>

የዋለልኝ መኮነን የአማራ እስረኞች. . .  !!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የዋለልኝ መኮነን የአማራ እስረኞች. . .  !!!
 አቻምየለህ ታምሩ
በምስሉ  የሚታዩት ሴቶች  ውስጥ ከሶስቱ በስተቀር የተቀሩት አስራ አንዱ  ወይዛዝርት  በ«ያ» ትውልድ ትርክት መሰረት የአማራ ባሕል ተጭኖባቸው በዋለልኝ  መኮነን «የብሔር፣ ብሔረሰቦች እስር ቤት» ውስጥ ገብተው  አማራ «የብሔር ጭቆና» ያካሄደባቸው ናቸው።  ዋለለኝ መኮነን  በፈጠራቸው እስረኞች ላይ  «የአማራ ባሕል ተጭኖባቸዋል» በማለት ተካሄደ ያለውን የማንነት ማጥፋት ፖሊሲ ለማሳየት ያቀረበው ምሳሌ  ጋሞ እያሳመረ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ  የሚያለብሰውን ሸማን ነበር።
ከወይዛዝርትም  መካከል ከሶስቱ በስተቀር  የተቀሩቱ ዋለልኝ መኮነን የሚባለው በሥርዓት ትምህርቱን  ያላጠናቀቀው  አፍ ነጠቅ አማራ ጫነባችሁ ያላቸውን  ሸዋ አሽቀንጥሮ ለመጣል  ጫካ የወረዱ  የነጻ አውጪ ድርጅቶች  አመራሮች ናቸው።  ያካሄዱት የነጻ አውጪ  ትግል  አላማም  አማራ ሸማ ጫነባቸው  የተባሉት  የዋለልኝ መኮነንን እስረኞች «ነጻ » ወጥተው  ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ አዳዲስ የአካባቢ አገራትን ለመመስረት ነበር።
የ «ያ ትውልድ» የጎሳ ድርጅቶች  እንዳሉት  ሸማን አማራ በዋለልኝ እስረኞች ላይ የጫነው ልብስ  ከነበር ዛሬ ነጻ አወጣናቸው የሚሏቸው  «ብሔሮች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች» ነጻ ወጥተዋል በተባለበት ዘመን ከዋለልኝ እስር ቤት ለመውጣትና ሸማን አስቀንጥሮ ለመጣል የታገሉ የነጻ አውጪ ድርጅቶች መሪዎች  ላይ የአማራን ሸማ ማን ጭኖባቸው ነው ሸማ  የለበሱት? ይህንን ጥያቄ ሸማን አማራ  በዋለልኝ እስረኞች  ላይ የጫነው ባሕል ነው ብላችቹ  የታገላችሁ የ «ያ ትውልድ» አባላትና የመንፈስ ወራሾቻቸው  መልሱልን እስቲ?
ዛሬ  ላይ ከአማራ የብሔር ጭቆና አላቀቅናቸው ያላችኋቸው  ብሔር፣ ብሔረሰቦች እንዴት ብለው ነጻ ካወጣችኋቸው በኋላ አማራ ሊጨቁናቸው የጫነባቸውን ሸማ ይለብሳሉ? ነጻ ወጥተው ሳለ ጭቆናን መረጡ ማለት ነው  እንዲህ በፎቶው ላይ እንደሚታየው የራሳቸው ባሕላዊ ልብስ ሊያደርጉት የቻሉ? በነገራችን ላይ የዛሬዎቹ የኦሮሞ አባ ገዳዎችም የሚለብሱት ሸማ ነው። ኦነግ ግን የታገለው  አማራ ጫነባቸው ያለውን  ሸማ የኦሮሞ አባ ገዳዎች እንዳይለብሱ ነበር። ሆኖም ግን አባገዳዎቹ በየአደባባዩ የባሕል ልብሳቸው አርገው የሚለብሱት አማራ ጫነባቸው የተባሉትን ሸማ ነው። በነገራችን ላይ አባገዳዎች በተለይም ቆቱዎች ከሐረር ከተማ  በገንዘባቸው  እየገዙ ማንም ሳያስገድዳቸው ሸማ ይለብሱ የነበሩት ምኒልክ ወረራቸው ከመባሉ ከአስርት አመታት በፊት ነበር።
ጭቆና ከሚባለው ፈጠራ ጋር ተያይዞ ጎሰኞች የሚያነሱት ትርክት አለ። የአገራችን ጎሰኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚጠሉት ነበረ ያሉትን ጭቆና ስለሚያስታውሳቸው እንደሆነ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነበረ  ያሉትን ጭቆና የሚያስታውሳቸው ከሆነ ዋለልኝ መኮነን አማራ ሊጨቁናቸው ጫነባቸው ያላቸውን ሸዋ ዛሬ ሲለብሱት ነበረ ያሉትን ጭቆና አያስታውሳቸውም ማለት ነው?  አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ እንዴት ይሆናል? ሰንደቅ ዓላማው ነበረ ያሉትን ጭቆና የሚያስታውሳቸው ከሆነና በዚህም ከጠሉት አባ ገዳዎችና እዚህ የዋለልኝ መኮነን እስር ቤት የነበሩት ጭቁኖች ሸማን ሲለብሱ ለምን  ነበረ የተባለውን ጭቆና  አያስታውሳቸውም?
በነገራችን ላይ ዋለልኝ መኮነን የተባለው አፍ ነጠቅ ዛሬ  በሕይዎት ቢኖርና ነጻ ወጡ የተባሉት  እሱ በፈጠረው እስር ቤት  ይኖሩ የነበሩት እነዚህ  ብሔር፣ ብሔረሰቦች እንዲህ  ሸማ ለብሰው  ባደባባይ  ሲያቸው  ዛሬም ቢሆን  «አማራ ጭኖባቸው ነው የለበሱት» ከማለት አይመለስም ነበር ።
Filed in: Amharic