>

በዚህ ወቅት የሴቶች ወደሥልጣን መምጣት ሸፍጥ እንጅ ስኬት አይደለም! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

በዚህ ወቅት የሴቶች ወደሥልጣን መምጣት ሸፍጥ እንጅ ስኬት አይደለም!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
በዐቢይ ሸንጎ ሴቶች ሐምሳ በመቶ ድርሻ ተሰጥቷቸው መሾማቸውን ከቁምነገር ስላልቆጠርኩት በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አልፈልኩም ነበር፡፡ ሹመቱ አቅምን፣ ብቃትን፣ ችሎታን ካላገናዘበ ጨዋታ እንጅ ቁምነገር አይደለምና፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የተሾሙት ሴቶች በሙሉ ከወያኔ/ኢሕአዴግ በመሆናቸው ትኩረት የሚስብ ስላልነበረ ነው፡፡ አሁን ወ/ሮ መዓዛ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊቀመንበር ሆና መሾሟ ግን በዚህ በሴቶች መሾም ዙሪያ አንዳች ነገር ማለት እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም እስከማውቀው ጊዜ ድረስ ወ/ሮ መዓዛ የወያኔ/ኢሕአዴግ አባል አይደለችም፡፡ ናት ሲል የሰማሁትም ሰው የለም፡፡
ይልቁንም በአቶ መለስ ዘመን “ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር!” የሚል ድርጅት በመመሥረትና ለተገፉ ለተበደሉ ግፍ ለደረሰባቸው ሴቶች ጥብቅና በመቆም ለመብታቸው በመታገል ወያኔን ስትተናነቅ የነበረችና ወያኔ ግፎቹንና ወንጀሎቹን እየሸሸገ በአደባባይ ንጹሕና ዲሞክራት (አስፋኔ ሕዝብ) መስሎ መታየትን ችሎበት በነበረበት ዘመን መጋረጃውን ገልጣ የወያኔን ኢፍትሐዊ አንባገነን አገዛዝነት ለዓለም ያሳየች፣ ያጋለጠች፣ ነጥብ አስጥላ ያስፎረሸች ታጋይ መሆኗን ነው ታሪኳ የሚያሳየን፡፡
ታስታውሱ እንደሆነ ከ18 ዓመታት በፊት በ1992/93ዓ.ም. ላይ አንድ ባለሥልጣን ዘመድ የነበረው ነውጠኛ ወጣት አንዲት የአዲስ አበባን ነዋሪ ወጣት ልጅ “ወደድኩሽ!” በማለት በኃይል “እሽ!” ለማሰኘት በሚያደርገው ጥረት ልጅቷን የዩኒቨርሲቲ (የመካነ ትምህርት) ትምህርቷን እንድታቋርጥ በማድረግ፣ እኅቷን በገጀራ ጭንቅላቷን ፈልጦ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት በመዳረግ፣ እናቷን እንደሚገላቸው እየዛተ በማስፈራራት መግቢያ መውጫ በመንሳት፣ አባትየውን ለሕግ አካላት ኡኡ ቢሉ መፍትሔ የሚሰጥና ቤተሰባቸውን ከጥቃት የሚጠብቅ መብታቸውን የሚያስከብር የሕግ አካል በማጣታቸው ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ከጥቃት መታደግ ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ብስጭትና ለሥነ ልቡና መታወክ ተዳርገው ቆሽታቸው አሮ ለሞት በመዳረግ የመላ ቤተሰቡን ሕይወት በዚህ መልኩ በማመሰቃቀሉ የወ/ሮ መዓዛ ድርጅት ለዚህ የግፍ ሰለባ ቤተሰብ ጥብቅና ቆሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ የግፍ ሰለባ ቤተሰብ ጎን እንዲቆም በመሥራቱና የሕግ አካላት ለልጅቷና ለቤተሰቦቿ ፍትሕ ሊሰጡ ባለመቻላቸው ፍትሕ አለመኖሩን በመግለጣቸው አቶ መለስ እነ ወ/ሮ መዓዛ “ፍትሕ የለም!” ማለታቸው በመያዝ “በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብታቹሃል!” በሚል አንባገነናዊ ምክንያት ኢፍትሐዊ ውሳኔ ወስኖ የወ/ሮ መዓዛን ድርጅት እንዲዘጋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በዚያ ወቅት እነ ወ/ሮ መዓዛ ከወያኔ ደኅንነቶች በየዕለቱ ዛቻና ማስፈራሪያ እያስተናገዱ ብዙ መከራ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ እንዲህ ዓይነት የተጋድሎ ታሪክ ያላት ሰው ናት፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ይህ የተጋድሎ ታሪኳ በምዕራባውያኑ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ለዓለም አቀፍ ሽልማትም አሳጭቷት ነበር፡፡ አሁን በዚህ የወ/ሮ መዓዛ ሹመት ላይ የወያኔ/ኢሕአዴግ ቁማር ወይም ስሌት ምን እንደሆነ ግልጽ የሆነላቹህ ይመስለኛል፡፡
ባጭሩ ወያኔ ያሰበው ወ/ሮ መዓዛን በመሾም ምዕራባውያኑን ማጭበርበር ማወናበድ ነው የፈለገው፡፡ እንጅ ወ/ሮ መዓዛ ነጻ ሆና የፍትሕ አካሉን ችግር ለመቅረፍ የምትችልበት ምቹ ሁኔታ ኖሮ እሱን እንድታስተካክል ተፈልጎ አይደለም፡፡ በፍጹም አይደለም! የወ/ሮ መዓዛ ሹመት ከመጠቀሚያነት የሚዘል አይሆንም፡፡
የገረመኝ ነገር የወ/ሮ መዓዛ መሸወድ ወይም መታለል ነው፡፡ ይመስለኛል ልትታለል የቻለችው የለውጥ ኃይል ምንትስ የሚባለው ነገር እውነት መስሏታል፡፡ ይሄ ለውጥ ምንትስ የሚባለው ነገር የወያኔ ድራማ (ትውንተ ሁነት) መሆኑን አላወቀችም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለምክትል ሊቀመንበርነት ሹመት ተጠይቀው “አንፈልግም!” ላሉ ሦስት የነቁ ሰዎች ያለኝን አድናቆት መግለጥ እወዳለሁ፡፡
በዚህ ወቅት ለምን የሴቶች ወደ ሥልጣን መምጣት ሸፍጥ እንጅ ስኬት አይደለም! ወዳልኩት ጉዳይ ሳልፍ ያሳለፍነውና አሁንም ያለንበት አስከፊ የወያኔ አገዛዝ ዘመን አይደለምና ለሴት ለወንድ እንኳ ምን ያህል ፈታኝና እግጅ አስከፊ መሆኑን የምታውቁት ነው፡፡ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን በሕዝብ ትግል ውስጥ የነበሩ ሴት እኅቶቻችን ምን ዓይነት ነውረኛና አጸያፊ ግፍ እየተፈጸመባቸው፣ ቅስማቸው ተሰብሮ ከፖለቲካው (ከእምነተ አሥተዳደሩ) እራሳቸውን እንዲያገሉ እንደተደረገ የምታውቁት ነው፡፡ ሴት ልጅ ለጥቃት ተጋላጭ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ በተለይ የዚህ ግፈኛ አገዛዝ ዘመን ሴቶችን ወደ ትግል ወይም ወደ ፖለቲካው የሚጋብዝና የሚመችም አይደለም፡፡
ወ/ሮ መዓዛ ወያኔ የወደቀና ጣልቃ የሚገባባት የሌለ ስለመሰላት ነው እንጅ ሹመቱን የተቀበለችው በማስፈራሪያና በጥቃት የሚያንበረክከው ወያኔ የሔደ መስሎ ቤተመንግሥት ጓዳ ውስጥ ተደብቆ እንዳለ ብታውቅ ኖሮ እርግጠኛ ነኝ ሹመቱን አትቀበልም ነበረ፡፡ ወ/ሮ መዓዛ ወያኔ እንደተደበቀ አይደለም በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመን ፍትሕ የወያኔ/ኢሕአዴግን ጥቅም ከማስጠበቂያነት ፈጽሞ በምንም ተአምር ሊወጣ እንደማይችል ቢገባት ኖሮ ሹመቱን ባልተቀበለች ነበረ፡፡ ይህ ሁኔታ የወያኔ አባል የሆኑ ሹመኞች ቀርተው እሷ ስትሾም የሚቀር ከመሰላት ተሳስታለች፡፡
ነገ በተለያዩ መንገዶች እጇን ለመጠምዘዝ ሲሞክሩ ወይም የምትሰጠው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሳይሆን ሲቀር ስታይ ምን እንደምታደርግ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እነዚያ ለምክትል ፕሬዘዳንትነት (ሊቀመንበርነት) ተጠይቀው “እምቢ አንፈልግም!” ያሉት ሦስት ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎች ግን ይሄ በሚገባ ገብቷቸዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ያልገባቸው ሰዎች “መንግሥት የሆነ ፓርቲ የራሱን ሰው የመሾሙ ነገር ያለ ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለምም የሚሠራው እንደዚሁ ነው!” ሲሉ እሰማለሁ፡፡ አንዱ እንዲያውም የሁለቱን የአሜሪካ ዴሞክራትና ሪፐብሊካን ፓርቲዎችን (አስፋኔ ሕዝብ እና ሕዝብ አስመራጭ ቡድኖችን) የየራሳቸውን አባል ዳኛ የማሾም ሩጫን ጠቅሶ ለማወናበድ ሲጥር ታዝቤዋለሁ፡፡ እነኝህ ግለሰቦች ፍትሕን በማገልገል እና በፍትሕ በመገልገል መሀከል ያለውን ልዩነት እንደማያውቁ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡
ዲሞክራቶችና ሪፕብሊካኖች (አስፋኔ ሕዝቦች እና ሕዝብ አስመራጮች) የየራሳቸውን ዳኛ ለማሾም ጥረት የሚያደርጉት ያሾሙትን ዳኛ ሕዝብን በትጋት፣ በንቃት፣ በታማኝነት እንዲያገለግል በማድረግ በዳኛው በኩል ለፓርቲያቸው (ለቡድናቸው) ማስታወቂያ ከመሥራት ያለፈ ጥቅም ለማግኘት ወይም ፍትሕ እያዛቡ እራሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ አይደለም፡፡ ይሄ ፍትሕን ማገልገል ይባላል፡፡ በፍትሕ መገልገል ማለት ደግሞ እንደ ወያኔ ፍትሕን እያዛቡ በፍትሕ መጠቀም ማለት ነው፡፡
ዲሞክራቶችና ሪፕብሊካኖች የየራሳቸውን ዳኛ በማሾም ጥቅም ያገኛሉ ከተባለ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ለሕዝቡ “እንዲህ እንዲህ እናደርጋለን!” እያሉ ቃል የሚገቧቸውን ነገሮች ሕግ አድርጎ ለማጸደቅ የሚያሾሟቸው ዳኞች ወሳኝ ሚና ስላላቸው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ እነዚህ “በምዕራቡ ዓለምም ያለ ነው!” የሚሉ ግለሰቦች ግን ይሄ አልገባቸውም፡፡ ነገሩን የተረዱት በጣም በተሳሳተ መንገድ ነው፡፡
ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች (አስፋኔ ሕዝቦችና እና ሕዝብ አስመራጮች) የየራሳቸውን ዳኛ ለማሾም ይሟሟቱ እንጅ በፍትሕ መከበር፣ መጠበቅና በሕግ የበላይነት ፈጽሞ ልዩነት የላቸውም፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡
እናም በዚህ በወያኔ ዘመን የሴቶችን መሾም የምቃወመው የሴቶችን ብቃት አጠያያቂ አድርጌ አይደለም፡፡ ለሴቶች ሹመትም ሀገራችን እንግዳ አይደለችም ለሕዝቧም ብርቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእንዲህ ዓይነት ግፈኛና ነውረኛ የአገዛዝ ዘመን ሴቶችን በፖለቲካው (በእምነተ አሥተዳደር) እንዲሳተፉ ማድረጉ ለወያኔ ግፈኛና ነውረኛ ጥቃት ማጋለጥ ስለሆነ ነው፡፡ በግሌ ነጻ አስተሳሰብ ያላቸው ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ የምፈልገው የሰብአዊ መብትን ማክበር የሚችል መንግሥት ስናገኝ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ከማንም ቀድማ ሴትን ለሀገር መሪነት ደረጃ በማብቃትና በታሪኳ ከዐሥር በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ሀገር እንዲመሩ በማድረግ የሴቶችን ዕኩልነትና የአቅም ብቃት ላረጋገጠች ሀገር የሴቶች ለሥልጣን መብቃት ብርቅ ተደርጎ እንዲታይ መጣሩ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ነውርና አሳፋሪም ነገር ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ ምን ያህል ለታሪካችንና ለማንነታችን ባዕድና ሩቅ እንደሆንን የሚያሳይ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን ሴቶች የነበራቸውን ቦታ በተመለከተ ደጋግሜ መጻፌ ይታወሳል፡፡ እንዲያውም ከጉልበት በስተቀር በሌሎች አቅሞች ሁሉ ሴት በእጅጉ ከወንድ እንደምትልቅም
“ወንድና ሴት ዕኩል ናቸው!” ያለው ማን ነው? በፍጹም አይደሉም!
በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፌ ላይ መጻፌ ይታወሳል፡፡
አንድን ነገር ለስኬት ማብቃት ከፈለጋቹህ ሴቶች እንዲካተቱና እንዲደግፉት ማድረግ ዓይነተኛ መላ ነው፡፡ ሴትን ለሀገር መሪነት ማብቃቱ ቀርቶ የመምረጥ መመረጥና ከጓዳ ወጥቶ በሥራ ቦታዎች ሥራ የመሥራት መብት ከሰጡ መቶ ዓመት የማያልፋቸው ምዕራባውያኑ ግን ይሄ ዜና ብርቅ ሆኖባቸው በብዙኃን መገናኛዎቻቸው እያራገቡት ይገኛሉ፡፡
እነ ዐቢይም የሕዝባዊ ትግሉ ዓላማና ጥያቄ ሴቶችን ማሾም የሆነ በማስመሰል የሕዝብን አጀንዳ (ርእሰ ጉዳይ) ቀልብሰው ሴቶችን በመሾም ዜናውን ሁሉ የሴቶች በማድረግ እናገኘዋለን ብለው ካሰቧቸው ጥቅሞች አንዱ በዚህ መልኩ በምዕራባውያኑ በመወደስ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ነው፡፡
በሉ እንግዲህ ወገኖቸ ነገሩ ይሄው ነው፡፡ ንቁ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic