>

የኦሮሞ ፖላቲካ ራሱ ተሻግሮ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያሻግር  የነፃ አውጪ ዘመን ፖላቲካ ከኦሮሚያ መክሰም አለበት!!! (ብርሀን መስቀል አበበ)

የኦሮሞ ፖላቲካ ራሱ ተሻግሮ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያሻግር  የነፃ አውጪ ዘመን ፖላቲካ ከኦሮሚያ መክሰም አለበት!!!
ብርሀን መስቀል አበበ
እስከ April 2018  ማለትም  በ( #OromoProtests) ቲም ለማ (#TeamLemma) ወደ ክልል እና ወደ  ፌዴራል ስልጣን እስኪመጡ  ድረስ  የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች (በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የተለያዩ  ነፃ አውጪ ግንባሮችን ጨምሮ) ዋና አላማቸው የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ከተዘረጋው አፋኝ አስተዳደር  ነፃ ወጥቶ በእውነተኛ ፌዴራል አስተዳዳር ራሱን በራሱ እንዲያስተዳዳር እና ኦሮሞ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት  የሚገባውን ስፍራ ይዞ ኢትዮጵያን  እንዲመራ ማስቻል ነበር።
የኦሮሞ ህዝብ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ  በደረገው የተቀናጀ  ሰላማዊ ትግል፣ እና በፕሬዚደንት ለማ እና በጠቅላይ ሚንስትር አብይ ( #TeamLemma ) በሰጠው ድርጅታዊ አመራር የህወሃትን መዋቅር ከኦሮሚያ ውስጥ ከማፍረስ አልፎ ህወሃትን ከመዕከላዊ መንግስት በማበረር በኢትዮጵያ ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም መንገድ ወደ ማመቻቸት ተሸጋግሯል።
ስለዚህ  ከApril 2018(ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በፌዴራል፣ ፕሬዚደንት ለማ በክልል ደረጃ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ስልጣ እስከ መጡበት ቀን በኋላ)   የኦሮሞ የፖላቲካ  ድርጅቶች( ነፃ አውጪ ግንባሮች እና ቡድኖችን ጨምሮ) የተደራጁበት አለማ ግቡን መቷል ማለት ነው። ድርጅቶቹ ለራሳቸው በስቀመጡት ራዕይ መሠረት የኦሮሞ ህዝብ ነፃ ወጥቷል።
አሁን ኦሮሚያን የሚያስተደድረው በኦሮሞ ህዝብ ታርክ ከ150 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ   በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በጀግንነቱና በአርቆ አስተዋይነቱ የተመሰከረለት ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ  ነው ። የኢትዮጵያ ፖላቲካም ቢሆን  በኦሮሞ ማንነቱም ሆነ በኢትዮጵያዊነቱ የኮራና በኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በተወደደና በተከበረው በብልህ መሪያችን በጠቅላይ ሚንስት አብይ አህመድ  እጅ ነው።
ስለዚህ አሁን በኦሮሚያም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የኦሮሞ ህዝብ የሚፈልገው በትግሉ ያገኘውን ድል የሚያጠናክር እና ከ150 ዓመታት በላይ የፈረሱትን የኦሮሞ ህዝብ የፖላቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተቋማትን መልሶ የሚገነቡ ራዕዎች፣ አደረጃጀቶ እና መሪዎችን ማግኘት ነው።
ከ1960ዎቹ እስከ 2018 ከ60 ዓመታት በላይ የተካሄደውበየኦሮሞ ነፃ አውጪዎች ፖላቲካ ዘመን አሁን በድል ተጠናቋል። ከዚህ በኋላ ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአገር ግንባታ ዘመን ነው። የአገር ግንባታ ፖላቲካ ደግሞ ከነፃ አውጪ ፖላቲካ የተለየ ራዕይ፣ አደረጃጀት፣ አመራር እና እውቀት ይጠይቃል።
ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ አሁን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ፖላቲከኞችን እስከ ዛሬ ለኦሮሞ ህዝብ ትግል  ለደረጉት አስተዋፆ አመስግኖ በክብር በጡረታ የሚሸኝበት ጊዜ ነው። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።
1ኛ) አብዛኞቹ የኦሮሞ የነፃ አውጪ  ዘመን ፖላቲከኞች(ከ1960 ዎቹ ጀምሮ እስከ 2018 ማለትም ለ 60 አመታት በፖላቲካ የተሳተፉ አዛውንቶች)  በእድሜ የገፉ እና ቢያንስ  ከ65 ዓመት በላይ በመሆናቸው ከ 35 ዓመት በታች ያለው የኦሮሞ ህዝብ ከ76% በላይ የሆነበትን ወጣት የኦሮሚያ ህዝብ የሚመሩበት እውቀትም፣ ጥበብም ሆነ ልምድ የላቸውም። ልምድ አላቸው ከተባለም በውጪ ሆኖ የፖላቲካ ቦታ ሳይዙ  የማማከር ስራ መስራት ብቻ ነው።
2ኛ) የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የኦሮሚያ መንግስት እነዚህን አንገፋ የኦሮሞ ፖላቲከኞች በጡረታ ሲሸኝ ታሳቢ ማድረግ ያለበት ሰብአዊና ፖሊሲ ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በኦሮሞ ነፃ አውጪ ፖላቲካ የተሳተፉት የኦሮሞ የፖላቲካ ታጋዮች እድሚያቸውን አና ዘመናቸውን በሙሉ  ለኦሮሞ ህዝብ ስለሰው አብዛኛቹ ጡረታ የሚወጡበት የግል ንብረት እና ሃብት የላቸውም። ስለዚህ ህዝብ እና መንግስት ከህዝብ በሚሰበሰብ ታክስ የጡረታ ደሞዝ እና መኖሪያ ስፍራ ቢያመቻችላቸው ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለአገር ክብር ነው።  ከዚህ ሰብኣዊ እሳቤ በተጨማሪ ይህን ማድረግ የእድሜ ባለፀጋዎቹ ፖላቲካን እንደ ገቢ ማግኛና ብቸኛ መኖሪያ መንገድ እንዳይመለከቱ ያደርጋል። ከዚህም በላይ የነዚህ አንጋፋ ፖላቲከኞች በጡረታ በክብር መሸኘት ደጋፊዎቻቸውንም ሆነ በኦሮሞ ህዝብ የፖላቲካ ትግል የተሳተፉትን ሁሉ ሞራል ያበረታታል። የኦሮሞ ህዝቡንም ህብረት ያጠናክራል።
3 ኛ) ሌላው የኦሮሞ ህዝብ መገንዘብ ያለበት እውነታ ከዚህ በኋላ የኦሮሞ ህዝብ በፖላቲካ አሻጥርም ሆነ በታጣቂዎች ጉልበት ህወሃትን ጨምሮ  በሌሎች የኦሮሞ ህዝብ ጠላቶች አገዛዝ  ስር የሚወድቅበት ሁኔታ በጭራሽ የለም። ልኖርም አይችልም። አሁን የኦሮሞ ህዝብ ብሄራዊ ጥቅሙን የሚያውቅ እና የሚያስከብር፣ በማንም የማይደፈር የፖላቲካ ማህበረሰብ ሆኗል።  ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ ፖላቲካ ከዚህ በኋላ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ፖላቲካ ጥበቃም ሆነ ሞግዝትነት አያስፈልገው። ይልቁንም የነፃ አውጪ ፖላቲካ ለኦሮሞ ህዝብ ብሄራዊ ጥቅም ጎጂ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ አስተሳሰቡ ሳይቀር መፍረስ አለበት።
4ኛ)  የኦሮሞ ህዝብ ፖላቲካ ራሱንም ሆነ ኢትዮጵያን ህዝብ ወደ ህዝባዊ መንግስት ስረዓት  የሚያሸጋግረው በኦሮሞ ነፃ አውጪ ዘመን ፖላቲካ ሳይሆን ኢትዮጵያ  አቀፍ  እና ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያሳትፍ የፖላቲካ ራዕይ፣ አደረጃጀት እና አመራር በመስጠት ነው። የኦሮሞ የነፃ አውጪ ዘመን ፖላቲካ ከዚህ በኃላ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የኦሮሞ ህዝብን ፖላቲካ እንዲጠራጠር እና በኦሮሞ መሪዎች ላይ እምነት እንዳይጥል  ከማድረግ ውጪ ምንም ፖላቲካዊ ፋይዳ ስላሌላ ሙሉ በሙሉ መክሰም አለበት።  ስለዚህ የተፈጠሩበት አላማ ያለቀባቸው እና ጊዜ ያለፈባቸው  በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚጠሩ የነፃ አውጪ ዘመን የፖላቲካ ድርጅቶች ህዝቡ ላይ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ 1ኛ) ራሳቸውን በራሳቸው ማክሰም( ማፍረስ)፣ 2ኛ) በክብር ጡረታ መውጣት፣  ወይም  3 ኛ) አሻፈረኝ በፖላቲካ እቀጥላለው ካሉ  አሮጌውን የነፃ አውጪ ዘመን የፖላቲካ ራዕይ፣ አደረጃጀት እና አመራር  አፍርሰው በአዲስ ራዕይ፣ አመራር፣ እና አደረጃጀት ተደራጅተው የኦሮሞንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖላቲካ ለመምራት መዘጋጀት አለባቸው።
5 ኛ)  አሁን የኦሮሞ ህዝብ ጠንካራ  ሽምቅ ተዋጊ ከሚፈልግበት የኦሮሞ ነፃ አውጪ  ዘመን ፖላቲካ  ወጥቶ ጠንካራ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት፣ባህል እና ስነ ልቦና የተላበሰ ለህዝብ፣ለአገር እና ለህግ  ተገዥ የሆነ  የፖሊስ፣ የመከላከያ እና የደህንነት ኃይል ወደ ሚገነባበት ዘመን ተሸጋግሯል። በመሆኑም ለኦሮሞ ህዝብ የሽምቅ ተዋጊ ለመገንባት በየበረሃው ሲዳክሩና ሲለፉ የነበሩ የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች አሁን ትጥቃቸውን እና የሰው ኃይላቸውን በቆራጥነት እና በጀግንነት የኦሮሞ ህዝብ እየመሩ ላሉት ለፕሬዚደንት ለማ እና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ   አስረክበው ከፖላቲካው ሜዳ መክሰም ወይም ጡረታ መውጣት አለባቸው።
ስለዚህ  የኦሮሞ ህዝብ ፖላቲካ ራሱ ተሻግሮ  የኢትዮጵያን ህዝብ እንድያሻግር  እስከ ዛሬ የነበሩት የኦሮሞ የነፃ አውጪ ዘመን  የፓላቲካ ድርጅቶች ወይ መክሰም ወይም በጡረታ ከፖላቲካው አለም ወጣት ወይም በሌሎች የ21ኛ ክፍለ ዘመን የፖላቲካ ራዕይ፣ አደረጃጀት እና አመራር ባላቸው የፖላቲካ ድርጅቶች  መተካት አለባቸው።
 ከዚህ ውጭ ግን በኦሮሞ ህዝብ መካከል የፓላቲካ፣ የክልል እና የሃይማኖት ክፍፍል በመፍጠር   የኦሮሞ ህዝብ በስንት ትግል በመጣው ለውጥ ላይ እንቅፋት ለመሆን የሚፈልጉ ኃይሎችን የኦሮሞ ህዝብ ለአንድ ቀንም እንደማይታገሳቸው መታወቅ አለበት።
Filed in: Amharic