጉም ጠፋ።  ከዚያ አልተመለሰም።  ከቡራዩ እልቂት እና ከአዲስ አበባ ወጣቶች አፈሳ በኋላ፣ የፖለቲካ አየሩ ጥሩ አይመስልም። አዲስ አበባ አኩርፋለች። ከመዲናዋ ሕዝብ ጋር ተቀያይሞ እና ቂም ተቆጣጥሮ፤ ዘላቂ እና የሰከነ ፖለቲካ ማራመድ መሞከር ሳይከብድ አይቀርም። የከተሜው ሕዝብ ሲያፈቅር አይጣል ነው፤ ሲጠላም እንዲያው። ሬንጀር የለበሱ የፖሊስ አባላት በየስፍራው በቡድን በቡድን እየሆኑ የመበተናቸው አዝማምያ አንዳች ነገር እንዳለ ሹክ ይለናል። እንደ ሱናሚ ወጥቶ ዶ/ር አብይን ሰማይ ላይ የሰቀለ ሕዝብ፤ ደራሽ ውሃ እንዳይሆን የተሰጋ ይመስላል። “ሀምሌ ቢያባራ በጋ መስሎን…”  እንዲሉ አንድ አዛውንት!

***

 የፖሊሱ ግርግር ከየትራፊኩ ጭንቅንቅ ጋር ተደምሮ የከተማዋን ጭንቀት አብሶታል። ባለስልጣን ባለፈ እና በሄደ ቁጥር መንገድ የመዝጋቱ አባዜ አሁንም አልቀረም። የመንገዶች መጣበብ፤ ስርዓት ያለማክበሩ ነገር ጋር ተደምሮ በነዋሪው ላይ ፈተና ሆኗል። የ፲ ደቂቃ መንገድ ለመጓዝ ሶስት እና አራት ሰዓት የመውሰዱ ነገር አዲስ አበቤን በእጅጉ አማርሯል።  የእግረኞች፣ የከብቶች እና ተሽከርካሪ መንገድ በውል እስካልተለየ ድረስ የትራፊኩ ጉዳይ እስከ ወዲያናው የሚፈታ አይደለም። በሆላንድ ሃገር፤ አስራ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪ ሕዝብ፤  ስምንት ሚልዮን ተሽከርካሪ አለ። በዚህች የበሬ ግንባር በምታክል ሃገር፤ ስምንት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪ ያለ አንዳች ችግር ይንቀሳቀሳል። አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ተሽከርካሪ ባለበት በኛ ግዙፍ ሃገር ግን ከሚሊዮን በላይ አደጋ እንሰማለን።

 የከተማው ትራፊክ ለኔ ብጤው ተሳፋሪ ብርክ ያስይዛል። ከአራት አቅጣጫ የሚመጣ ተሽከርካሪ እየተሽሎከለከ ሲሄድ አይን ካልጨፈኑ በቀር መሸማቀቁ ኪሎ ያስቀንሳል። ከዚያ ሁሉ የመኪና ማጥ ውስጥ ገብቶ፤ በዚያ ፍጥነት መውጣት መቻል በራሱ ድንቅ ሳይሆን ተዓምር ነው። በመዲናችን ያፈጠጠ የትራፊክ ችግር አለ።  በቂ እና የተመቻቸ መንገድ ያለመኖሩ ብቻ አይደለም ችግሩ። ጥራታቸው ያልተፈተሹ ተሽከርካሪዎች እና ያለ አንዳች ትምህርት የሚሰጥ መንጃፈቃድ ዋነኞቹ የአደጋ መንስኤዎች ናቸው።

ፒያሳ ላይ የታዘብኩት የታክሲ ስልፍ እጅግ አስደንግጦኛል።  ከሰባ ደረጃ የጀመረው ሰልፍ ማቆምያው አያሌው ሙዚቃ ቤት በር ላይ ነበር። በስራ ሰውነቱ ዝሎ የዋለ ሕዝብ አንድ መስመር ሰርቶ ተራውን ይጠብቃል። ስርዓት አስከባሪ የለም።  በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህ የታክሲ ሰልፈኛ ላይ የማያባራ ዝናብ ይጥላል፤ መብራት የለም። እድለኛ ተሳፋሪ ከሰዓታት በኋላ የታክሲ ወረፋው ይደርሰዋል። ነዋሪው ሕዝብ ችግሩን እንደ እለት-ተለት ተግባር ለምዶት ኖሮ፤ ሲያማርር እንኳ አይሰማም። ዝናብ በዘነበ ቁጥር የመብራት መጥፋቱ ምስጢር ግን ሊገባኝ አልቻለም።

 

***

 አለተ ረቡዕ፤ ፕ/ር መረራ ጉዲናን በአካል ለማግኘት ፈልጌ ስልክ ደወልኩ። ስልኩን አንስተው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ፤ በአምስተኛው በር በኩል እንድጠብቃቸው ነገሩኝ። ስድስት ኪሎ እንደደረስኩ ወትሮውን አካባቢው ከነበረ ክስተት ፍጹም የተለየ ነገር ታዘብኩ።

 “የመመረቂያ ጽሁፍ ካስፈለገህ በጥራት እንሰራለን።” አለኝ እበር ላይ የቆመ አንድ ደላላ። የ “ዲግሪ” እና የ “ጥናታዊ ጽሁፍ” ንግድ በህወሃት ዘመን እንደተፈጠረ ቀድሜ ብሰማም በዚህ ደረጃ ወርዶ  ግልጽ ይሆናል ብሎ መገመት ግን ይከብዳል። በዚያች ቅጽበት የባችለር፣ የማስተርስም ሆነ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቅያ ጽሁፍ በየፈርጁ እየተዘጋጀ በገንዘብ እንደሚሸጥ በተጨባጭ አረጋገጥኩ። በዚህ አገልግሎት የሚጠቀሙት የህወሃት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆኑ ተራው ተማሪም እንደሆነ ተገነዘብኩ።

 አምስተኛ በር ላይ እንደደረስኩ፤ ፕ/ር መረራ ዘንድ እንደመጣሁ ለጥበቃው ነገርኩት። “ፕ/ር መራራ ስራ ካቆሙ ሰነብተዋል።” ስትል መልሰችልኝ አንዷ የጥበቃ አባል። እዚያው ሆነው የፕ/ር መረራን ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውን እንኳ ያለመስማታቸውን ስመለከት፤ ሕዝቡ ምን ያህል ከመረጃ እንደራቀ ያመላክተናል።  በጥቃቅን መረጃ ሳይቀር እኛ ውጭ ያለነው ከሀገር ቤቱ እንደምንሻል የተረዳሁት ያኔ ነው።

 በመጨረሻ ግቢ ገብቼ ወደ የፖለቲካ ሳይንስ ዲፓርትመንት አመራሁ። ዩኒቨርሲቲ መማርያ ክፍሎች፤ ላውንጆች፤ ዲፓርትመንቶች በእጅጉ ማርጀታቸውን ታዘብኩ።  ስድስት ኪሎ በተለምዶ ”አፓርታይድ” የሚባለው ላውንጅ (ተማሪዎች መግባት የማይፈቀድላቸው ካፌ)  ቁጭ ብለን ስለሃገርኛው ፖለቲካ ትንሽ አወጋን። የአትላንታው ዳዊት ከበደ አብሮኝ ስለነበር ስለ ፊንፊኔ ታሪክ ወግ ጀመረ…። አምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ላይ የሳቸው አሻራም ስለመኖሩ ለምንጠይቃቸው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጡም፤ በ”ፊንፊኔ ኬኛ” የፖሊቲካ ትርክት የፕ/ር መረራ ጉዲና እይታ የተለየ መሆኑን ተረዳን። ጥግ እና ጥግ ሆኖ ከመጠዛጠዝ፤ ሁሉም መሃል ድረስ መጥቶ መገናኘት አለበት። አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም።  አዲስ አበባ ያለ ኦሮሚያ፤ ኦሮሚያ ደግሞ ያለ አዲስ አበባ ህልውና ሊኖራቸው አይችልም ባይ ናቸው። የጥያቄው ምላሽ ሾላ በድፍን ይሁን እንጂ፤  እሳቸው የሚመሩት ድርጅት የተሳተፈበት መግለጫ ለራሳቸው እንግዳ እንደሆነባቸው ግን ከአቋማቸው መረዳት አይከብድም።

ኢትዮጵያዊነታቸው ከኦሮሞ ማንነታቸው ጋር የሚጋጭባቸው ሰው አይደሉም ፕ/ር መረራ ጉዲና። እንደሌሎቹ የኦሮሞ ኢሊቶች፤ የቡርቃ ዝምታን የፈጠራ ትርክት እና የአኖሌን ተረት-ተረት ሳያጣጥሙ የሚጋቱ ሰው አይደሉም።  ለፖለቲካ ጥራት ሲባል የሚከወነውን የእሹሩሩ ፖለተካ ቁማርንም አይጫወቱም። የእያንዳንዱ መብት ተጠብቆ፤ ሁሉም በእኩልነት አብሮ የሚኖርባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ነው ትግላቸው።

***

ሕዝብ ሁሉ ቧልተኛ፤ አሿፊ፤ ፌዘኛ እየሆነ እንደመጣ ታዘብኩ። ቀልደኛው በዝቷል። በፖለቲከኞች ንግግር ላይ አቃቂር ማውጣት የተለመደ ነገር ነው። በችግሩ ላይ የሚያሾፍ፤  በራሱ ላይ የሚቀልድ ሰው መብዛቱ ተፈጥሯዊ ባይሆንም ጤነኝነት የጎደለው ክስተት አይደለም።  ቀልድ የመንፈስ ጭንቀትን ማስወገጃ  መሳርያ መሆኑን የስነ ልቦና ጠበብት ይናገራሉ። ምንም ደስታ በሌለበት፤ ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው ለማለት ቢከብድም፤  “ድብርትንና ጥይትን ተኝቶ ማሳለፍ ነው” እንዳሉ፤ ችግርን በሳቅ መቅበር ጤንነት ነው። የቧልቱ ነገር እንዳለ ሆኖ፤ የሰውን የፈጠራ ችሎታ ሳያደንቁ መለፍ ግን አይቻልም። አርቲስት ሃና ዮሃንስ የነገረችን ቀልድ ነው። አንዱ ባለጊዜ ጠርሙስ ውስኪ ጠጥቶ ሲያሽከረክር በትራፊክ ይያዛል። ትራፊክ ፖሊሱ የአልኮል መጠን መለኪያ ማሺን ላይ እንዲተነፍስ ያዘዋል። አሽከርካሪው ተነፈሰ፤ ምንም ያለም። ደግሞ ተነፈሰ፤ አሁንም የለም። በመጨረሻ ከአልኮል ነጻ መሆኑ ሲነግረው ደንግጦ ይጠጣበት ወደነበረ መሸታ ቤት አመራ። ከአልኮል ጠርሙስ ውሃ እየቀዱ እንደጋቱት ተሰማው።  “የተወጋ” መጠት መሸጥ የተለመደ ነው።  ፖሊሱ የያዘው ቻይና ስሪት አልኮል መቆጣጠርያ ማሽንስ ትክክል ስለመስራቱ ምን መተማመኛ ይኖረዋል? ልክ ሳይፈተሽ እንደሚገባው የቻይና ሲኖትራክ ገና ብዙ ጸብ ማስነሳቱ አይቀርም።

 ቀልድን ተናግሮ የማይጨርሰው ዘላለም ኩራባቸው ጋር አንድ ምሽት አሳለፍን።  አፉ ለአፍታ እንኳን አይከደንም። ከአንደበቱ የሚወጣው ነገር ሁሉ ጦሽ ያደርጋል። የሚናገረው ቀልድ መሬት ላይ ጠብ የማይል ቁምነገርን የተሸከመ ነው። ስለ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የነገረን ቀልድ ብዙዎቻችንን አስቆናል። የአቶ መልሰን አስክሬን ለመመርመር የመጣ ቡድን፤  አስከሬኑን ከመቃብር ሲያወጣው አካላቸው እንዳለ ነው። ምስጥ አልበላውም። ምስጦቹ ሁሉ ጥግ ይዘው በቡድን በቡድን ተደራጅተው እርስበርስ ይባላሉ። ሰውየው ምስጦቹንም በዘር አደራጅተው ኖሮ እነሱ ሲባሉ የአቶ መለስ አስከሬን እስካሁን አልነኩትም።

***

 

  አንድ ዘመድ ቤት ለጥየቃ ሄጄ በግድግዳው ላይ ያሉ ፎቶዎች ማየት ጀመርኩ። የተሰቀሉት ፎቶዎች በሙሉ የዲያስፖራው ብቻ ናቸው። ሃገር ቤት ካሉት ልጆች የአንዳቸውም ፎቶ አልተሰቀለም።  “የናንተ ፎቶ ለምን አልተሰቀለም?” ብዬ ጠየቅኳት አንደኛው ልጃቸውን። “ዲያስፖራን እንጂ፤  ‘ድሃ ቦራ’ ን ማን ከቁብ ይቆጥረዋል?” ስትል መለሰችልኝ።  እውነቷን ነው። ለዲያስፖራው ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ ክብር እና ትኩረት በመንግስት ደረጃም ይስተዋላል። ሂልተን እና አሌሌ ሆቴሎች እየፈረሙ የሚበሉ ዲያስፖራዎችንም ታዝበናል። 

እውቀት ወይንም ገንዘብ ያካበተን ዲያስፖራ ወደ ሃገሩ እንዲገባ ፤ ገብቶም እንዲሰራ ከማበረታታት እና ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ሌላ ነገር ነው። ከውጭ ለሚገባውን ብቻ ለይቶ የተለየ መብት መስጠት ተገቢ አይደለም። መንግስት የትራንስፖርት እና የሆቴል ወጪዎችን ሸፍኖለት የሚገባ ዲያስፖራ ጥገኛ ከመሆን ውጭ ለሃገር ምንም እንደማይፈይድ ግልጽ ነው። ከዚህ ቀደም ለፕሮፓጋንድ ፍጆታ ብቻ ሲባል በምእራቡ አለም የመንግስት ተጧሪ ሆነው በዌልፌር ይኖሩ የነበሩትን ሰብሰበው ያስገቡ ነበር።  ይህንን ይቃወሙ የነበሩ ዲያስፖራ ወገኖች አሁን ራሳቸው ሲፈጽሙት ትክክል የሚሆንበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም።  ቆሎ ለዘር እንዶድ ለድግር አይሆንም…

 (ማሳሰብያ፡ ባለፈው ጽሁፌ ላይ ወዳጄ ሼክስፒር ፈይሳን መጥቀሴ በአሉታዊ መልኩ እንደተተረጎመ ተረድቻለሁ።  የደህንነቱ ሰው እሱንም የቀረበው ወደ ሃገር ቤት እንዲገባ እና እድገቱን እንዲመለከት ብሎ ነበር እንጂ ከነሱ ጋር ንክኪ ኖሮት እንዳልሆነ ማስረገጥ እሻለሁ።  ሼክስፒር የቀረበለትን ጥሪ በተመሳሳይ ምክንያት አልተቀበለም ነበር።) ከኢትዮጲስ ጋዜጣ ቁትር ፯ የተወሰደ

…ይቀጥላል 

  

 

 

Filed in: Amharic